ኦነግ እና መንግሥትን ለማግባባት ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ያቀኑት የሃገር ሽማግሌዎች ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በምዕራብ ኦሮሚያ ያጋጠመውን የጸጥታ መደፍረስ በሽምግልና ለመፍታት ወደ ስፍራው አቅንተው የነበሩ የሃገር ሽማግሌዎች ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።

ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ካቀኑት የሃገር ሽማግሌዎች መካከል አንዱ የሆኑት ኢንጂነር መስፍን አበበ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ነጋዴዎች፣ አባ ገዳዎች እና የሃይማኖት አባቶች ከልዑኩ ቡድን አባላት መካከል ይገኙበታል።

“አስቀድመን ከነቀምት፣ ጊምቢ እና ደምቢ ዶሎ ከተሞች ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገናል” የሚሉት ኢንጂነር መስፍን የሃገር ሽማግሌዎቹ ከነዋሪዎች የተነሱላቸውን ጥያቄዎች እና አስተያየቶች አድምጠዋል።
ከዚያም ጊዳሚ ከሚገኝ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉን ይናገራሉ። ”የውይይቱን ውጤት መንግሥት እና ኦነግ መግለጫ የሚሰጡበት ጉዳይ ስለሆነ እኔ በዚህ ላይ ሃሳቤን አልሰጥም” ብለዋል።

ኢንጅነር መስፍን ጨምረው እንደሚሉት ”ውይይቱ በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅ ሳይሆን በቀጣይነት ብዙ ወይይት ሊያስፈልግ ይችላል” ብለዋል።

”በጉዟችንም ሆነ በቆይታችን ምንም አይነት ችግር ሳይገጥመን በሰላም ደርሰን ተመልሰናል” ይላሉ ኢንጂነር መስፍን።

ሌለው የልዑኩ ቡድን አባል የሆኑት የታሪክ መሁሩ ሼክ ሃጂ ኢብራሚም ይገኙበታል። ሼክ ሐጂ እንዳሉት ከተለያዩ የከተማ ነዋሪዎች ጋር በተደረጉት ውይይቶች ላይ በርካታ የመብት ጥያቄዎች ተነስተዋል ብለዋል።

”መሰረተ ልማቶች እንዲገነቡ፣ የኦሮሞ ህዝብ መብት እንዲከበር፣ ኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩ የሌሎች ብሔሮች ተወላጆች መብቶች እንዲከበሩ ለመንግሥት መልዕክት አስተላልፉልን ሲሉ ጠይቀውናል” ሲሉ ሼክ ሐጂ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ ከሚገኙ የኦነግ ወታደሮች እና አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የሚያስታውሱት ሼክ ሐጂ፤ ”ከፍተኛ አመራሮቻችን አዲስ አበባ ነው ያሉት፤ ከእነሱ ጋር መወያየት ይኖርባችኋል” የሚል ምላሽ ከኦነግ ወታደሮች እና አመራሮች እንደተሰጣቸው ይናገራሉ።

በተጨማሪም ‘የኦሮሞ ህዝብ መብት ለረዥም ዓመታት ሳይከበር ቆይቷል። የኦሮሞ መብት እንዲከበር እንሻለን። ይህንንም መናገር ያለበት እላይ ያሉት ከፍተኛ አመራሮቻችን ናቸው። ከእነሱ ጋር ተወያይታችሁ ከስምምነት መድረስ ትችላላችሁ” እንደተባሉ ሼክ ሐጂ ኢብራሂምም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

”ወደ ሃገር ውስጥ ሳንገባ በመሪዎቻችን እና በክልሉ ፕሬዚዳንት መካከል የተደረሰው ስምምነት ለምን ተግባራዊ አልተደረገም?” የሚል ጥያቄ በኦነግ ወታሮች መነሳቱን ሽማግሌዎቹ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ አድማሱ ዳምጠው ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ የሄዱት የሃገር ሽማግሌዎች ተደብድበው እና ተዘርፈው የሄዱበትም ዓላማ ሳይሳካ መመለሳቸውን ተናግረዋል።

በቄለም ወለጋ ዞን ከሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ የጦር መሳሪያ ተዘርፏል የሚሉት አቶ አድማሱ፤ ከአንድ ሺህ በላይ ቀበሌዎች ውስጥ የመንግሥት አስተዳደር እንዲፈርስ ተደርጎ በሌላ ሥርዓት እየተደራጀ ነው ብለዋል።

ሼክ ሐጂ ኢብራሂም ግን ”የተደበደበም ሆነ የተዘረፈ ሰው አላየንም። በሰላም ሄደን በክብር ነው የተሸኘነው” ይላሉ።

”ከውይይታችን መረዳት እንደቻልነው ሁለቱም ወገኖች የሚፈልጉት ሰላም እንዲሰፍን ነው” የሚሉት ሼክ ሐጂ፤ ከጥቂት ቀናት በኋላም የኦነግ እና የመንግሥት ባለስልጣናትን አንድ ላይ በማምጣት እንደሚያወያዩ ተናግረዋል። – ቢቢሲ

Share.

About Author

Leave A Reply