ኢትዮጵያ የቻይና ብድሯን መክፈል ቢሳናት ምን ይፈጠራል? DW

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ስሪ ላንካ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሺየቲቭ የተበደረችውን ገንዘብ መክፈል ሲሳናት ወደቧን ለ99 አመታት ለቻይና አሳልፋ ለመስጠት ተገዳለች። የዓለም አቀፍ ንግድ አማካሪው አቶ ሞገስ በቀለ “ይኸ ወደ ኢትዮጵያ የማይመጣበት ምክንያት አይኖርም” የሚል ሥጋት አላቸው። በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለው የተዛባ የንግድ ሚዛንም አሳሳቢው ጉዳይ ነው

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተሳተፉበት እና ከሚያዝያ 17 እስከ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሔደው የመቀነት እና መንገድ ዕቅድ ስብሰባ (Belt and Road Forum) ኢትዮጵያ ከቻይናው የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ-ልማት ግንባታ ኩባንያ (State Grid Corporation of China) ጋር የ1.8 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራርማለች። ገንዘቡ ለ16 የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ለኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል የመሰረተ-ልማት ግንባታ ለማከናወን ሥራ ላይ እንደሚውል የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።

አራት ቢሊዮን ዶላር የወጣበት እና 752 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር አገልግሎት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሯትን አገር ከዕዳ ጫና ውስጥ ከከተቱ ውድ ሥራዎች መካከል ቀዳሚው ነው። አንዴ በኤሌክትሪክ መቋረጥ ሌላ ጊዜ በአፋር ክልል በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ግልጋሎቱ ሲቆራረጥ የታየው ይኸ የባቡር አገልግሎት እስካሁን እዳውን ጨርሶ መክፈል አልቻለም። ኢትዮጵያ ከቻይና ያበጀችው ወዳጅነት ስኬታማነት ማሳያ ተደርገው ከሚቆጠሩ ሥራዎች መካከል ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የተዘረጋው የምድር ባቡር አገልግሎት ይገኝበታል። የዓለም አቀፍ ንግድ አማካሪው አቶ ሞገስ በቀለ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከቻይና ባበጀችው ወዳጅነት ፖለቲካዊ እና ምጣኔ-ሐብታዊ ትርፍ አግኝታበታለች።

አቶ ሞገስ “ቻይና በፖለቲካው አንፃር ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ፖሊሲ ለማመጣጠን የሚያስችል አማራጭ ኃይል ሆናለች። በአሁኑ ሰዓት ቻይና ከተለያዩ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት እያሰፋች መጥታለች። ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሺየቲቭ በሚባለው የትብብር ስምምነት ከመቶ በላይ አገራት ጋር ውል ስምምነት ገብታለች። ያ ደግሞ ከፖለቲካ አንፃር ተደማጭ ሆና እንድትቀርብ አስችሏታል። ሌላው ኢትዮጵያ ለተለያዩ የመሰረተ-ልማት ፕሮጀክቶች የምትፈልጋቸውን ብድሮች በአጭር ጊዜ እና በምትፈልገው መጠን እንድታገኝ በር ከፍቶላታል” ሲሉ ይናገራሉ።

475 ሚሊዮን ዶላር የፈጀው እና ዛሬም የመንገደኞችን ፍላጎት መሙላት ያልሆነት የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር መጓጓዣ ኢትዮጵያ ከቻይና የመሰረተችው ወዳጅነት ውጤት ነው። በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበው የአዲስ አበባው አደይ አደባ ስታዲየም ግንባታ በቻይናዎች ይከወናል። በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ሆቴል አጠገብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያስገነባው ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ የቻይና ኩባንያዎች ማስታወቂያ እና ቻይናውያን ሰራተኞች በብዛት ይታዩበታል። ከሌሎች በርካታ የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች ጀርባ ቻይና እና ቻይናውያን በገንዘብ፣ በሰው ኃይል እና በግንባታ ሲሳተፉ ይታያል።

ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በቅርበት ያጠኑት የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ጉዳዮች ተመራማሪ አቶ ጌዲዮን ገሞራ ጃለታ እንደሚሉት ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች ለመሰረተ-ልማት ግንባታ የሚያሻቸውን ገንዘብ በማቅረብ ጉድለታቸውን ሞልታለች።
አቶ ጌዲዮን “የአፍሪካ አገሮች ፋይናንስ የማግኘት ችግር አለባቸው። የራሳቸውን ገንዘብ አሰባስበው የመንገድ፤ የትምህርት ቤት እና የሆስፒታል [አገልግሎቶች] የማሟላት ችግር አለባቸው። መንገድ ከሌለ ኤኮኖሚው ሊያድግ አይችልም። የአፍሪካ ልማት ባንክ ያወጣው ሰነድ በመሠረተ-ልማት ረገድ ወደ 60 ቢሊዮን ዶላር ጉድለት አለ ይላል። ኢትዮጵያንም ሌላ የአፍሪካ አገሮችንም ከአገር ውስጥ ገንዘብ የመሰብሰብ አቅማቸው ከአጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠናቸው ከ10 በመቶ በታች ነው። ስለዚህ ከዚያ ችግር ውስጥ ለመውጣት እንዲህ አይነት ፕሮጀክቶችን መጠቀም ምንም ጉዳት የለውም” ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግንባታቸው የተጓተቱ የስኳር ፋብሪካዎችን ለማጠናቀቅ የቻይና ገንዘብ እና ኩባንያዎች እገዛ አስፈልጎታል። ካንስ የተባለ የቻይና ኩባንያ የጣና በለስ እና የወልቃይት የስኳር ፋብሪካዎችን እየገነባ ነው። የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት የስኳር ፋብሪካ ጄጄአይስ ለተባለ ሌላ የቻይና ኩባንያ ተሰጥቷል። አቶ ጌዲዮን “በአፍሪካ ኅብረት አንገብጋቢ የሚባሉ ፕሮጀክቶች አሉ። ከዚያ ውስጥ አንዱ የአጀንዳ 2063 የፈጣን ባቡር ነው። ከዚህ በተጨማሪ ርዋንዳ ላይ ባለፈው አመት የተፈረመ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት አለ። 22 አገሮች ፈርመዋል፤ ሕግ ይሆናል ፤ እርስ በርስ ይገበያያሉ። ያ ማለት መንገድ ማደግ አለበት፤ አየር መንገድ ማደግ አለበት፤ ባቡሩ ማደግ መቻል አለበት። የአፍሪካ አገሮች ፍላጎታቸውን አስተባብረው [ገንዘብ] ከቻይና መውሰዱ ችግር የለውም” ሲሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች ወደ ቻይና ማማተራቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ።

ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ጠለቅ ብለው ያጠኑት ባለሙያው ኢትዮጵያን የመሰሉ አገሮች የሚበደሩት ገንዘብ “ለመጣለት አላማ ካልዋለ እና የሙስና ወጥመድ ውስጥ ከወደቀ በጣም ከባድ ነው። የዕዳ ጫና ይፈጥራል። ያንን ለመክፈል ደግሞ አገሮች ችግር ውስጥ ይወድቃሉ። ይኸ ዕዳ በየሶስት ወሩ ነው የሚከፈለው። በጣም የዶላር ጫና ይፈጥራል” የሚል ሥጋት አላቸው።

Share.

About Author

Leave A Reply