እነ አቶ በረከት ስምዖን ጠበቆቻቸው ባሉበት ቦታ ሆነው በፕላዝማ ወይም አይሲቲ ቴክኖሎጂ እንዲከራከሩላቸው ጠየቁ፡፡

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 8/2011ዓ.ም (አብመድ) በአቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሳ ካሳ ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቷል፡፡ ክሱንም ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍረድ ቤት በጽሑፍ አቅርቧል፡፡

ተከሳሾቹ ክሱን ለማንበብ በቂ ጊዜ አንዳልነበራቸው በመጥቀስ መልስ ለመስጫ ተጨማሪ ቀናትን ጠይቀዋል፡፡ ጉዳያቸውን የሚከራከርላቸው ጠበቃ እንደሌላቸው እና ከዚህ በፊት የመጡት ጠበቆቻቸውም ለደኅንነታቸው በመሥጋት መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ባሉበት ሆነው በፕላዝማ ወይም በአይ ሲ ቲ ቴክኖሎጂ መከራከር እንዲችሉ እንዲፈቅድላቸውም ጠይቀዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ክሱን ለተከሳሾቹ ያቀረበው ትናንት ማለትም ሚያዝያ 7 ቀን 2011ዓ.ም በመሆኑ ተከሳሾቹ የጠየቁት የጊዜ ቀጠሮ ላይ ተቃውሞ እንደሌለው አስታውቋል፡፡ የተከሳሾችን ደኅንነት መጠበቅ የክልሉ መንግሥት ኃላፊነት እንደሆነና ልዩ ከለላ ተሰጥቷቸው መከራከር እንዲችሉ መደረግ እንዳለበት የገለጸው ዐቃቤ ሕግ ‹‹የፕላዝማ ቴክኖሎጂ እስካሁን ያልተሞከረ እና አስቸጋሪ ነው›› ብሏል፡፡

ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱ የክልሉ መንግሥት የጠበቆቹን ደኅንነት እንዲጠብቅ እና ጠበቆቹ መጥተው እንዲከራከሩ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹ የህግ ምክር እና እገዛ የማግኘት መብት እንዳላቸውም ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ በጠየቁት መሠረት ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ስድስት ቀናት በመፍቀድ ተለዋጭ ቀጠሮ ለሚያዝያ 14 ቀን 2011ዓ.ም ሰጥቷል፡፡

ከእነ አቶ በረከት ስምዖን ጋር በተጠርጣሪነት አቶ ዳንዔል ግዛው አብረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ጉዳያቸውን አብሮ ለማየትም ፍርድ ቤቱ ለሚያዝያ 14 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ዘጋቢ፡- ቢኒያም መስፍን

Share.

About Author

Leave A Reply