Thursday, January 17

እውን ለጃዋር መሀመድ የቀረበው ጥያቄ ጊዜ ያለፈበት ነው?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በቅንነት የቀረበ ጥያቄ ቀና ምላሽ ይሻል!

የፖለቲካ ምሁሩና አክቲቪስቱ አቶ ጃዋር መሐመድ ከናሁ ቲቪ ጋር በነበረው ቆይታ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን አስመልክቶ ከ23.56ኛው ደቂቃ ጀምሮ በሰጠው ማብራርያ ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፦

“..በኦሮሞ ሕዝብ ስም የትግራይ ሕዝብ አይጨቆንም፣ የሶማሌ ሕዝብ አይጨቆንም፣ በኦሮሞ ሕዝብ ትግል ስም ሥልጣን ላይ የወጣ ማንኛውም ፓርቲ ሆነ ግለሰብ በሌሎች ብሔሮች ላይ አምባገናን ሆኖ ሌሎች ብሔሮችን ከሚጎዳ ብቃጠል ብሞት ይሻለኛል። ልክ ለኦሮሞ ሕዝብ ሌት ተቀን እንደሠራሁት ሌላውም ሕዝብ እንዳይጨቆን፣ እንዳይገለል፣ መድልዎ እንዳይደረግበት በግንባር ቀደምትነት እቆማለሁ”

እንግዲህ ጃዋር በዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት ለኦሮሞው ብሔር መብት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች መብት መከበር በእኩል ደረጃ እንደሚታገል በቃለ መጠይቁ ሂደት አስታውቋል… ይበል የሚያሰኝ ነው።

በሌላ አንፃር አክቲቪስት ታማኝ በየነ ባለፈው እሑድ በሚሊኒየም አደራሽ ለአቶ ጃዋር ያደረገው ጥሪ ይህን ይመስላል፦

“….ኢትዮጵያ የሚጠቅማት የተለያየ ሐሳብ የሚንሸራሸርባት ሀገር ከሆነች በልቡ ቂም የሚቋጥር አይኖርም፣ ስለዚህ በየቦታው ያሉ የተለያየ የፖለቲካ እምነት የሚያራምዱ ወንድሞች ኢትዮጵያዊያን አሉ። ከነዚህም ውስጥ አንዱ የኦሮሞ ወጣቶችን የኦሮሞን ሕዝብ ትግል እየመራ እያስተባበረ የሚገኘው ወጣት ጃዋር መሐመድ በኢትዮጵያ ውስጥ ለኦሮሞ መብት መታገሉን የኦሮሞ ወጣቶች በፍቅርና በአክብሮት ተቀብለውታል።፣ ዛሬ በዚህ መድረክ ላይ ሆኜ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ለጃዋር ጥያቄ አቀርባለሁ። አንተ ለኦሮሞ ለትግሬው ለሁሉ እንድትቆም ለኢትዮጵያ የምትታገል ሆነህ ኢትዮጵያን በፍቅር አንድ ሆነን እንድንረዳት በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም እጠይቅሃለሁ”

እንግዲህ እዚህ ጋ ልብ በሉልኝ። ጃዋር ናሁ ቲቪ ላይ ባለፉት ዓመታት ለኦሮሞ ሕዝብ ሙብት መከበር በታገለበት ልክ ሌላው ቀርቶ የኦሮሞ ፖለቲከኞችንም ቢሆን የብሔሮችን መብት ከጣሱ በግንባር ቀደምትነት እንደሚፋለማቸው አስቀድሞ ተናግሯል። የታማኝ ጥያቄም ለዚሁ አቋሙ አፅንዖት የሚሰጥ ጥያቄ እንጂ ከጃዋር ነባር አቋም ጋር የሚላተም አይደለም፣ ታማኝ ከዚህም ባለፈ ጃዋር የያዘውን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እንዲቀይር ጥያቄ አላቀረበለትም። እንዲያውም በሀገሪቱ ውስጥ ልዩ ልዩ ሐሳቦች መንሸራሸራቸውን እንደ ትሩፋት ቆጥሮ ነው ያነሳው።

ያልገባኝ፦

1. የጃዋር ምላሽ፦ ጃዋር በፌስ ቡኩ ገፅ ላይ በለጠፈው ምላሹ መነሻ ላይ ታማኝ ጥያቄውን በቅንነት ያነሳው መሆኑን ይጠቁምና ግን ጥሪው የዘገየ መሆኑን ይናገራል። የታማኝ በየነ ወንድማዊ ጥያቄው የሚያተኩረው ደግሞ “ስለምትቀጥለው ኢትዮጵያ” እንጂ ስላለፈችው ኢትዮጵያ አልነበረም። የእኔ ጥያቄ የታማኝ ጥያቄ ጃዋርም እንዳነሳው በቅንነት የቀረበ እስከሆነ ድረስ ጃዋርም ረዥሙን የሐቲት ሐረጎቹን ባለፈው ነገር ለመወቃቀስ ከመመደብ ይልቅ እንደ አንድ ምራቁን እንደወጣ ፖለቲከኛ ጥያቄውን በምሥጋና ተቀብሎ ባመነበትና እርሱም ናሁ ቲቪ ላይ በግልፅ እንደተናገረው ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሙብት እንደሚታገል በድጋሚ ለታማኝ ወንድማዊ እጋርነቱን ቢያረጋግጥለት ምን አለበት? የሚል ነው። የጃዋር ምላሽ ውስጥ ግን የአንበሳውን ድርሻ የወሰደው የትግሉ ትርክትና የስኬቱ ባለቤትነት ጥያቄ መሆኑ አሳዝኖኛል። በዚህም ሂደት ታማኝን የድል አጥቢያ አርበኛ አድርጎ ለመሳል የተሞከረ ይመስላል። ከዚህ በፊት ታማኝ የትግል አጋርነት ጥያቄ በግል ካላቀረበም በመጠኑ ወቀስ አድርጎ አጋርነቱን ቢገልፅ በቅንነት ለቀረበ ጥያቄ በቅንነት የተሰጠ ምላሽ አድርገን በተቀበልን ነበር። ጃዋር ግን በቀጥታ የትግል አጋርነት ምላሹን ከመስጠት ይልቅ በትግሉና በስኬቱ “Narrative” ጀምሮ በዚያው መደምደሙ እንደ እኔ የሚደገፍ አይደለም። ባይሆን ማጠቃለያው ላይ ለሁሉም ብሔሮች መብት መከበር መታገል የወትሮ አቋሙም መሆኑን ለታማኝ አስምሮለትና ጥያቄውንም በደስታ የሚቀበለው መሆኑን ዳግም ቢያረጋግጥለት ምላሹ የአንድ ባሳል ፖለቲከኛ ምላሽ ተደርጎ ይወሰድለት ነበር።

ለነገሩ አእቲቪስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ታማኝ በየነ በየትኛውም መስፈርት የድል አጥቢያ ጥያቄ አቅራቢ አይደለም፣ ምናልባት ጃዋርን ቀደም ሲል በቀጥታ አይጠይቀው እንጂ መላው ኢትዮጵያዊያን በያዙት የፖለቲካ መስመር ለሁሉም ብሔሮች እኩልነት እንዲታገሉ ጥያቄ ማቅረብ የጀመረው ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ነው። ታማኝ በየነ እኮ የሕወአት ሠራዊት አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ማግስት ከውጪ ሀገር ሆኖ ሳይሆን እዚያው እሳቱ መካከል ቆሞ ያለ ፍርሃት በድፍረት ማንም አጋር አጠገቡ ሳይቆምለት በብቻኝነት የወያኔን አጀንዳ ፊት ለፊት የተቃወመ ጀግና ነው። ታማኝ በሚገርም ሁኔታ ለውጪ ሀገር ሚዲያዎች ሀገሪቱ “Under the gun” እንደሆነች ጥርት ባለ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ገና ከማለዳው ያሳወቀ ምርጥ የኢትዮጵያ ልጅ ነው። የታማኝ በየነ ገራሚው የስታዲየም ንግግሩስ እንደምን ይረሳል? አሁንም እደግማለሁ…እዚያው እሳቱ መኻል ቆሞ!!!!!! ታማኝ የ”አብረን እንታገል” ጥሪን በማቅራብ ያን ያህል የሚታማ አልነበረም።

2. በሁለተኛ ደረጃ ይህን የጃዋርን ምላሽ ተከትሎ አንዳንድ የማከብራቸውም የፌስ ቡክ ወዳጆቼንም ጨምሮ በታማኝ በየነ ላይ ለመሳለቅ ያደረጉት እሽቅድምድም አስደንግጦኛል። አንዳንዶቹም ከታማኝም አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ በስነ ጥበቡም ዓለም ሰፊ ዕውቅና ያለውን የኮሜዲ ሙያን አሳንሰው ለማሳየት ሞክረዋል፤ ለታማኝ “ኮሜዲያን” የሚለውን ቅፅል መስጠትን እንደ ውርደት የቆጠሩም አልጠፉም…በዚህ ሂደት ግን የተዋረዱት እነርሱ እንጂ ታማኝ አይደለም። Such immature reflection is a kind of self suicidal… Intellecual self suicidal! ከነርሱ ስላቅ ይልቅ የአቶ ጃዋር መሐመድ ምላሽ መቶ እጥፍ ይሻለኛል።

(ጌታሁን ሄራሞ)

Share.

About Author

Leave A Reply