ኦዴግ የኦነግን ስህተት እየደገመ ነው? (መሳይ መኮንን)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ኦዴግ ወደ ሀገር ለመግባት መውሰኑን ዛሬ አስታውቋል። ሌሎቻችሁም ትግሉን ተዉትና ቅሌን ጨርቄን ሳትሉ ተከተሉኝ ሲልም አስገራሚ መግለጫ ሰጥቷል። ዳር ዳር ሲሉ የነበሩት አመራሮች በመጨረሻም ውስጥ ገብተን ማየቱ ይሻላል ብለው ከጀማው ተለይተው ከህወሀት ጋር ለመደራደር ወስነዋል።

ኦዴግ የኦነግን ስህተት እየደገመ ይሆን? እነዚሁ የኦዴግ መሪዎች ኦነግን ይዘው በሽግግሩ ወቅት ከህወሀት ጋር ለመስራት ገብተው ነበር:: በአስርሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቻቸው ትጥቅ እንዲፈቱ ተደርገው እነሱም ባዶ እጃቸውን አጨብጭበው ከሀገር እብስ ብለው የወጡበት ታሪክ ከህሊናቸን ጓዳ አልጠፋም። በእርግጥ የትላንቱ ህወሀት አሁንም አለ። ብሶበታል። አውሬነቱ ገደብ አልፏል። በደም የጨቀየ ከትላንት የከፋ ወንጀለኛ ሆኗል። ለትላንቱ ኦነግ ያልተመለሰ ህወሀት ለዛሬው ኦዴግ ልቡ ይራራ ይሆን? ምን ተገኝቶ ኦዴግ ሀገር ቤት ገባ? የዶ/ር አብይ አህመድን የተስፋ ቃል ተማምኖ?

እኔም በተገኘሁበት አንድ መድረክ ላይ (ሙኒክ ጀርመን) የሀገራዊ ንቅናቄው ስብሰባ ላይ የኦዴጉ ዶ/ር ዲማ ነገዎ ህወህት ጭንቅ ይዞት ለድርድር ቢጠራን እንኳን በጋራ ተነጋግረን የምንወስነው እንጂ በተናጠል ለድርድር የምንገባ አይሆንም ብለው ጭበጨባ በጭብጨባ የሆኑበትን መድረክ አስታውሳለሁ። ታዲያ አሁን ያን ቃል ምን በላው? ዶ/ር ዲማ ለሙኒኩ ተሰብሳቢ ጭብጨባውን ይመልሱ እባክዎን?!

ድርድር መልካም ነው። ይደገፋል። በመርህ ሲሆን ደግሞ ውጤቱ ጥሩ ይሆናል። የተስፋን ቃል ብቻ ተከትሎ መንገድ የሚጀምር ሃይማኖተኛ እንጂ ፖለቲከኛ አይሆንም። ዶ/ር አብይ ቤተመንግስት ገቡ እንጂ ስልጣን አልያዙም። ለነመረራ፡ በቀለ ገርባና ሌሎች የፖለቲካ መሪዎች ፊት የነሳ አገዛዝ ኦዴጎችን አበባ ነስንሶ፡ ዘንባባ አንጥፎ ይቀበላቸዋል ማለት ቂልነት ነው። ኦዴግ ትልቅ ፋወል ሰርቷል። ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት መንገድ ጀምሯል። ከሁለቱም ሳይሆን እንዳይቀር ስጋት አለኝ።

Share.

About Author

Leave A Reply