እንግሊዝ የኢትዮጵያን የግብር አሰባሰብ ስርዓት የሚያሻሽል ፕሮግራም ይፋ ልታደርግ ነው።

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ፕሮግራሙ በእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት (ዲ ኤፍ አይ ዲ) የሚተገበር ሲሆን፥ ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ 35 ሚሊየን ፓውንድ መመደቡን የእንግሊዝ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የድርጅቱ ዋና ፀሃፊ ፔኒ ሞርዳውንት ፕሮግራሙን ዛሬ ይፋ የሚያደርጉ ሲሆን፥ ከፋይናንስና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ።

ዋና ፀሃፊው ከፕሮግራሙ ይፋ መሆን በኋላም ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ጋር እንደሚወያዩም ይጠበቃል።

በቆይታቸው በሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የሚገኘውን የእንግሊዝ ጨርቃ ጨርቅ አምራች የሆነውን ፋብሪካ የሚጎበኙ ይሆናል።

በተጨማሪም በ80 ሚሊየን ፓውንድ ለቀጣዮቹ ስድስት አመታት የሚተገበረውን እና፥ የተቸገሩ ኢትዮጵያውያንና ስደተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የስራ እድል ፈጠራ ፕሮግራም አፈጻጸም የሚጎበኙም ይሆናል ነው የተባለው።

እንዲሁም የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት በሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለሚገኙ ሰራተኞች ደህንነትና ዋስትና የሚያደርገውን የ3 ሚሊየን ፓውንድ ድጋፍም ይፋ ያደርጋሉ።

ከዚህ ባለፈም በሃገር ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን በመጎብኘት የተደረጉ ድጋፎችና የተገኙ ውጤቶችን ይገመግማሉ።

የሲቪክ ማህበራትን በተለይም የአካል ጉዳተኞችን ማገዝ የሚያስችል የ9 ሚሊየን ፓውንድ ፕሮግራም ይፋ ማድረግም የጉብኝታቸው አንድ አካል ነው።

ዛሬ ይፋ ይሆናል የተባለው የግብር አሰባሰብ ማሻሻያ መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የግብር አሰባሰብ ስርዓት በማዘመን ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ያግዛል ተብሏል።

ይህም የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በማጠናከር ሃገሪቱ የምታካሂደውን የድህነት ቅነሳ ፕሮግራም በራስ አቅም ለመሸፈን ያስችላል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም ኢንቨስትመንትን እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለማስፋፋትና ለማሳደግ ያግዛልም ነው የተባለው።

Share.

About Author

Leave A Reply