“ከስንት ግዜ በኋላ ነው ግን የተገናኛችሁት?” ብለህ ለጠየከኝ፤ ምን እንደምመልስልህ አላውቅም። የጊዜ ቀመሩን ልንገርህ እችላለሁ። (ሮማን ተወልደ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የልጅነት ጓደኛዬ ነው። ሠፈራችን ያለችው ትንሿ ሜዳ ላይ አባሮሽ፣ ሌባና ፖሊስ፣ ባልና ሚስት፣ ቆሪኪ፣ አኩኩሉ ተጫውተናል። አዳልጦኝ፣ አደናቅፎኝ፣ ስሮጥ፣ ስንቀለቀል ወድቄ፤ ጉልበቴ ሲላላጥና ሲደማ አብሮኝ አልቅሷል። ትምህርት ቤት፣ አንድ ክፍል ውስጥ አብረን የመጀመሪያ ፊደል፣ አልፋቤትና ቁጥሮችን መቁጠር ጀምረናል። ቅዳሜና እሁድ ሠፈራችን አቅራቢያ ያለችው ጫካ ውስጥ ተሯርጠናል። “ጅቡ መጣብሽ!” እያለም አስፈራርቶኛል። አጋም እና ቀጋ ለቅሞ አብልቶኛል። ጥሻው ሥር ከተደበቀችው ንፁህ ምንጭ በእጁ እያፈሰ አስጎንጭቶኛል። ከ”ላሜ ቦራ” እናት ከእትዬ ማሬ ቤት ሁሌ ለዐይን ያዝ ሲያደርግ፣ ወተት ለማምጣት አብረን ሄደን ወደየቤታችን ተሸኛኝተናል።

ልጅነት በ’ኩርድና’ እና ጉርምስና ሲተካ አብረን ሠፈራችን ማዶ የሚገኘው ወንዝ ውስጥ ውኃ ተራጭተናል። በሠፈራችን ፓሲቲ እና ሻይ ቤቶች ውስጥም፣ ውጭም ድዳችንን አስጥተናል። በየቪዲዮ ቤቶቹም እየሄድን መዓት የሕንድ እና የአሜሪካ ፊልሞችን አብረን አይተናል። አምስትና ስድስተኛ ክፍል ፈጠን ፈጠን ብለው የጎረመሱት ወንዶች ካላናገርሽን፣ ካልተሽኮረመምሽልን፣ ካላስኮረጅሽን እያሉ ሲያስቸግሩኝ አስጥሎኛል። ሰኔ ሠላሳን ጠብቀው ሊደበድቡኝ ካስፈራሩኝና ካሰፈሰፉት ሁሉ አስጥሎኛል። ቢችል ኖሮ፤ በጥፋቴም ያለ ጥፋቴም በነጋ በጠባ ይቆጡኝ፣ ይቆነጥጡኝ እና ይቀጠቅጡኝ ከነበሩት ሂሳብ እና አማርኛ አስተማሪዎቻችንም ያስጥለኝ ነበር። አብረን ፒያሳ ሄደን ባቅላቫ በልተን፣ ሻይ ጠጥተን በእግራችን ሠፈር ድረስ እጅ ለእጅ ተያይዘን ተመልሰናል። ወሲብ ምን እንደሆነ የሰውነታችን እድገት ምልክቶች ቢሰጡንም፤ ደፍረን አልሞከርነውም።

መሞከሪያ ጊዜያችን ሲደርስ፣ ኑሮ ለያየን። ሠፈር ቀይረን ሄድን፤ እንደልብ ከሱ ጋር መገናኘቱም ቀረ። ዓመታት ተቆጠሩ። ግንዛቤዬም፣ ማሕበረሰቡም፣ ቤተሰቤም ማግባት እና መውለድ እንደሚጠበቅብኝ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገዶች በሚያሳውቁኝ ወቅት፤ እሱን ባገኘው እና ባገባው እመርጥ ነበር። ግን ትዳር የሚሉትን ‘እስር’ ከሱ ጋር አልደፈርኩትም። ወይ ደግሞ ‘አማልክቱ አልፈቀዱትም’።

በጠና ታምሜ፣ መፈጠሬን ባማረርኩበት ወቅት አብሮኝ ነበር። አገግሜም የህይወቴ ትርጉም ተዛብቶብኝ፣ ነገሮች ሁሉ ተፐውዘውብኝ፣ አእምሮዬን በሳትኩበት ወቅት አብሮኝ ነበር። አእምሮዬንም ስቼ፣ ነጥቼ ገርጥቼ፣ ከ’ሰውነት’ ተራ በወጣሁበት ገ ዜ ከኔ ጋር ነበር። “መቼ ነበር ይህ?” ብትለኝ፤ ሁሌም እልሀለሁኝ።

ከዛ ደግሞ፥ ሁሉም ነገር የተስተካከለልኝ እና የተሳካልኝ በመሰለኝ ወቅት፣ “ደስታሽን አላደፈርስብሽም” የሚለኝ ድምፁ እንደ ገደል ማሚቶ ይሰማኝ ነበር።

“ላለው ይጨመርለታል” ቢልም ቃሉ፥

ያለማወቄን፣ የማሕበረሰቤን፣ የቤቶቼን እና የቂልነቴን ምኞቶች ያቀፈው፣ ዓለማዊ ደስታዬ ሁሉ ተናደብኝ። ቶሎ፣ ቶሎ የተገነባው ሰንበሌጠ-ሃሴት ሲናድብኝ እና እየተንኮታኮትኩ ስወድቅ አብሮኝ ነበር። በፈጣሪና እንደነበረኝ በማላውቀው ጉልበቴ ከወደኩበት ቀና እንዳልኩ፤ አዲስ ተስፋ እና መንፈሳዊ ከፍታን የማግኘትን ተስፋም የሠጠኝ እሱ ነው። ቀና ማለቴን እንድገነዘብ እና ቀናነትን እንዳቆየውም የሚያደርገኝ እሱ ነው።

እናማ. . .

የጊዜ ቀመሩ፥ በእርግጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል የተገናኘነው ከጥቂት ወራት በፊት ነው። እሱንም ‘አማልክቱ ፈቀዱት’ እና እንዳለን፣ እንደተገናኘን አለን እልሀለሁኝ። በመንፈስ ግን ከውልደቴ፣ ከውልደቱ በፊት ጀምሮ እስከ ከዝንትዓለም ባሻገር ከፍቅሬ ጋር አብረን ነበርን፣ እንኖራለንም፣ ነንም።

Share.

About Author

Leave A Reply