Thursday, January 17

‹‹እነ ቴሌን ለግል ባለሀብት?›› ታሪካዊ ስህተት ወይንስ መልካም አጋጣሚ ?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሰሞኑ ካስተላለፋቸው አበይት ውሳኔዎች አንዱ በመንግስት እጅ ውስጥ የቆዩ ግዙፍ የንግድ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ለግል ባለሃብቶች እንዲዘዋወሩ መፍቀድ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ለዓመታት ‹በግል ባለሀብቶች እጅ ሊገቡ አይገባም› በሚል መንግስት ሲሟገትላቸው የባጁትን ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫዎች እና የባህር እና ሎጂስቲክ ባለስልጣንን በሙሉ ወይንም ‹በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ› ወስኗል፤ይሄ ውሳኔ ከተሰማ በኃላ የድጋፍ እና ነቀፌታ ሀሳቦች ተከትለዋል፡፡

ቢቢሲ ባናገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ዘንድም ጉዳዩ ለየቅል የሆነ አቀባባል እንዳለው ለማጤን ችሏል፡፡ በመንግስት እጅ ውስጥ የቆዩ የንግድ ድርጅቶችን ወደ ግል የማዞር ጽንሰ ሀሳብ በፖሊሲ ደረጃ ከተያዘ ሃያ ዓመታት ግድም እንዳለፉት የሚጠቅሱት የአግሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር ደምስ ጫንያለው፣ የአሁኑ የመንግሥት እርምጃ ልዩ የሆነው ግዙፍ የንግድ ተቋማት ለግል ባለሀብቶች ተሳትፎ ክፍት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ እንደሆነ ያስገነዝባሉ።

‹‹ለኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶች ክፍት መደረጋቸው ትልቅ እመርታ ነው፡፡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች (እንደ ኢትዮቴሌኮም) ባሉ ድርጅቶች ውስጥ ገብተው ከፍተኛውን የሀብት ድርሻ ኢትዮጵያዊያን እንዲይዙት ማድረግ ቢቻል ትልቅ ለውጥ ነው›› የሚሉት ዶ/ር ደምስ ውሳኔው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲጠናከሩ እገዛ እንደሚያደርግ ያስረዳሉ፡፡ ብዙ ባለሀብቶቻችን ይሄን መሳይ ‹የኢንቨስትመንት› አማራጭ ስላልነበራቸው የባንክ ሼርን መግዛትን በመሰሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተጠምደው እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ሃላፊ እና በአሁኑ ጊዜ ‹ኢንሺየቲቭ› አፍሪካ የተሰኘው ተቋም መስራች እና ስራ አስፈጻሚ አቶ ክብር ገና ግን ፈላጊ ያላቸው፣ ትርፍ እያስገኙ ያሉ ትልልቅ የንግድ ድርጅቶችን ለግል ባለሀብቶች ማስተላላፍ ትልቅ ጉዳት እንዳለው ይሟገታሉ፡፡ ለአብነት የሚጠቅሱት ጉዳት ደግሞ፣ ለልማት ስራዎች ማስፈጸሚያ ይውል የነበረው የንግድ ድርጅቶቹ ገቢ ለባለሀብቶች ግላዊ ብልጽግና ብቻ ሊውል የመቻሉን ዕድል ነው፡፡

‹‹ለምሳሌ ኮሚዩኒኬሽን እስከ 2 ቢሊየን ብር ድረስ የዘጠኝ ወር ገቢ ነበረው፡፡ በየዓመቱ እያደገ ያለና ለልማት የሚውል ገቢ ያለው ድርጅት ነው፡፡ ለግል ባለሃብት ተላለፈ ማለት (በተለይ ለውጭ ባለሀብት ከተሰጠ) ይሄንን ገንዘብ ይዞ ወደ ሀገሩ ከመሄድ ባሻገር በእኛ ሀገር ‹ኢንቨስት› የሚያደርግበት ምክንያት የለውም፡፡ የግል ባለሀብቱ ኢትዮጵያዊ ነው ብንልም እንኳ ገቢውን ለልማት ያውለዋል ለማለት ያስቸግራል፣ በዚህም ምክንያት ለልማት ይውል የነበረው ገንዘብ ይቀንሳል፡›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ ባሻገር እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ‹በሰራተኞቻቸው የዓመታት መስዋዕትነት› ለትርፍ የበቁ ተቋማትን ለግል ለማስተላላፍ መሞከር ‹ሀገርን መከፋፈል› ነው ሲሉም ይቆጫሉ፡፡

የአቶ ክቡር ገናን ስጋት የሚጋሩ ወገኖች ጨምረው ከሚያነሷቸው ስጋቶች አንዱ እነዚህ ድርጅቶች በግል ባለሀብቶች በመያዛቸው ምክንያት የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ዋጋ ሊያሻቅብ ይችላል በሚል የሚጠቃለል ነው፡፡

ዶ/ር ደምስ ጫንያለው የዋጋ ማሻቀቡ የሚፈጠር ከሆነ ጫናው በሰራተኛው ማህበረሰብ ዘንድ እንዳይበረታ የሚያደርግ መላ ይጠቁማሉ፣ ‹‹በግል ዘርፉ ውስጥ ተሳታፊ ሰራተኞች የሚያገኙት ገቢ የሚመለከት የፖሊሲ ርምጃዎችን መውሰድ ያስልጋል፡፡ ለምሳሌ የዝቅተኛ ደሞዝ ፖሊሲ የለንም፣ እየጮህን ነው ያለነው፡፡ ፍትሃዊ የጉልበት ዋጋ ተመን ከተቀመጠ የዋጋ ጭማሪ አያስፈራንም፣›› በማለት ጭማሪው በግልም ሆነ በመንግስት ስር ተቀጥሮ ከሚሰራው ሰራተኛ የገቢ ሁኔታ ጋር የተስማማ እንዲሆን መጣር እንዳለበት ይመክራሉ፡፡

ኢትዮ-ቴሌኮምን የመሳሰሉ ተቋማት ከመሰል የጎረቤት ሀገር ድርጅቶች የአገልግሎት ክፍያ ጋር ሲነጻጸሩ ውድ መሆናቸውን የሚያነሱት ዶ/ር ደምስ በአሁኑ እርምጃ ተጠቃሚዎች በተሻለ ዋጋ የተሻለ አገልግሎት የሚያገኙበት ዕድል ሊኖር እንደሚችልም ተስፋ አላቸው፡፡

ከሁሉም ከሁሉም ግን መንግስት የተቆጣጣሪነት ሚናውን በበቂ ሁኔታ ቢወጣ ስጋቶቹን መመከት እንደሚቻል ጨምረው ይመክራሉ፡፡ ከዚህ በዘለል ግን አሁንም በውሳኔው ውስጥ የተዘረዘሩ ድርጅቶች በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ የሚይዙትን ድርሻ አጋኖ ማስላትም ሊታሰብበት እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡ ለእሳቸው እኒህ ድርጅቶች ያላቸው የኢኮኖሚ ድርሻ ከ15 በመቶ አይዘልም፣ ግብርናው ቀሪውን 85 በመቶ በመያዝ አሁንም የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ባለውለታነቱን ቀጥሏል፡፡

በውሳኔው መጻኢ ውጤት ላይ ከሚደረጉ ሙግቶች ጎን ለጎን የሚንሸራሸረው ጥያቄ በአሁኑ ወቅት እነዚህን ተቋማት ወደ ግል ማዘዋወር ለምን አሰፈለገ ? የሚለው ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማህበር የማክሮ ኢኮኖሚ ተመራማሪ ዶክተር ሰኢድ ኑሩ የአሁኑን ውሳኔ ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ችግር አንጻር ይመለከቱታል፡፡ኢትዮጵያ ካለባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመውጣት፣ በብድር ተጀምረው ያላለቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ፣ ብሎም በዓለም የንግድ መድረክ የምትወቀስባቸው የኢኮኖሚ አቋሞች ላይ ለውጥ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ማሳያ ትዕምርታዊ እርምጃ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ምንጭ. ቢቢሲ

Share.

About Author

Leave A Reply