ኦህዴድ ሆይ፤ ህዝብ የተስማማበት ህገ መንግስት ስጠንና እንኳን አዲስ አበባን ኢትዮጵያን እንስጥህ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል እንዲሉ ከዚህ ቀደም ከጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞች በየሶሻል ሚዲያ ስንሰማው የሚኮሰኩሰንን ነገር ተስፋ የጣልንበት የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) በድንገት ተቀብሎ ጽኑ አቋሙ አድርጎ ይዞ መጥቶ ብዙዎቻችንን አስደንግጧል።

እርግጥ በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ የሀሳብ ልዩነቶች እምብዛም የሚንጸባረቁ በመሆኑና ኦፒዲ የተለየ ሆኖ ሳይሆን ከህወሀት መሸሽ በኋላ ኢትዮጵያን ዳግም ወደ ነበረ አንድነቷና ከብሄር የፖለቲካ ጣጣ ሊያወጣን ይችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት “የቲም ለማ” ትርክት በኦፒዲኦ ውስጥ በጽኑ መንጸባረቁ ነው። “ሁላችንም ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን” የሚለው የፓርቲው ሊቀመንበር ልብ ገቢ ንግግርና የክልሉ ፕሬዚዳንት “ኢትዮጵያ ሱስ ነች” የሚሉትን አስደማሚ ንግግሮች ተከትሎ መላው ኢትዮጵያዊ፣ ሀገር ውስጥ ቢኖራ ወይ ዲያስፖራ፣ ሴት ከወንድ፣ ብሄር ከብሄር ሳይለይ በአንድ ልብ ተቀብሎ አስተናግዷቸዋል።

ይሁንና ይህን አለም ሁሉ ያደነቀውን የኢትዮጵያውያንን ስሜት ይሄው ድርጂትና እነዚሁ መሪዎች በድንገት ቀዝቃዛ ውሀ ቸልሰውበት ዳግም ሊገኝ የማይችለውን ብርቅዬ የፖለቲካ ቅቡልነት በገዛ እጃቸው አጥፍተውታል። ከኢትዮጵያ የኛ የሁላችን ናት አሰባሳቢ ትርክት ወደ “ፊንፊኔን ኬኛ” ግትር መግለጫ ሲወርዱ ለአፍታም ያህል “ትናንት ምን ብለን ነበር? ይሄ ህዝብስ ምን ይለናል?” ብለው አላሰቡም።

“ኦፒዲኦ ለአዲስ አበባ እንዲህ የቋመጠው ነገ ምን ሊያደርግ፣ ምንስ ሊያደርገን ነው?” የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ሊያስነሳ እንደሚችል ውልብ እንኳ አላላቸውም።
ይህም የኦሮሞ ህዝብ ቁጥር መብዛት የትኛውንም አይነት ተቃውሞና ትግል የማንበርከክ አቅም አለኝ ወደሚል እቡይ አስተሳሰብ እንዳወረዳቸውና በተለይም “ዴሞክራሲያዊ ፍልስፍና፣ የሰለጠነ የመነጋገርና የመወያየት መንግስት” የመመስረት እቅድ እንዴሌለ አመላካች ሆኗል። ኦፒዲኦ አዲስ አበባን ለኦሮሞ የማድረግ ቁርጠኛ አቋም ካለው ሊጀምር የሚገባው በሶስት ገጽ መግለጫ አይደለም። በመግለጫ የተገኘ እንዲህ ያለ ድል የለም።

ሊቀድም የሚገባው በመጀመሪያ አዲስ አበባን ፊንፊኔ ለማድረግና ፊንፊኔንም የኦሮሞ ለማድረግ የሚያስችል ህዝባዊ ቅቡልነት ያለው ህግና ህገ መንግስት አለን ወይ? የሚለው ነው። እርግጥ ነው ኦፒዲኦ አሁን በስራ ላይ ያለውን ህገ መንግስት እንደ ማጣቀሻ ሊያቀርብ ይችል ይሆናል። ግን ይህ ህገ መንግስት እሱና ጀሌዎቹ ብቻ ጽፈው ያጸደቁት እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ያመነበት እንዳልሆነ የአደባባይ ሀቅ ነው።

በመሆኑም ኦፒዲኦም ሆነ ሌሎች መሰረታዊ የሀገር ጉዳይ ላይ ወደ ውሳኔ ከመሄዳችሁ በፊት መጀመሪያ የምንስማማበትን ህግና ህገ መንግስት እንዲኖረን አድርጉ። ህዝብ ይወያይ፣ ይከራከር፣ ይስማማ፣ ህገ መንግስት ይኑረን።

ሀገ መንግስት ብትሰጡን አዲስ አበባን ሳይሆን ኢትዮጵያንም ጨምራችሁ ውሰዱ!
ቃሊቲ ፕሬስ

Share.

About Author

Leave A Reply