ኦፌኮ እና ኦነግ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በጋራ ለመስራት ተስማሙ።

ኦፌኮ እና ኦነግ በዛሬው እለት በጋራ በሰጡት መግለጫ ነው በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያስታወቁት።

በዚህም መሰረት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በኦሮሞ እና ኦሮሚያ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሰሩ ነው በመግለጫው ያስታወቁት።

የስምምነታቸው መሠረትም የህዝብ ጥያቄ መሆኑን የድርጅቶቹ አመራሮች ገልፀዋል።

ድርጅቶቹ፥ እውነተኛ ፌዴራላዊ ስርዓት ለማረጋገጥ፣ የህግ የበላይነትን ለማስፈንና የራስን መብት በራስ መወሰን ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ባሳለፍነው ነሃሴ ወር በሰጠው መግለጫ ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጋር ጥምረት ለመፍጠር ውይይት ማድረግ መጀመሩን መግለጹ ይታወሳል።

ሁለቱም ድርጅቶች በጋራ ለመስራት ከስምምነት የደረሱትም ይህንን ተከትሎ ነው።

መቀመጫቸውን ኤርትራ ያደረጉ የኦነግ አመራሮች የፊታችን መስከረም 5 2011 ዓ.ም ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚመለሱ ይጠበቃል።

ከኤርትራ ወደ ሀገር የሚመለሰውን ልኡክንም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ እንደሚመሩትም ተነግሯል።

በዚህም 1 ሺህ 300 የግንባሩ ታጣቂዎችም ከመሪያቸው ዳውድ ኢብሳ ጋር ትጥቃቸውን በመፍታት ወደ ሀገር ቤት ይገባሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ባሳለፍነው ነሃሴ 1 2010 ዓ.ም በኤርትራ አስመራ ከተወያዩ በኋላ የእርቅ ስምምነት መፈራረማቸውም አይዘነጋም።

Share.

About Author

Leave A Reply