‹‹ኦብነግ የታገለው የሶማሌ ህዝብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ነው›› አቶ አብዱልራህማን መሀዲ – የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ዋና ጸሃፊ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

አቶ አብዱልራህማን መሀዲ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) መስራችና ዋና ጸሃፊ ናቸው፡፡ የተወለዱት በሶማሌ ክልል ቀብሪደሃር ሲሆን፤ ሶማሊያ ሞቃዲሾ ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ማስተርስ ዲግሪ በማኔጅመንትና ቢዝነስ አድሚንስትሬሽን አግኝተዋል፡፡ በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲም ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ኦብነግ ከአመሰራረቱ አሁን እስካለበት ደረጃ ያሳለፈውን ሂደት በተመለከተ ከአዲስ ዘመን ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር መቼና የት በእነማን ተመሰረተ?

አቶ አብዱልራህማን፡- ኦብነግ የተመሰረተው እኤአ በ1984 ነው፡፡ ላለፉት 34 ዓመታት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ የተመሰረተው ኦጋዴን ውስጥ ነው፡፡ መስራቾቹ ስድስት ናቸው፡፡ እኔ አንዱ ነኝ፡፡ ሶስቱ በህይወት የሉም፡፡ አንደኛው አሁን ብዙ ተሳትፎ አያደርግም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስማቸውን መጥቀስ ይችላሉ ?

አቶ አብዱልራህማን፡- አብዱልራህማን መሀዲ፣ ሼክ ኢብራሂም አብደላ፣ መሀመድ ኢስማኤል፣ አብዱላሂም መሳዲ፣ አብዱራህማን ዩሱፍ መገንና አብዲ ጌሌ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የተለያዩ ቢሮዎች በሀገር ውስጥና በውጭ አላችሁ?

አቶ አብዱልራህማን፡- በአጠቃላይ በዓለም ላይ ከ60 በላይ ቢሮዎች አሉን፡፡ በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአፍሪካ ውስጥም፡፡ ቀደም ብሎ አዲስ አበባ ውስጥ ሕዋስ ነበረን፡፡ ድርጅታችን በጣም ሰፊ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ምን ያህል ቢሮ አላችሁ ?

አቶ አብዱልራህማን፡– ሶማሌዎች ባሉበት አካባቢ ሁሉ ቢሮዎች አሉን፡፡ ከሞያሌ እስከ አዲስ አበባ፡፡

አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶቹን ሊጠቅሱልን ይችላሉ?

አቶ አብዱልራህማን፡– አዲስ አበባ ቢሮ ከፍተናል፡፡ ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋ፣ ቀብሪደሀር፣ ደገሀቡር፣ ዋርዴር፣ ሽላቦ፣ ጎዴ፣ ቀላፎ፣ ፊቅ፣ አፍዴር፣ ለገሂዳ እና በሌሎችም አካባቢዎች፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ድሬዳዋ ላይ ቢሮ መክፈታችሁንና በከተማው ለድርጅቱ የድጋፍ ሰልፍ መካሄዱን ተከትሎ እንቅስቃሴው በድሬዳዋ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ለማንሳት ያለመ ነው የሚሉ አካላት አሉ፡፡ በድሬዳዋ ላይ የይገባኛል ጥያቄ አላችሁ?

አቶ አብዱልራህማን፡– ድሬዳዋ አማራውም ኦሮሞውም ሶማሌውም ሁሉም በጋራ የሚኖሩበት ከተማ ናት፡፡ በርካታ ባህሎችም አንድ ላይ ይገኙባታል፡፡ ሕብረ ብሄራዊ ባሕልንም ያቀፈች፤ ሁሉም በሰላም የሚኖርባት ከተማ ነች፡፡ ጥያቄው ይሄ ነው ይሄ ነው የሚለው ምንም ጠቀሜታ የለውም፡፡ ክፍፍሉ አይጠቅምም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሰላም ጥሪው ተደራድራችሁ እስከገባችሁ ድረስ ኦብነግ የራሱ ተዋጊ ሠራዊት ነበረው?

አቶ አብዱልራህማን፡- በኢትዮጵያ ለውጥ በመጣበት እአአ በ1991 በሽግግር መንግስቱ ዘመን የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ከኢሕአዴግ ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ በአዲስ መልክ የተቋቋመ ድርጅት ሆኖ የመጀመሪያውን የኦጋዴን መንግስት አቋቁመን ነበር፡፡ እአአ በ1992 ወደ ምርጫ ገባን፡፡ 87 በመቶ የሚሆነውን ድምጽ አሸነፍን፡፡ በዚህ ምክንያት የመጀመሪያውን የሶማሌ ክልላዊ መንግስት መሰረትን፡፡ በዚህም በሁለት ዓመታት በነበረው ሂደት ሕወሓት ደስተኛ አልነበረም፡፡ የእኛን አካሄድ አልወደዱትም፡፡ እነርሱ የሚፈልጉት የራሳቸው አሻንጉሊት የሆነ (ሳተላይት) መንግስት መመስረት ነበር፡፡ ጥቃት ሰነዘሩብን፡፡ አገዱን፡፡ ከዛ በኋላ የራሳችንን ነጻ አውጪ ሰራዊት መስርተን ላለፉት 27 አመታት ስንዋጋ ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በተለያየ ጊዜ ውጊያ አድርጋችኋል፤ ምን ያህል ጊዜ ነው የተዋጋችሁት ?

አቶ አብዱልራህማን፡– 27 አመቱን ሙሉ ውጊያ ላይ ነበርን፡፡ መቁጠር አይቻልም፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባርን ስታቋቁሙ ዋነኛው ግባችሁ ምንድን ነበር?

አቶ አብዱልራህማን፡– በእኛ አካባቢ የተለያዩ ነጻ አውጪ ግንባሮች እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር፡፡ የወጣቶች ንቅናቄም በስፋት ይታይ ነበር፡፡ እኛ ነጻ የሆነ ሕዝቡን የሚጠብቅ ድርጅት የሚያስፈልግ መሆኑን አምነን ወሰንን፡፡ የአካባቢው ተወላጆች ስለሆንን ለሕዝቡ ፍላጎት የሚዋጋ አዲስ ድርጅት ፈጠርን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኦብነግ በድረ ገጹ ባሰፈረው ‹‹ፖለቲካል ኦብጀክቲቭ›› በሚለው ሀተታው ኦጋዴን በመልክአ ምድራዊም ሆነ በፖለቲካዊ አስተዳደር የኢትዮጵያ አካል ሆና አታውቅም ይላል፤ ድርጅታችሁ ኦጋዴን የኢትዮጵያ አካል አይደለችም ብሎ ነው የሚያምነው ?

አቶ አብዱልራህማን፡- ኦጋዴን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ክልልዊ መንግስት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕገመንግስት ሕዝቡ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብት ተቀባይነት አለው፡፡ እኛ ግን የህዝቡ መብት እስከተከበረ ድረስ በዚሁ እንቀጥላለን ነው የምንለው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ድርጅቱ በፕሮግራሙ ኦጋዴን በኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት መያዝዋን ይገልጻል፡፡ ይህም ቀደም ባለው ጊዜ ታላቋን ሶማሊያ ለመመስረት በሶማሊያ መንግስት የሚቀነቀነውን ሃሳብ ደጋፊ መሆኑን ያሳያል ብለው አስተያየት የሚሰጡ አካላት አሉ፤ ይህን ጉዳይ እንዴት ያዩታል ?

አቶ አብዱልራህማን፡- እነዚህ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ናቸው፡፡ መቼም ቢሆን ታላቋን ሶማሊያ እናቋቁማለን አላልንም፡፡ ኦብነግ የታገለው የሶማሌ ህዝብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ነው፡፡ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በኢትዮጵያ ሕገመንግስት ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ ይሄንን ስራ ላይ ማዋል እንፈልጋለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- የድርጅታችሁ አርማ ከሶማሊያ ሰንደቅ አላማ ጋር በሚጠቀመው ባለአምስት ጫፍ ኮከብ ይመሳሰላል፡፡ ሶማሊያ የኮከቦቹ አምስት ጫፎች ሶማሊያውያን ያሉበትን የምስራቅ አፍሪካ አምስት ስፍራ ይወክላል ትላለች፡፡ በቀድሞ ህገ መንግስቷም እነዚህን አካባቢዎች በመጠቅለል ታላቋን ሶማሊያ የመመስረት እቅድ አስቀምጣ ስትንቀሳቀስ ነበር፡፡ እነዚህን ነገሮች በማገጣጠም ከሶማሊያ ጋር ትስስር አላችሁ ይባላልና በዚህ ላይ ምን ይላሉ ?

አቶ አብዱልራህማን፡- ይህ በኦብነግ ህገ ደንብ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ አምስቱ የኮከቦቹ ጫፎች የቆሙት የሶማሌ ህዝብን አንድነት ለማሳየት ነው፡፡ በኦጋዴን የሚገኘውን የሶማሌ ሕዝብ የሚያሳይ ሲሆን፤ እንደ ሶማሌ አንድነቱና መለያው ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኦብነግ ይፋዊ ድረ ገጽም ኦጋዴንን ነጻ ማውጣት በሚል የተቀመጠ ሃሳብ አለ፤ ምን ማለት ነው ታዲያ ?

አቶ አብዱልራህማን፡– ነጻ መውጣት ማለት ብዙ ትርጉም አለው፡፡ ነጻነት ማለት ትገነጠላለህ ማለት አይደለም፡፡ ከጭቆና ነጻ ልትወጣ ትችላለህ፤ ከረሀብና ከፍርሀት ነጻ መሆንንም ያካትታል፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት በኦጋዴን ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸምበት ነበር፡፡ እንደ ሰው የህዝብን መብት ማክበር ካልቻልክ ሴቶችን ከደፈርክ ከገደልካቸው ካጠፋሀቸው ለምንድነው የሀገሪቱ አካል የምንሆነው ? አብረን እምንኖር ከሆነ እርስ በእርስ ተከባብረን ለመኖር ችግር የለውም፡፡ ጭቆና ካለ ግን አይሆንም፡፡

ኦብነግ በጣም ግልጽ አቋም ነው ያለው፡፡ እኛ የምንታገለው የተከራከርነው የሶማሌ ሕዝብ እራሱን በእራሱ እንዲያስተዳድር ነው፡፡ ሕዝቡ ነው የሚፈልገውን የሚወስነው፡፡ የአንተ ወይንም የኦብነግ መብት አይደለም ተገንጠል ወይም ተቀላቀል የሚለው፡፡ የእኛ ስራ ህዝባችን የፈለገውን የመመረጥ መብቱ መረጋገጡን ማየት ነው፡፡ ስለዚህም የሶማሌ ህዝብ መብት መረጋገጡን በጸደቁት ዓለም አቀፍ ህጎችም መሰረት ማረጋገጥ ነው አላማችን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢብራሂም አብደላ ማናቸው ?

አቶ አብዱልራህማን፡- የቀድሞው የኦብነግ ሊቀመንበር ናቸው፤ በህይወት የሉም፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርሳቸው በአንድ ወቅት ‹‹የኦብነግ አላማ ኦጋዴንን ከኢትዮጵያ ቅኝ ግዛትነት ነጻ ማውጣትና ከአረብ ሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ማጎልበት ነው›› የሚል ሃሳብ በአፍሪካ ቀንድ መጽሔት የመጀመሪያው ዓመት ቁጥር 7-1985 ማንጸባረቃቸው ይታወቃል፤ ይሄን እንዴት ይመለከቱታል ?

አቶ አብዱልራህማን፡- ይህ በኦብነግ ላይ የተከፈተው ፕሮፓጋንዳ አካል ነው፡፡ ኦብነግ ሶማሌያዊ ድርጅት ነው፡፡ አፍሪካዊ ድርጅት ነው፡፡ በአፍሪካ ነው የምንኖረው አፍሪካውያን ነን፡፡ ግለሰቡ የራሱን ሀሳብ ሊገልጽ ይችላል፡፡ ኦብነግ ግን ግልጽ የሆነ አቋም ነው ያለው፡፡ አዎ ከአረቦች ጋር ግንኙነት አለን፡፡ ምክንያቱም እኛ ሙስሊሞች ነን፡፡ ኢትዮጵያም ከአረቦች ጋር ግንኙነት አላት፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኦብነግ የወቅቱ ሊቀመንበር የሆኑት አድሚራል መሀመድ ኡመር ኡስማን ወታደራዊ ማእረጋቸውን ያገኙት ከየት ነው ?

አቶ አብዱልራህማን፡- የሶማሊያ ባሕር ኃይል አዛዥ ነበሩ፡፡ ማእረጋቸውን ያገኙት ከሶማሊያ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እርሳቸው ‹‹እኛና አልሸባብ የጋራ ጠላት አለን›› ሲሉ መናገራቸውን በአንድ የጥናት ጽሁፍ ተጠቅሷል፤ ይሄን እንዴት ያዩታል ?

አቶ አብዱልራህማን፡- ይህ ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው፡፡ ሊቀመንበሩ በፍጹም አልሸባብና ኦብነግ የጋራ ጠላት አላቸው አላሉም፡፡ ስም ማጥፋትና በኦብነግ ላይ የሚደረግ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ አልሸባብ የእኛን በርካታ አባላት ገድሏል፡፡ ይሄ በቀድሞው ሥርዓት ሲነዛ የነበረው ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ምክንያቱም ድጋፍ ለማግኘት ይጠቀሙበታል፡፡ ኦብነግ ብሄራዊ ድርጅት ነው፡፡ በኦጋዴን ለሚኖሩት የሶማሌ ሕዝቦች የሚታገል ነው፡፡ በሶማሊያ ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር ምንም የምናደርገው ነገር የለም፡፡ ስለሶማሊያም ምንም አይነት ፍላጎት የለንም፡፡ ይሄ ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አልሻባብና አልቃይዳ በአሸባሪነት የተመዘገቡ ድርጅቶች ናቸው፡፡ አንዳንዶች ኦብነግ ከነዚህ ቡድኖች ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለው ይላሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው ?

አቶ አብዱልራህማን፡– እ.አ.አ ከ2007 እስከ 2018 የካቲት እኔ በአሜሪካን ኮንግረስ ቀርቤአለሁ፡፡ አሜሪካ ውስጥ ቢሮ አለን፡፡ በአውሮፓም ቢሮ አለን፡፡ የአሜሪካ መንግስት ደህንነት እኛ ከአልሸባብና ከአልቃይዳ ግንኙነት ቢኖረን ዝም ብሎ ያሳልፋል ብለህ ታስባለህ? ኦብነግ ከአልሸባብ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም፡፡ ብሄራዊ ድርጅት ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ድርጅት አይደለም፡፡ ሙስሊሞች ነን፡፡ ለህዝብ ነው የምንታገለው፡፡ ደጋግሜ እንደነገርኩህ ሰዎች ውንጀላና ስም ማጥፋት ላይ ነው የሚሄዱት፡፡ በእዚህ መንገድ ብቻ ነው የሚዋጉን፡፡ ከሶስት ዓመታት በፊት ሶስት የማእከላዊ ኮሚቴ አባሎቻችን በአልሻባብ ተገድለዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኦጋዴንና በሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለተፈጸሙ ጥቃቶችና የቦምብ ፍንዳታዎች ኦብነግ ተጠያቂ መሆኑ ይገለጻል፡፡ ይሄንስ እንዴት ያዩታል ?

አቶ አብዱልራህማን፡- አሁንም የእኛ አቋም በጣም ግልጽ ነው፡፡ በፍጹም ሲቪሎችን ኢላማ አድርገን አናውቅም፡፡ ለምሳሌ በኦጋዴን ሶማሌዎችና ከሌሎች ክልሎች የመጡ ብዙ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም መብታቸውን እናከብራለን፡፡ ሌሎች ብሄሮች እኩል መብት አላቸው፡፡ ይሄ ከፖሊሲያችን የሚጻረር ነው፡፡ በምንም መንገድ ሲቪሎችን ኢላማ አናደርግም፡፡

አዲስ ዘመን፡- እ.አ.አ በ2007 እኤአ በኦጋዴን ነዳጅ ፍለጋ ስራ ላይ በነበሩ ቻይናውያንና ኢትዮጵያውያን ላይ በተሰነዘረ ጥቃት በርካቶች ሞተዋል፡፡ ኦብነግ እንደፈጸመውም በወቅቱ ተጠቅሷል፤ ትክክል ነው?

አቶ አብዱልራህማን፡– በ2007 ህወሓት መራሹ መንግስት በዚህ በጣም እጅግ ጠቃሚ በሆነው የኦጋዴን የግጦሽ መሬታችንና የእንስሳ ሀብታችን ባለበት አካባቢ ሕዝባችንን መግደል ሴቶችን መድፈር ጀመረ፡፡ ወታደራዊ ጦር ሰፈር አቋቋመ፡፡ ቻይናዎቹ የነዳጅ ቁፋሮ በሚያደርጉበት ወቅት ሕዝቡ ቅሬታ ያሰማ ነበር፡፡ አንድ የኢትዮጵያ ብርጌድ ሰራዊት ነበር በኦቦሌ አካባቢ የሰፈረው፡፡ በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ ሰራዊትና በኦብነግ መካከል ውጊያ ነበር፡፡ በግጭቱ መካከል የሲቪል ድርጅት ካለ ግጭት ሲፈጠር ምንድነው የሚሆነው በሁለቱም ወገን ጉዳት ይደርሳል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለደረሰው ጉዳት ማነው ኃላፊነቱን የሚወስደው ?

አቶ አብዱልራህማን፡- በጦርነት ወቅት ሁልጊዜም ጉዳት ይደርሳል፡፡ ብዙ ሲቪሎች ከአውሮፓ፤ ከአሜሪካ፤ ከቻይና በመንገድ ላይ የሚሰሩ አሉ፡፡ አጥቅተናቸው አናውቅም፡፡ ቻይናዎቹን ግን ማን እንደገደላቸው አናውቅም፡፡ ውጊያው ግን በሁለቱም ሰራዊት መካከል ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ በኦብነግ ድረ-ገጽ ላይ በቻይናዎቹ ላይ ለተሰነዘረው ጥቃት ኃላፊነቱን እንወስዳለን ብላችሁ አሳውቃችሁ ነበር፡፡

አቶ አብዱልራህማን፡- እኛ ኃላፊነት የወሰድነው በአካባቢው ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር ውጊያ ያደረግን መሆናችንን ነው፡፡ ቻይናዎቹን የገደልነው እኛ ነን ብለን ኃላፊነት አልወሰድንም፡፡ ስምንት ያህሉን ማርከናቸው ነበር፡፡ ውጊያው እንዳለቀ ለቀይ መስቀል አስረክበናቸዋል፡፡ በስፍራው የሁለቱ ሰራዊቶች ግጭት ነበር፡፡ በሁለቱም ወገን ጉዳት ደርሷል፡፡ በግጭት ወቅት ሲቪሎች የበለጠ ችግር ላይ ይወድቃሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሙሉ ነጻነት ካልተገኘ በአካባቢው የሚገኘውን ነዳጅ ማንም መጠቀም አይችልም የሚል አቋም ታንጸባርቃላችሁ ይባላል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ቢያስረዱን ?

አቶ አብዱልራህማን፡- ይሄን በተመለከተ የድርጅታችን አቋም ግልጽ ነው፡፡ እኛ ያልነው እያንዳንዱ ክልል የየራሱ የተፈጥሮ ሀብት አለው፡፡ በአካባቢው የሚኖረው ሕዝብ በእነዚህ ሀብቶች ላይ መብት አለው፡፡ በጋራ ልንካፈል እንችላለን፡፡ ይሄ ድርድር ያስፈልገዋል፡፡ አንዳንድ ኩባንያዎች አሉ፡፡ የሕዝቡን የአኗኗር ዘይቤ ያጠፋሉ፡፡ ጥፋት ያደርሳሉ፡፡ ባህላዊ የግጦሽ ቦታዎቻችንን ያጠፋሉ፤ እጽዋትን ይቆርጣሉ፡፡ ሕዝባችንን ይገፋሉ፡፡ ይሄን የማድረግ መብት የላቸውም፡፡

የተፈጥሮ ሀብቶች በሚመዘበሩበት ወቅት ይሄን የሚመለከት ዓለም አቀፍ ሕግ አለ፡፡ ሕዝባችን መብት አለው፡፡ ይህ የተፈጥሮ ሀብት የሚወጣ ከሆነ የግድ በክልላዊ መንግስቱና በፌዴራል መንግስቱ መካከል ድርድር መኖር አለበት፡፡ እኩል ድርሻ መኖር አለበት፡፡ ሕዝባችን የተፈጥሮ ሀብቱ መብት አለው፡፡ ይሄ የኦጋዴን ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የአማራ፣ የኦሮሞ የሁሉም ክልሎች ጉዳይ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሀብትን በተመለከተ የአካባቢው ሕዝብ ተገቢ ድርሻ ሊኖረው ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደርን እንዴት ይመለከቱታል ?

አቶ አብዱልራህማን፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የፖለቲካ ምህዳሩን ከፍቶታል፡፡ አቋሙ እጅግ በጣም ቀና ነው፡፡ ለዚህም ነው አርበኞች ግንቦት ሰባትን፣ ኦነግን፣ ኦብነግን ሌሎችንም የተለያዩ ነጻ አውጪ ግንባሮችን እንዲገቡ ያደረገው፡፡ በጣም አዎንታዊ ነው፡፡ እጅግ በጣም እናደንቀዋለን፡፡ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ የበለጠ ብዙ መሰራት አለበት ብለን እናምናለን፡፡ አሁንም ተቋማት የሚጨቆኑ ከሆነ፤ የፖለቲካ ምህዳሩ በደንብ ካልሰፋ አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙ ጨቋኝ ሕጎች አሉ፤ እነዚህን መለወጥ ይገባል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብና እያንዳንዳችንም እውነተኛ ዴሞክራሲን ለማምጣት ብዙ መስራት አለብን፡፡ ለውጥ ያመጡ እርምጃዎች መውሰዳቸውን እናምናለን፡፡ ይሄንን እንዲቀጥልበት እናበረታታለን፡፡

አዲስ ዘመን፡-እ.አ.አ ነሀሴ 12 ቀን 2018 የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጋችሁን አውጃችኋል፤ ምክንያቱ ምንድን ነው?

አቶ አብዱልራህማን፡– ቀደም ሲል እንደነገርኩህ የሶማሌን ክልል የሚያስተዳድር መንግስት ሆነን ነበር፡፡ ህወሓት ጥቃት አደረሰብን፡፡ ራሳችንን በመከላከል ላይ ነበርን፡፡ አሁን የኢትዮጵያ መንግስት ያንን ጦርነት አቁሟል፡፡ ለምን ብለን እንዋጋለን? እየተዋጋን ሳይሆን እራሳችንን በመከላከል ላይ ነበርን፡፡ አሁን የፖለቲካ ምህዳሩ ተከፍቷል፡፡ እኛም መብታችንን በሰላም እንጠቀማለን፡፡ ለምን ሰው መግደል ያስፈልጋል? ለዚህ ነው ተኩስ ማቆም ያደረግነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁን ሰራዊት አላችሁ ?

አቶ አብዱልራህማን፡- አዎን፡፡ ሠራዊታችን በክልሉ የጸጥታ ኃይል መዋቅር ውስጥ ይካተታል፡፡ ከዚህ በኋላ በኦጋዴን ምንም አይነት ውጊያ አይኖርም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ ወቅቶች በኢትዮጵያ መንግስትና በኦብነግ መካከል ድርድሮች ነበሩ፡፡ ግን ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም፤ ለምንድን ነው ያልተሳካው ?

አቶ አብዱልራህማን፡- እኛ የምንደራደረው ለራሳችን አይደለም፡፡ እኛ የምንደራደረው ለዴሞክራሲ ነው፡፡ የቀድሞው አስተዳደር ፖለቲካ ምሕዳሩን ለመክፈት ዝግጁ አልነበረም፡፡ የሚፈልገው ምርኮ ነበር፡፡ መጥተን መሳሪያችንን እንድናስገባና እንደ እንስሳ እንደፈለገ እንዲገዛን ነበር የሚፈልገው፡፡ አሁን ግን የፖለቲካ ምሕዳሩ ተከፍቷል ብለን እናምናለን፡፡ ዴሞክራሲ ካለ ጦርነትና ውጊያ ውስጥ አንገባም፡፡ ሁሉም ሕዘብ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ፖለቲካ መብቱን አግኝቷል፡፡ ከአብይ በፊት የነበረው አስተዳደር የፖለቲካ ምህዳሩን ለመክፈት ፈቃደኛ አልነበረም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አስተዳደርም ቢሆን ዘግይታችሁ ነው ስምምነት ላይ የደረሳችሁት?

አቶ አብዱልራህማን፡– እኛ አይደለንም የዘገየነው፡፡ መዘግየቱ የመጣው ከኢትዮጵያ መንግስት ነው፡፡ ዝግጁ ነበርን፡፡ እየጠበቅናቸው ነበር፡፡ እገዳው መነሳቱ ከታወጀበት የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነበርን፡፡ በእኛ በኩል ለዚህ ስምምነት ደጋፊና ንቁ ተሳታፊ ነበርን፡፡

አዲስ ዘመን፡- የስምምነታችሁ መሰረታዊ ነጥቦች ምንድን ናቸው ?

አቶ አብዱልራህማን፡– የስምምነቱ ይዘት በጣም ግልጽ ነው፡፡ አንደኛው ፖለቲካ ግቦቻችንን በሰላም ማራመድ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የራሱን ሕገ መንግስት እንዲያከብር፤ የሕዝባችን መብት እንዳይጣስ፤ የተፈጠሩ ችግሮችም እንዲፈቱ የሚያጠኑ ኮሚቴዎች ተመስርተዋል፡፡ በተረፈ ሁሉንም ነገር በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ ተስማምተናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ወቅቶች የተናጠል ድርድር በሕወሓትና በኦብነግ መካከል ተደርጎ ነበር የሚሉ መረጃዎች አሉ፡፡ ይሄን እንዴት ያዩታል ?

አቶ አብዱልራህማን፡– አይደለም፡፡ ምንም አይነት የተናጠል ድርድር ከሕወሓት ጋር አድርገን አናውቅም፡፡ አልነበረንም፡፡ በኬንያ የተደራደርነው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ነው፡፡ የትግራይ ጀነራሎች በቦታው ነበሩ፡፡ እነርሱ ብቻ አይደሉም፡፡ መከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈጌሳ ነበሩ ድርድሩን ይመሩ የነበሩት፡፡

አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ወደስልጣን ከመጡ በኋላም በድረገጻችሁ ላይ ድርድር ለማድረግ ኢሕአዴግ እምነት የሚጣልበት ድርጅት አይደለም፡፡ መለወጡን የሚያሣዩ ተግባራዊ እርምጃዎች ወስዶ ማየት እንፈልጋልን ብላችሁ ነበር፡፡ ተግባራዊ ለውጥ ተመልክታችኋል ?

አቶ አብዱልራህማን፡– ዶክተር ዐቢይ እጅግ ብዙ ተግባራዊ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ጋዜጠኞችንና ተቃዋሚውን ሁሉንም ይጨቁን የነበረውን የጸረ አሸባሪ ሕግ እንዲሻሻል እያደረገ ነው፡፡ ይሄ በጣም ቀና እርምጃ ነው፡፡ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁትን አርበኞች ግንቦት ሰባት ኦብነግና ኦነግ ሌሎችንም ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል፡፡ በጣም ጥሩ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ አሁንም ገና ብዙ ርቀት መሄድ ይቀረዋል፡፡ በጣም ጨቋኝ የሆኑ ሕጎችን መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ ሕጎችን የማስተካከሉ ሂደት እንደሚቀጥል እናምናለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሶማሊያ ሕዝብ የሚበጅ ምን መፍትሄ አለን ነው የምትሉት ? በእጃችሁ ላይ የያዛችሁት አማራጭ ምንድነው ?

አቶ አብዱልራህማን፡– እንደምታውቀው አሁን የሶማሌ ሕዝብ የራሱ ክልልዊ መንግስት አለው፡፡ አሁንም የሶማሌ ሕዝብ የተገለለ ነው የሚል ስሜት አለን፡፡ በሕገመንግስቱ ውስጥ ከተቀመጠው ከ10 በመቶ በላይ መብቱን አላገኘም፡፡ የሶማሌ ሕዝብ የሚገባውን ሁሉንም መብት እንዲያገኝ እንፈልጋለን፡፡ የሶማሌ ሕዝብ ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሁሉም ብሄሮች በሰላም አብሮ ለመኖር አንዳቸው አንዳቸውን ማክበር አለባቸው፡፡

ሁሉም በኢትዮጵያ ያሉ ተቋማት ለሁሉም ሕዝብ እኩል መሆን አለባቸው፡፡ ፓርቲዎች በመንግስት ውስጥ የተለየና ተጨማሪ ስልጣን ሊኖራቸው አይገባም፡፡ አንዳችን አንዳችንን መረዳት አለብን፡፡ ሌላው እየተጨቆነ አንድ ወገን ብቻ ዴሞክራሲ ሊኖረው አይችልም፡፡ ሁሉም ሕዝብ፣ ሠራዊቱ፣ መንግስት፣ ተቃዋሚ ፓርቲው ሁሉም እኩል መብት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ እኛ የምናምንበት እነዚህ መብቶች እስካልተከበሩ ድረስ ሀገሪቱ ሁልግዜም ችግር ውስጥ ነው የምትሆነው፡፡ ሌላው ነገር ማንም ብሄር ከማንም በላይ አይደለም፡፡ ሁሉም ብሄሮች በኢትዮጵያ በህጉ መሰረት እኩል መብት ሊኖራቸውና ሊከበርላቸው ይገባል፡፡ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ማክበር አለበት፡፡ ቀድሜ እንደነገርኩህ መንግስት ሕዝቡን የግሉ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ሕዝብ ነው መንግስትን መምረጥ የሚችለው፡፡ መንግስት የማስተዳደር አቅም ከሌለው መልቀቅ ነው ያለበት፡፡ ይሄ ነው ኢትዮጵያ የሚጎድላት፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለዚህ መስራት አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሁኔታዎች እንደምትፈልጉት ባይሆኑ ትግላችሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ሆናችሁ ትቀጥላላችሁ ወይንስ ትገነጠላላችሁ ?

አቶ አብዱልራህማን፡- ይሄን ጥያቄ ቀድሜ መልሻለሁ፡፡ የሶማሌዎች መብት በኢትዮጵያ ያለው ሕገመንግስቱ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ እነዛ በሕገ መንግስቱ ውስጥ ያሉ መብቶች ከተከበሩ መነጠል አያስፈልገንም፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቀጣዩ ምርጫ ትሳተፋላችሁ ?

አቶ አብዱልራህማን፡-አዎ በቀጣዩ ምርጫ እንሳተፋለን፡፡ እየተዘጋጀን ነው፡፡ ቢሆንም ብዙ ችግር አለ፡፡ እኔን ለመሰሉ ከሀገር ውጭ ረዥም ጊዜ ለነበሩ ሰዎች የምዝገባው ሂደት ከባድ ነው፡፡ ይሄን በተመለከተ መንግስት አንድ ነገር እንዲያደርግ እንጠብቃለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ምርጫ ቦርድ ተመዝግባችኋል ?

አቶ አብዱልራህማን፡- የተመዘገብን ነን፡፡ እኛ የዚህች ሀገር መስራች ነን፡፡ እአአ በ1991 የኢሕአዴግ አካል ሁነን ነው ስራ የጀመርነው፡፡ አሁን አስፈላጊ ከሆነ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምዝገባን በተመለከተ ሂደት ላይ ነን፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አስተዳደራዊ ወሰንና ሌሎችንም ጉዳዮች ሰበብ በማድረግ ግጭቶች ተከስተው በሁለቱም ወገን ከባድ ጉዳት ደርሶ ነበር፡፡ በርካታ ዜጎች ሞተዋል፡፡ በመቶ ሺዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ በእናንተ በኩል የግጭቱ መንስኤ ምንድን ነው ብላችሁ ነው የምትገመግሙት ?

አቶ አብዱልራህማን፡- የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝብ አብረው የኖሩ ናቸው፡፡ ግጭት የለም፡፡ 2000 ኪሎ ሜትር በሆነው የጋራ ድንበር ለረጅም ዘመናት አብረው ኖረዋል፡፡ ይኖራሉም፡፡ የአካባቢ ሰዎች በውሃ፣ በግጦሽ መሬት በመሳሰሉት ሊጋጩ ይችላሉ፡፡ በሌላው ማህበረሰብ ውስጥ እንዳለው ሁሉ ማለት ነው፡፡ ይሄ ፖለቲካዊ አላማ ይዞ የተነሳ ግጭት ነው፡፡ ይሄን የፈጠረው የሰራውም ሕወሓት ነው፡፡ በሶማሊያና በኦሮሚያ የነበረው ግጭት በመጨረሻው ሰአት በኦሮሚያ በአማራ አካባቢ ሕዝባዊ አመጹ በበረታበት ሰአት አቅጣጫ ለማስቀየር የተደረገ ነው፡፡ ይሄንን አጥብቀን እናወግዛለን፡፡ እንቃወማለን፡፡ እኛ የምናምነው እነዚህ ሕዝቦች ወንድማማቾች ሆነው ለብዙ ዘመናት የኖሩ ናቸው፡፡ኦብነግ ይህን ግጭት አይደግፍም፡፡ በማሕበረሰቦች መካከል የሚደረግ ጦርነትን አንደግፍም፤ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሶማሌና የኦሮሚያ አስተዳደራዊ ወሰንን በተመለከተ ውዝግቦች ይነሳሉ፤ መፍትሄው ምንድን ነው ?

አቶ አብዱልራህማን፡- ድንበር የሚባለው ነገር ሰው ሰራሽ ነው፡፡ በተለይ በአፍሪካ ደረጃም ድንበር የሚባለው ነገር ቅኝ ገዢዎች የፈጠሩት ሲሆን፤ ማሕበረሰቦች ለብዙ ሺህ ዘመናት አብረው ኖረዋል፤ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ወደፊትም አብረው ይኖራሉ፡፡ አውሮፓ የተለያዩ ሀገራት ድንበር ዘለል ሆነው በጋራ የህዝብ ጥቅም ተሳስረው ይኖራሉ፡፡ በህዝቦች መካከል የጋራ የሆነ የጥቅም ትስስርን ማጎልበት ነው የሚገባው፡፡ ድንበሮች ሰው ሰራሽ (አርቴፊሻል) ናቸው፡፡ እኛ በድንበሮቹ አናምንም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሰላም ማለት ለእርስዎ ምንድነው ? አሁን የሚታዩትን ችግሮች ፈትቶ ሰላም ለማስፈን ምን ይጠበቃል?

አቶ አብዱልራህማን፡- ለእኔ ሰላም ማለት የእያንዳንዱ መብት መከበር ማለት ነው፡፡ እንደ ግለሰብ እንደ ሀገር የሁሉም መብት የሚከበርበትና ማንም ሌላውን የማይጨቁንበት የማይረግጥበት ማለት ነው፡፡ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን እኩል የምንካፈልበት፤ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የምናሳድግበት፤ የፖለቲካ የኢኮኖሚ ነጻነት የሚከበርበት፤ እርስ በእርስ የምንከባበርበት፤ የሴቶቻችንን የሕጻናቶችንና የአዛውንቶችን መብት የምናከብርበት፤ በሕዝብ የተመረጠ መንግስት ሆኖ ለሕዝብ የሚሰራበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ለእኔ ሰላም ማለት ይሄ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን!

አቶ አብዱልራህማን፡- እኔም አመሰግናለሁ!

አዲስ ዘመን ጥር 2/2011

Share.

About Author

Leave A Reply