Thursday, January 17

“እዮሃ መስከረም ሁለት” (የኔ ና የኔ ባቾች የመስከረም ሁለት ቀን ማስታወሻ ) መላኩ ብርሃኑ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ገና ጎህ ከመቅደዱ ቤት ለቤት እየዞርን በፉጨትም በድምጽም እንጠራራለን። መላ ! አሼ! ቡችላ ! ያይራድ! አሌክስ! ጭራሞ! ጢሊንጥ! ባምባ! ሚኬሌ! ሰዬ! ጋብሪ! ኡጁሉ! ….
ለመሰባሰብ ደቂቃዎች ይበቁናል። አንዳንዶቻችን ከመቸኮላችን ፊታችንን አንታጠብም። ቁርሱን የሚበላ ማንም የለም። ብዙዎቻችን በኪሳችን ሳንቲሞች አይጠፉም። እንቁጣጣሽ አበባ ያዞርንበት አምሳም ሰባአምስት ሳንቲምም ይኖረናል።

ይቺ ቀን ከእንቁጣጣሽ ቀጥለን የምንናፍቃት ቀናችን ናት። መስከረም ሁለት እንዲህ በቀላሉ አይነጋልንም።

የኦሎምፒያ ልጆች ነን። 18 ቶች እንባላለን። የቀበሌያችን ስም ነው። ከላይ ሰፈር ታች ሰፈር ድረስ ተጠራርተን እንደተሰባሰብን ፈጠን ፈጠን እያልን ወደእስጢፋኖስ እናዘግማለን። ቀን ልናየው የምንችወልው ትዕይንት እንገምታለን።

“ስማማ …የኛ ታንኮች እኮ ከእስራኤል ይበልጣሉ…”
“ጀቶቹስ ቢሆኑ! ደሞ እሪኮፍተር ባንዲራ ይበትናል ተብሏል”
“እየውላችሁ! ሌሊት ሚሳይል ተተኩሷል መሰለኝ ዛሬ”
“እረ ባክህ አትዋሽ…መድፍ ነው እንጂ ሚሳይል ይተኮሳል እንዴ ደሞ!”
“አየር ወለዶቹ ዛሬ ይገለባበጣሉ ተብሏል …እንዳያመልጠን”

ይህንን እያወራን …አንዳችን ከአንዳችን በላይ ለመደመጥ እየተሽቀዳደምን ቤተክርስቲያን እንደርሳለን። የእስጢፋኖስን በሮች እየተሳለምን ዙሪያውን እንዞራለን። ከዚያም ተጣድፈን እንወጣለን።

ቦታ እንዳይያዝብን እየተራኮትን ፊት ከሚገኙት የድንጋይ መቀመጫዎች ላይ በተርታ ተደርድረን እንቀመጣለን። እፎይ! …ድንጋዮቹ አልተያዙም…ከዚህ በኋላ ብዙ መቶ ሺህ ሰዎች ከኋላችን ይደረደራሉ። ገና ቦታ ጠፍቶ ብዙዎች ይበሳጫሉ። እኛ ግን አንደኛ ደርሰናል። ሳቅ በሳቅ ሆነን ፊልም ቤት ገብቶ እስኪጀምር ድረስ ባዶ ስክሪን ላይ እንደሚያፈጥ ሰው በባንዲራ እና በዘምባባ ወዳጌጠው “ወደክብር ወደትቢዩኑ” እናፈጣለን። እዚያ ላይ መንጌ ይመጣና ይናገራል። ሰላምታ ሲሰጥ ማየት እንፈልጋለን። በኋላ ሰፈር ስንመለስ እንደሱ ሰላምታ መስጠት እንለማመዳለን።

ወደበኋላ ወላጆቻችን በቀበሌ በቀበሌ ተሰልፈው መምጣታቸው አይቀርም። እኛ ቀድመናቸዋል። ስንወጣ ቤተክርስቲያን እንሂድ ብለን አስፈቅደን ነው። እንዳትጠፉ ተያያዙ ተብለን ነው የተሸኘነው።አሁን ያለነው ግን አብዮት አደባባይ ነው። ከሰዓታት በኋላ የምንናፍቀው ትዕይንት ይጀምራል።

አሁን ጸጥ ያለች የምትመስለው አብዮት አደባባይ በኋላ ቀውጢ ትሆናለች። ዝማሬ! የወታደር ሰልፍ ትዕዛዝና የኮቴ ጩኸት …የጦር መሳሪያዎች ትዕይንት …በላይ የሚያንጃብበው ሄሊኮፕተር ….በምድር የሚርመሰመሰው ሰልፈኛ የምድር ሃይል…እነሱን እያሰብን ደስ ይለናል። ብርዱ እያንቀጠቀጠን በኋላ በምትወጣው ጸሃይ እንጽናናለን። አይርበንም። በዓመት አንድ ቀን በጉጉት ጠብቀናት የምትመጣው መስከረም ሁለት ቀን ከእንቁጣጣሽ እኩል ለኛ የሰፈር ልጆች የደስታ ቀናችን ናት።

ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ሳይሞላ አብዮት አደባባይ ይሞላል። ግርግር ይሆናል። ዩኒፎርማቸውን አሳምረው የለበሱ ፖሊሶች ያስተናብራሉ። ሰፊው አስፋልት ጭር ይላል። ሰልፈኞቹ የሚያልፉት በዚያ ነው። በካርቶን ላይ የተጻፉና በአጠና የተሰቀሉ መፈክሮች እዚህም እዚያም ሰው ተሸክሟቸው ይወዛወዛሉ። መሃላቸው ለንፋስ ማሳለፊያ በተቀደዱ ጨርቆች ላይ የተጻፉ ረጃጅም መፈክሮች በሁለት ሰዎች ተወጥረው ይታያሉ።

እኛ ጊዜው እስኪደርስልን መፈክሮቹን ተሽቀዳድመን እናነባለን። “አብዮታዊት እናት ሃገር ወይም ሞት!” ….“ከጓድ መንግስቱ ሃይለማርያም አብዮታዊ አመራር ጋር ወደፊት!” …”ኢትዮጵያ ትቅደም!” … አንሳሳትም። በቃላችን ያጠናናቸው መፈክሮች ናቸው። እኛም አንረሳቸውም እነሱም በየዓመቱ አይጠፉም።

ማርክስ ሌኒን እና ኤንግልስ ጓደኛሞች መስለው ተደርድረው የተነሱት ግዙፍ ፎቶ ከኋላችን ከብደውናል። ከፊት ትሪቢዩኑ ላይ የመንጌ ፎቶ ገጭ ብሎ ሁሉንም በአርምሞ የሚመለከት መስሏል። አብዮት አደባባይ መግቢያ ላይ “ወዛደራዊ አለምአቀፋዊነት ይለምልም” የሚል የተጻፈበት ግዙፍ ሳይን ጌት ለዘመናት በቆመበት አለ። ዱርዬ የምንላቸው ልጆች እዛ ላይ ሁሉ ወጥተው ትዕይንቱን ይመለከታሉ።

የተጠራሞተ ገጽታ ያለው ጭቁን ህዝብ ፣ የየቀበሌው ሰልፈኛ የካርቶን መፈክሩን እያነበነበ ግራ እጁ እስኪገነጠል ከመፈክሩ ጋ እየወነጨፈ ይመጣና አብዮት አደባባይን ይሞላዋል። “ያለሴቶች ተሳትፎ አብዮቱ ግቡን አይመታም” የሚል መፈክር የያዙ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ጥለት ያለው ሸማ የለበሱ አኢሴማዎችም እንዲሁ እየፎከሩ ይመጣሉ። አብዮት ጠባቂዎች በብርማ ቀለም ልብሳቸው ቆመህ ጠብቀኝ ጠመንጃ ይዘው በሰልፍ ይመጡና ህዝቡን ይቀላቀላሉ። አስፓልቱ ግን ጭር እንዳለ ወታደራዊ ሰልፈኞቹን ይጠብቃል።

ጸሃይዋ መክረር ትጀምራለች። እኛም ሽንብራ ዱቤ ገዝተን መቆርጠም እንጀምራለን። ሸንኮራ አዟሪዎች አንድ አንጓ በአምስት ሳንቲም ይሸጡልናል። ውድ ነው። ግን መስከረም ሁለት ስለሆነ እኛም ሃብታም ስለሆንን ችግር የለም። ዝንብ በዝንብ ብንሆንም ደስ ይለናል። አይደክመንም አይርበንም አይጠማንም። 3 ሰዓት አካባቢ ሲሆን ስነስርዓቱ ይጀመራል።

መንጌ ወታደራዊ ዩኒፎርሙን ለብሶ ትሪቢዩኑ ላይ የሚጠብቁት እንግዶች መሃል ድንገት ከች ይላል። እልልታውና ጭብጨባው ይጦፋል። ከዚያ በኋላ አስተዋዋቂው በማይክራፎን የሚለፍፈው ነገር ያደነቁረናል።

“እዮሃ መስከረም ሁለት
አዲስ ዘመን አዲስ ልደት “ የሚለው መዝሙር ይንቆረቆርልናል። አብረን እንዘምራለን።

መንጌ በወታደራዊ ዩኒፈፎርሙ ደምቆና ኮስተር ብሎ ከዘለዓለም የረዘመ ንግግር ያደርጋል። እየተቆጣ! እየጮኸ! እየረገጠ! እየፈረከ …እኛ ግን አንሰማውም። ይሰለቸናል። እናወራለን። እንንጫጫለን። አጠገባችን ያሉ አዋቂዎች በኩርኩም ቆግተው ዝም እስኪያስብሉን ቂጣችንን ድንጋይ ላይ እየፈተግን ወሬያችንን እንቀዳለን። ጃኬት ያለው በጃኬቱ ጸሃይዋን ይከላከላል። የሌለን እንደሰም አንቀልጣለን። መንጌ ሲጨርስ ህዝቡን መፈክር ያስፈክራል። አብረን እንፈክራለን። ከዚያም ፉጨትና ሁካታ ይከተላል።

ያንን ተከትሎ ወታደራዊ ትዕይንቱ ይጀምራል። ደስ ሲል…በሰልፍ በሰልፍ አይተናቸው የማናውቃቸው መሳሪያዎች በኦራል መኪኖች ላይ ተጭነው ያልፋሉ። ላያቸው ላይ ወታደሮች ሰላምታ ሰጥተው እናያቸዋለን። አውሮፕላን የሚመሳስሉ ሚሳይሎችና ሮኬቶች እናያለን። ክንፋቸው የተቆረጡ ጀቶች እየመሰሉን መላ ምታችንን እንሰነዝራለን። አርባ ተኳሽ …አየር መቃወሚያ..መድፍ..ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች..ምኑ ቅጡ።

ከዚያም ግዙፍ ባለብረት ጎማ የሶቪየት ታንኮች ይርመሰመሳሉ። ያ አስፋልት የእርሻ መሬት መስሎ ይፈራርሳል። አካባቢው በታንክ ጭስ ይሞላል። በባዶ ሆዳችን ያ የናፍጣ ጭስ ሲሸተን ያጥወለውለናል። ቢሆንም በታላቅ ጉጉትና መደነቅ ፈዝዘን ትዕይንቱን እንከታተላለን። ከሰዎች የወዳደቀ ትናንሽ የወረቀት ባንዲራ ይዘን እናውለበልባለን። ብረት ቆብ ያጠለቁ ወታደሮች ስናይ እንደነሱ ታንክ መንዳት ያምረናል። በአጠቃላይ ወታደር መሆን ያምረናል።

የመሳሪያው ትዕይንት ሲያልቅ እግረኛው ጦር ይመጣል። አቤት ሰልፍ! አቤት ወታደራዊ አቋም ፖሊስ፣ አየር ሃይል፣ ኮማንዶ፣ ባህር ሃይል፣ ባለቀይ እና አረንጓዴ ቦኔት ለባሽ አየር ወለድና ስፓርታ ጦር …እኩል እየረገጡ እኩል እየመተሩ ሮቦት መስለው በአጠገባችን ይተማሉ።

መንጌ ጋ ሲደርሱ አዛዡ ያዝዛል።

ሻ ለ ቃ !
ቀኝ አይተህ በክብር ሰ ላ ም በል!

ፊት ያሉት መሪዎች ወደመንጌ ዞረው ሰላምታ ገጭ አድርገው ግራ ቀኝ እያሉ ይራመዳሉ። እንደውሃ ይፈስሳሉ። አይቋረጥም። ትሪቡኑን ሲያልፉ የት እንደሚሄዱ እንጃ። ለወራት ያደረጉት ልምምድ በዚያን ትሪቢዩን ፊት ሲያልፉ ታበቃለች። ሄሊኮፕተሮች ወረቀት ይበትናሉ። ወረቀቱን ለማግኘት ትርምስ ይፈጠራል። እኛ ደግሞ ነጂውን ለማየት አንገታችን አስኪሰበር እናንጋጥጣለን።

በጣም ደስ ይለናል። ቀትር እስኪሆን ያየነውን ትዕይንት ለወር ያህል እያነሳን እንጨዋወትበታለን። ወታደር መሆን ያምረናል። ተዋጊ መሆን ያምረናል። በልጅ ልባችን የአገራችን መደፈር የኛ መደፈር መሆኑ ይገባናል።

ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያ የምትባለው አንዲት እናት ሃገራችንን በጣም አንወዳታለን። ሁላችንም የአንዲት ሃገር ልጆች መሆናችንን ስለምናውቅ በሃገራችን እንኮራለን። “አንዲት እናት ሃገር ወይም ሞት!” ስንል ነው ያደግነው።

በጊዜው ብሄር ምን እንደሆነ አናውቅም። ፖለቲካም አናውቅም። የምናውቀው ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ነበር። አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራችንን ብቻ ነው ! በጋራ ሆነን ስለአገራችን ብቻ የሚወራበት ቦታ መሄዳችንን ነው። የምናውቀው መስከረም ሁለት የሁላችን መሰባሰቢያ መሆኑን ብቻ ነው። ልጆች ነን።

ባንዲራችን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ
አርማችን ነው መመኪያችን
ለኢትዮፐያ ሃገራችን
ባንዲራችን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ!

ይህ ነበር መዝሙራችን። ልጅነት ስንቱን አሳየን። ሁሉም አለፈ!

Share.

About Author

Leave A Reply