ከሸዋ-አድዋ የታሪክ ፍኖት ጎዞ ክፍል ፩

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

እርግጥ ነው ጊዜ ይዳኛል። ቀደምቶች ይቀደማሉ፤ ኋለኞች ይመራሉ። ስመ ገናና ከተሞች ባድማ ይሆናሉ፤ ጠፍ ስፍራዎች ይከተማሉ። አንጎለላ ለዚህ ምስክር ናት። የዛሬን አያድርገውና አንጎለላ ግዙፍ ከተማ ነበረች። በአንጎለላ ቀዝቃዛ ነፋስ ይነፍሳል፤ የጉብታ ቁጥቋጦዎችን በመራኛ ጭፈራ ስልት እያወዛወዘ። ሰዓቱ ረፋድ ነበር። ለዘብተኛ ጀንበር ጨረሯን የፈነጠቀችበት። ስፍራው ወለል ያለ ሜዳ ነው። በአራቱም ማዕዘናት ሲመለከቱ የመልክዓ ምድር ሰገነት የለም። እንደ አከንባሎ በተደፋ ሰማይ ስር ሰፌድ መሰል መልክዓ ምድር ከመጫሚያ ስር ተነጥፏል ብጉር የወረሳት ኩይሳ መሰሏ የ’አንጎለላ’ ኮረብታ ላይ ቁብ ብለው ሲታዘቡ።

መዳረሻዬ ሩቅ ነው፤ አድዋ። መነሻዬ ቅርብ ነው፤ ከነገስታቱ ባድማ ሸዋ። “ስፍራው ‘አንጎ’ ለምትባል ሴት ነበር፤ ባለቤቷ ‘ሎላ’ ይባላል። ንጉስ ሣህለሥላሴ ቦታውን ምትክ መሬት ሰጥተው ለቤተ መንግስትነት ከመውሰዳቸው በፊት” ብለውኛል በስፍራው ያገኘኋቸው የዕድሜ ባለጸጋ አዛውንት። አንጎለላ የዕደ ጥበብ ኢንዱስትሪና የዲፕሎማሲ ማዕከል የነበረች፣ የንጉሥ ሣህለሥላሴ ከተማ፤ የሸዋ ነገስታት ባድማ ናት። ለቤተ መንግስትነቷ ቋሚ ምስክሮች ግን አልጠፉም። የሣህለሥላሴ ባለሁለት ፎቅ ህንፃ ፈራርሶ ምድር ቤቱ ብቻ ይገኛል። በአፄ ልብነድንግል አባት በአፄ ናዖድ የተመሰረተች ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያንም በስፍራው ትገኛለች። ”ቤተ ክርስቲያኗ የነገስታት መሳለሚያ ነበረች” ይላሉ የአካባቢው አባቶች። በፀበልተኞች የተከበበችዋ ደብር በአማኞች አጠራር ‘ሠሚነሽ ኪዳነ ምህረት’ ይሏታል።

ቤተ ክርስቲያኗ የአድዋና የአምባላጄውን ጀግና የፊታውራሪ ገበየሁን አጽም በክብር አስቀምጣለች። በቤተ መንግስቱ ፍርስራሾች ሶስት ግዙፍ ዛፎች ይገኛሉ። እነሱም የችሎት ማስቻያ ዛፍ (ቆባ ይባላል በእኔ ትውልድ ቀዬ)፣ ንጉሱ ከግብፅ ለመብረቅ መከላከያ ያስመጡት የኮርች ዛፍ እና በመኳንንቱ ጠጅ እየጠጣ ማደጉ የሚነገርለት ሾላ ዛፍ ናቸው። ‘ሰሜን ሸዋ ዛፉም፣ ሰዉም፣ አፈሩም ታሪክ ነው’ ያሉትን ምሁር ያስታውሳል። የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ትውልድ ስፍራ (እንቁላል ኮሶ) ከአንጎለላ ቤተ መንግስት ፍርስራሽ ቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል። ንጉሠ ነገስቱና የጦሩ ፊታውራሪ (ጎራው ገበየሁ) አንድ ቀን የተወለዱና በልጅነት በጋራ ቦርቀው ያደጉ ሲሆን ምኒልክ ‘ታላቅ የጥቁር ንጉሠ ነገሥት’፤ ፊታውራሪ ገበየሁ ደግሞ ጀግና የጦር መሪ ሆነዋል።

ወደ አድዋ ሲዘምቱም ታማኙ ፊታውራሪ “ግንባሬን ከተመታሁ ከትውልድ ስፍራዬ ቅበረኝ፤ ስሸሽ ጀርባየን ተመትቸ ከወደኩ ስጋዬን ለአሞራ ስጠው” ብለው ለንጉሡ ተናዘዙ። ከአድዋ ጦርነት ቀደም ብሎ ሕዳር 28 ዘንጉን ይዞ አምባላጄ ሲያዋጋ ዋለ። የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም ደግሞ መድፉን ይዞ አድዋ ላይ ተሰለፈ። ከምንድብድ (አድዋ) ጦር ሜዳ መድፈኛው ፎክሮ ጠላት መሃል ገባ። ግንባሩን ተመቶ መስዋዕት ሆነ። ንጉሱም ከሰባት ዓመታት በኋላ ክርስትና ከተነሱባት ደብር አፅሙን በክብር በማስቀመጥ ቃላቸውን ጠበቁ። በአንድ ጀምበር፣ በአንድ ቀን የተወለዱት፣ በአንድ ልብ ተማምነው አኩሪ ገድል የፃፉት ዳግማዊ ምኒልክና ፊታውራሪ ገበየሁ ለዘላለም ተለያዩ። ከአድዋ ጦርነት መልስ ጃንሜዳ ላይ በነበረ ሰልፍ የቀኝ እጃቸው የፊታውራሪ ገበየሁ ፈረስ ሌጣውን ከፊታቸው ሲያልፍ ዳግማዊ ምኒልክ ስቅስቅ ብለው ማልቀሳቸውን ጸሃፌ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ፅፈዋል። አዝማሪም የሁነቱን ትንግርት በስንኝ ቋጠሮ አዜመ።

‘አድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው፣ ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው፣ ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፣ ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ” የተባለላቸው ታላቁ የጥቁር ንጉስ አበሻን ለጠላት እንቁላል ከመገበር ታደጉት። ከሳምንት በፊት ለ123ኛ ጊዜ ዝክረ አድዋ በጀግኖች ትውልድ ስፍራ (አንጎለላ) በድምቀት ሲከበር ጀግኖች በቦረቁበት ስፍራ ፈረሰኞች በጉግስና ሽምጥ ግልቢያ እንዲሁም በአማርኛና ኦሮምኛ ባህላዊ ጭፈራዎች ዘክረዋቸዋል።

ሙሉውን ጽሁፍ ይህን ተጭነው ያንብቡ

 

Share.

About Author

Leave A Reply