ኢትዮጵያ የመሬት አጠቃቀሟ ሳይንሳዊና ምክንያታዊ ባለመሆኑ የመሬት አጠቃቀም ችግር ለአገሪቱ ዕድገት እንቅፋት ሆኗል

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ኢትዮጵያ የመሬት አጠቃቀሟ ሳይንሳዊና ምክንያታዊ ባለመሆኑ፤ እንዲሁም ወጥ አገር አቀፍ ፖሊሲና የአሰራር ስርዓት ባለመዘርጋቷ እድገቷ እየተጓተተ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ። በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ትምህርት ክፍል ዲንና የዘርፉ ምሁር ዶክተር በላቸው ይርሳው፤ በኢትዮጵያ የመሬት አጠቃቀም ሳይንሳዊና ምክንያታዊ የሆነ ፖሊሲና አሰራር አልተዘረጋም። በዚህም መሬት የአገሪቱ የልማት ምንጭ ከመሆን ይልቅ የግጭትና የጭቅጭቅ ምንጭ ሆኗል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ለከተማ፤ ለግብርና፤ ለኢንዱስትሪ እና ለሌሎች ዓላማ የሚውል የመሬት ይዞታና ሳይንሳዊና ምክንያታዊ የሆነ የመሬት አጠቃቀምና አሰራር አልተዘረጋም ይላሉ። እንደምሁሩ ገለፃ፤ የገጠርና የከተማ አስተዳደርን አጣጥሞ ማስተዳደር አልተቻለም፤ የመሬት አጠቃቀምም ሳይንሳዊ አልተደረገም። ከተሞች ሲስፋፉ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ባረጋገጠና የከተማ ነዋሪዎችን ችግር በሚፈታ መልኩ አይደለም። በዚህም፤ አርሶ አደሮችን ለስደትና ለከፍተኛ ችግር እየዳረገ ነው።

የከተማ ነዋሪዎቹም በብዙ ችግር የሰሩት ቤት ህገወጥ ናችሁ በሚል ይፈርስባቸዋል። ከተሞች በሳይንሳዊ የመሬት ስሪት ስለማይገነቡ ለዜጎች ምቹ አይደሉም፤ ደረጃቸውንም ያልጠበቁ ሆነዋል። በአጠቃላይ አገር አቀፍ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ባለመኖሩና የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ ባለመደረጉ የአገሪቱን ልማት በእንቅፋት የተሞላ ሆኗል። ከዚህም በላይ ሌብነት እንዲስፋፋ፤ የዜጎች ሰብዓዊመብት እንዲጣስ ምክንያት ሆኗል። ሕዝቡንም ለግጭትና ለሌሎች ችግሮች እየዳረገ መሆኑንም ያብራራሉ። በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ቦጋለ ተረፈ፤ ኢትዮጵያ መሬቷን በፖሊሲና በተቀናጀ የአሰራር ስርዓት ባለመምራቷ የከተማውን ብቻ ሳይሆን የግብርናውን ዘርፍ እንቅፋት ሆኗል። የአገሪቱንም ልማት ወደኋላ እየጎተተው እንደሆነ ይናገራሉ።

ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተቀረጸ የገጠርና የከተማ የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲና ስርዓት የለም። በመሬት የሚጠቀሙ የተለያዩ ባለድርሻዎች የሚገዙበት ስርዓትም የለም። ይህም ባለመሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት በተደረገው ጥናት በአንድ ቦታ ላይ የተለያዩ አካላት ለተለያየ ዓላማ ለመፈጸም አቅደው ተገኝተዋል። ለመሬት ሽሚያ ምክንያትም ሆኗል። የአገሪቱን የመሬት አቅም በመለየት እንደየሁኔታው ባለመጠቀም ተገቢው ውጤት እንዳይመጣና ለአገሪቱ ልማት እንቅፋት መሆኑ ተመላክቷል። ከዚህም ባለፈ ለሰላም እንቅፋትና ለሌብነት ምክንያት መሆኑም በጥናቱ መረጋገጡን ያመላክታሉ።

የላይፍ ኮንሰልተንሲ አማካሪ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዳምጠው ወልዴ፤ የዜጎች በከተማ የመኖር ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል። ይሁን እንጂ፤ ሳይንሳዊ የመሬት አጠቃቀምና የመረጃ ስርዓት ባለመኖሩ የሕዝቡን ፍላጎት የሚያረካ ስራ ማከናወን አልተቻለም። ከዚያም በላይ በየትኛውም ደረጃ የወጡ ህጎችን ተግባራዊ ማድረግ አዳጋች ሆኗል። በዚህም የአገሪቱ ከተሞች የማደግ ዕድላቸው ሰፊ ቢሆንም፤ ዕድላቸውን እየተጠቀሙ አይደለም። በዚህም አገሪቱ እየተጎዳች ነው ይላሉ። ኢንጅነሩ እንደሚናገሩትም፤ ለከተሞች ዕድገት የሆነውን ችግር ለመፍታት ቤት ከማፍረስ የመሬት አጠቃቀምና የቤት ግንባታ ስርዓቱን በወቅቱ ማስተካከል ይገባል።

ህጎችና አሰራሮችን በመዘርጋት በተገቢው መንገድ ውስኑን የመሬት ሀብት የዜጎችን ፍላጎት በሚያረካ መልኩ መጠቀም። የመረጃ ስርዓት ማዘመንና መተግበር አስፈላጊ ነው። ጥናትን መሰረት አድሮጎ በየጊዜው ማስተካከያ እርምጃ መውሰድም አስፈላጊ ነው። ይህ ከተከወነ አገሪቱ ዘመናዊ ኮተሞች እንዲኖራት እንደሚያደረጋት ይጠቁማሉ። ኢንጂነሩ ከዚህም በተጨማሪ፤ በአገሪቱ ያሉትን የመሬት አጠቃቀም ህጎች ማጥናትና ማስተካከያ መደረግ ያለበትን ማስተካከል፤ ማስተካከያ ከተደረገ በኋላም ግንዛቤ ማስጨበጥ፤ ተቋማትን ማጠናከር ይገባል ይላሉ።

በከተሞች ያለውን የቤት አቅርቦት ለመፍታትና ከተሞችን ለማሳደግ የመሬት አጠቃቀም አማራጮችን ማስፋት አስፈላጊ ነው። ሁሉም ባለድርሻ ተቀናጅቶ በሚቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል። የፌዴራል የከተማ መሬትና መሬት ነክ ምዝገባና መረጃ ኤጄንሲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ዘውዱ፤ የከተማ መሬት አያያዝ የዘመነ አለመሆኑ የከተማ መሬትን በአግባቡ ለመጠቀም እንቅፋት ሆኗል። ዜጎችም ለተለያየ ችግር መዳረጋቸውን አንስተው ኤጄንሲው የከተማ ይዞታዎችን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማረጋገጥ የሚያስችል ስርዓት እየዘረጋ ነው።

በዚህም በከተማ አስተዳደሮችና በክልሎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው። የመረጃ ስርዓቱ ሙሉ በሙሉ ተዘርግቶ መረጃው ከተደራጀ በከተማ ያሉትን ህጋዊ መሬቶች መረጃ እጥረት እንደሚቀርፍ ይናገራሉ። የግብርና ሚኒስቴሩ ባለሙያ አቶ ቦጋለ በበኩላቸው፤ የአገሪቱ መሬት ያለው ይዘት በጥናት ተለይቶ ለተለያየ ዓላማ የሚውሉ መሬቶችን ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል። በተቀመጠው ፖሊሲና ስርዓት መሰረትም ሁሉም ባለድርሻ መጠቀም ይገባዋል። ይህ ስርዓት ካልተዘረጋ ግን በአገሪቱ መፃኢ ዕድል ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር በማንሳት፤ ይህን ለማስተካከል የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ያስጠነቅቃሉ።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲው ዶክተር በላቸውም፤ መንግስት በመሬት ላይ ያለውን ችግር ለማስተካከል በአገሪቱ ወጥ የሆነ የመሬት አጠቃቀምና አሰራር ስርዓት መዘርጋት አለበት። ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግና የሚተገበር መሆንም አለበት። የገጠርና የከተማ አስተዳደሮችን አጣጥሞ የመሄድ እና አርሶ አደሮችና በቦታው ላይ የሚሰፍሩ ዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው። የገጠርም መሬት ቢሆን ምርታማነትን መሰረት አድርጎ መለየት እንዳለበትም ያመላክታሉ። አሰራሩን ተግባራዊ ለማድረግም ዘመናዊ የአስተዳደር ስርዓት መዘርጋት፤ ባለሙያዎችን መጠቀም፤ ዘርፉን ከሌብነት ማጽዳት፤ አገር አቀፍ ዘመናዊ የመረጃ ስርዓት መዘርጋት፤ ለሁሉም ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ እና የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል።

በከተሞች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ እንደኮንደሚኒየምና ሌሎች አመራጮችን በመጠቀም ቤት ማቅረብ፤ ለዚህም እንደ ተዘዋዋሪ ፈንድ ያሉ ስርዓቶችን በመጠቀም የመሬት አጠቃቀምን ሳይንሳዊና ወጤታማ ማድረግ፤ መሬት የመንግስትና የህዝብ በመሆኑ በህገ ወጥ መንገድ የሰሩትን ወደ ህጋዊ መስመር ማስገባትና ከዚያ በኋላ ወደህገ ወጥነት እንዳይገቡ ማድረግ፤ ህጋዊ ስርዓቱን ተላልፈው የሚገቡም ሲገኙ የቤት ባለቤቶቹን ብቻ ሳይሆን የመንግስት መዋቅሩንም አብሮ ተጠያቂ ማድረግ መሬትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያስችል ይመክራሉ።

በኢትዮጵያ በገጠርም ይሁን በከተማ የመሬት ሳይንሳዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም በስፋት አይታይም። በዚህም የተነሳ ከተሞች ዘመናዊና ለነዋሪዎች ምቹ እንዳይሆኑ ምክንያት ሆኗል። በገጠርም ቢሆን መሬቱ ምርታማ ሊሆንበት የሚችለውን ሰብል ባለመለየቱና ሳይንሳዊ አጠቃቀም ባለመኖሩ አገሪቱ የምትጠብቀውን ያህል ምርት እንዳታገኝ አድርጓታል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ዘመናዊ የመሬት ፖሊሲና አሰራር ስርዓት መዘርጋት ለነገ የማትለው ስራ ነው። አለበለዚያ፤ ኋላ ቀርና ለዜጎቻቸው የማይመቹ ከተሞች ይኖሯታል። በገጠርም ለምርታማነት መቀነስ ምክንያት ይሆናል። ከዚህም በላይ ከህዝብ መብዛት ጋር ተያይዞ አገሪቱን ወደ ቀውስ ሊከታት ይችላል። በመሆኑም መንግስት በቶሎ ወደ ስራ መግባትና የአገሪቱን ልማት ማስቀጠል ይኖርበታል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2011

በአጎናፍር ገዛኸኝ

Share.

About Author

Leave A Reply