‹‹ከባንኮች ዘረፋ ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ኦነግ እንዳልፈጸመና ሲጀመር አካባቢው በመከላከያ ሠራዊት ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት በመሆኑ፣ የኦነግ ወታደሮች አልፈጸሙትም፤›› አቶ በንቲ ኡርጌሳ፡፡

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ባለፉት ሦስት ዓመታት አገሪቱን ወጥሮ የቆየው የግጭትና የአመፅ አዙሪት በተወሰነ ደረጃ ጋብ ያለ ቢሆንም፣ በሌላ ወገን ደግሞ ግጭቶች እንደ አዲስ የሚፈጠሩባቸውና ሁከቶች የሚስተናገዱባቸው ሥፍራዎች አልጠፉም፡፡ ይህም ቀድሞ የነበረው አመፅ ሥፍራ ቀየረ እንጂ አልረገበም ለሚሉ ወገኖች ሁነኛ መከራከሪያ ምክንያት ሆኗል፡፡

አሁንም ቢሆን በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ፣ በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር፣ በደቡብ ክልል ምዕራባዊ ዞኖችና በአፋር ክልል የነበሩ ግጭቶችና አመፆች፣ የአገሪቱ የሕይወት መስመር የሚባለውን የጂቡቲ መንገድ ማዘጋትና የሰዎችን ሕይወት እስከ መቅጠፍ የደረሱ ናቸው፡፡

የምዕራብ ወለጋ ጉዳይ

በምዕራብ ወለጋና በሌሎች ሦስት የኦሮሚያ ዞኖችና በቤንሻንጉል ጉምዝና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ታጥቆ የሚንቀሳቀስ የኦነግ ‹‹ሸኔ›› ቡድን እንደሚገኝ፣ ይህም በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራ እንደሆነ ባለፈው ሳምንት በአገሪቱ ወቅታዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት የአገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ አስታውቀው ነበር፡፡ ይህም የታጠቀ ኃይል በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝና መንግሥትም ባሳየው የተራዘመ ትዕግሥት ጉዳቱ እንዲያይል መሆኑን አስረድተው፣ በተለይ በምዕራብ ወለጋ መንግሥት ትጥቅ ለማስፈታትና ጥፋተኞችን ወደ ሕግ ለማቅረብ የአገር መከላከያ ሠራዊት ማሰማራቱን አስታውቀው ነበር፡፡ ከኤርትራ ይዞ ያመጣቸውን 1,200 ወታደሮች ወደ ካምፕ ከማስገባት በተጨማሪ አገር ውስጥ ያሉትን ታጣቂዎች ከዛሬ ነገ ለመንግሥት አስረክባለሁ እያለ በገዛው ጊዜ አዳዲስ አባላትን እየመለመለ ማሠልጠን ጀምሯል ያሉት ጄኔራሉ፣ የኦነግ ‹‹ሸኔ›› ሠራዊት በተሰነዘረበት ጥቃት ከከተማ ሸሽቶ ጫካ ገብቷልም ብለው ነበር፡፡

ይሁንና እሑድ ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. መንግሥት በወሰደው ዕርምጃ በሔሊኮፕተር በመታገዝ በኦነግ ጦር ላይ ጥቃቶችን ፈጽሟል የሚል መረጃ በስፋት ተሠራጭቶ ነበር፡፡ ይሁንና ይህ መረጃ ፍጹም የተሳሳተና መንግሥትን ለዚህ ዓይነት ጥቃት የሚያነሳሳ ምንም ምክንያት እንደሌለ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ የኢንዶክትሪኔሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና በምዕራብ ኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉምዝ የተፈጠረውን ግጭት ለማርገብ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አባል ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከ15 ቀናት በፊት የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በአካባቢው ሰላም የማስከበር ሥራ እያከናወነ መሆኑን የገለጹት ኮሎኔል ጌትነት፣ ‹‹በአየር ኃይል ለመጠቀም የሚያስችል ምንም ሁኔታ የለም፡፡ ቦምብ ለመጣልና ውጊያ ለመክፈት በአውሮፕላን የሚያደርስ ነገር የለም፤›› በማለትም የተሳሳተ መረጃ እየተሠራጨ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን በአካባቢው ከታጣቂዎች ጋር ውጊያ እያደረገ ላለው ሠራዊት ስንቅ ለማድረስ፣ የአመራሮች ጉብኝት ለማድረግና ትዕዛዝ ለማድረስ በሔሊኮፕተር እንቅስቃሴ ሲደረግ ነበር ብለዋል፡፡ የታጠቁ ተዋጊዎች በሠራዊቱ ሲማረኩም በሔሊኮፕተር እንደሚነሱም አስረድተዋል፡፡ በኅብረተሰቡ ጥቆማ የታጠቁ ኃይሎችና መሣሪያዎች በመያዝ ላይ መሆናቸውም አክለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያናገራቸው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የአስተዳደርና ፋይናንስ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ በንቲ ኡርጌሳ፣ ‹‹ግንባሩ በኦሮሚያ ክልል ያለውን የፖለቲካ ተቀባይነት ለማሳጣት፣ ሌሎች የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ያልተሳተፉበትና በዋናነት በአዴፓ ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ ጥቃት እየደረሰብን ነው፤›› ሲሉ አማረዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም በተለይ በቄለም ወለጋ ዞን የሚገኙ ተቋማት ላይ በሔሊኮፕተር የታገዘ ድብደባ በመደረጉ በንፁኃን ላይ ጉዳት መድረሱንም አክለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢው ያሉ የታጠቁ ኃይሎች በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ባንኮች መዘረፋቸው ታውቋል፡፡ ኮሎኔል ጌትነት በተለያዩ አካባቢዎች ዘረፋ ‹‹ሙከራዎች›› መኖራቸውን ገልጸው፣ ምን ያህል የባንክ ቅርንጫፎች ጥቃት እንደተሰነዘረባቸውና ምን ያህል ገንዘብ እንደተወሰደ መጣራት አለበት ብለዋል፡፡ ሆኖም ይህን ያህል ባንኮች ተዘረፉ በማለት በሚሠራጨው ዘገባ ስህተት ነው ሲሉ አጣጥለዋል፡፡

‹‹ይኼንን ዝርፊያ የፈጸመው ኦነግ ይሁን አይሁን ሌላ የታጠቀ በድርጅት ስም የተደራጀ ቢሆንም ባይሆንም በክፍተቱ እየተጠቀመ ያለ አካል ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረበላቸው አቶ በንቲ ኦነግ በባንኮች ላይ ዘረፋ እንዳልፈጸመ ተናግረዋል፡፡

‹‹ከባንኮች ዘረፋ ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ኦነግ እንዳልፈጸመና ሲጀመር አካባቢው በመከላከያ ሠራዊት ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት በመሆኑ፣ የኦነግ ወታደሮች አልፈጸሙትም፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን የኦሮሚያ ክልል ማክሰኞ ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ማምሻውን ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ 18 ባንኮች መዘረፋቸውንና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት መድረሱን ያስታወቀ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም መዘረፉን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም አሥር ያህል የመንግሥትና የግል ተሽከርካሪዎችም ተቃጥለዋል ብሏል፡፡ ወንጀሉን ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ወደ አሥር የሚጠጉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ላይ ጥቃት መድረሱን፣ ከእነዚህም መካከል በአምስቱ ላይ ዘረፋ መፈጸሙን የባንኩ ምዕራብ ዲስትሪክት ኃላፊ አቶ ግርማ ጨብሲ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ ግርማ አክለውም ጥቃቱ በታጠቁ ኃይሎች መፈጸሙን እንጂ በየትኛው አካል እንደተፈጸመ እርግጠኛ ሆነው መናገር እንደሚቸግራቸው ገልጸዋል፡፡ ጥቃት የደረሰባቸውን ባንኮች ሥራ አስኪያጆችን ማግኘት እንዳልተቻለና ስልካቸው ዝግ እንደሆነ፣ በዚህም ምክንያት ምን ያህል ጉዳት እንደረሰ መጠኑን ማወቅ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ ኦሮሚያ የሚገኘው የኦነግ ጦር ከአባ ገዳዎች የተደረገለትን ጥሪ ተቀብሎ ወደተዘጋጀለት መጠለያ ካምፕ እየገባ እንደሚገኝም ታውቋል፡፡

ያልበረደው የአፋር ተቃውሞ

ከዓመታት በፊት በብዛት የሶማሌ ኢሳ ብሔረሰብ አባላት የሚኖሩባቸው ሦስት ቀበሌዎች ወደ አፋር ክልል መካተታቸውን በመቃወም የጀመረው ተቃውሞ፣ ከእሑድ ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ ማግሥቱ ጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀትር ድረስ የኢትዮጵያ 80 በመቶ በላይ የወጪና ገቢ ንግድ የሚስተናገድበት የኢትዮ-ጂቡቲ መንገድ እንዲዘጋ መንስዔ ሆኗል፡፡ ሦስቱ ቀበሌዎች ተመልሰው ወደ ሶማሌ ክልል መካለል አለባቸው በሚል መነሻ በተነሳ ተቃውሞ አንድ የአፋር ተወላጅ መሞቱ ለክስተቱ ዋነኛ መነሻ እንደሆኑ ለሪፖርተር የገለጹት ምንጮች፣ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት መንግሥት በገባው መሠረት መንገዱ ቢከፈትም፣ በሌሎች የአፋር ክልል አካባቢዎች ተቃውሞው መቀጠሉን ጠቁመዋል፡፡

ካሁን ቀደም ታኅሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በተመሳሳይ ሥፍራ በተከሰተ ግጭት አራት ሰዎች መሞታቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ ኡንዳፎኦ፣ አዳይቱና ገዳማይቱ የተባሉ ቀበሌዎች ለተደጋጋሚ ግጭቶች ምክንያት እየሆኑ እንደሚገኙና በብዛት የሶማሌ ኢሳዎች የሚኖሩባቸው ቀበሌዎች እንደሆኑ ታውቋል፡፡

በአፋር ክልል በተነሳ ታቃውሞ ከአርዳኢታ እስከ አዋሽ በተዘጋው የኢትዮ ጂቡቲ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ምንም ዓይነት ጉዳት ባይደርስባቸውም፣ በተፈጠረ ሥጋት የአዲስ አበባ የነዳጅ ማደያዎች ከወትሮው የተለየ በተሽከርካሪዎች ሠልፍ ተጨናንቀዋል፡፡ በተጨማሪም ቤንዚን የሚመጣበት የኢትዮ ሱዳን መንገድ በቅርቡ በምዕራብ ጎንደር በተፈጠረ ግጭት መዘጋቱና ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ድንበር ላይ ተሠልፈው መቆማቸው ይታወሳል፡፡ እስካሁንም የአካባቢው ሰላም ወደነበረበት እንዳልተመለሰና በአካባቢው አንፃራዊ ሳላም ቢታይም፣ የተጠናከረ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው እየተገለጸ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በፀጥታ ምክንያት ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ወጥተው በባህር ዳር ዳር ከተማ ተጠልለው የሚገኙ ተማሪዎች በከተማው በመዘዋወር ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን፣ የነዋሪዎች ቤቶች በድንጋይ ሲደበድቡ እንደነበርም ተገልጿል፡፡ ይህም ድርጊት በከተማ አስተዳደሩ ተወግዟል፡፡ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ ተማሪዎቹ አልተመቸንም ካሉ ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰባቸው ተዘግቧል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ግጭት

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ታኅሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በተፈጠረ ግጭት ዘጠኝ ሰዎች ከሞቱ በኋላ፣ በወረዳው በሠፈራ ይኖሩ የነበሩ በርካታ የከምባታና ሌሎች ብሔሮች ተወላጆች እስካሁን ድረስ እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ ሪፖርተር ከሥፍራው ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዞኑ ከ1996 ዓ.ም. ወዲህ በሰፈራ መጥተው የሚኖሩ የከምባታ ተወላጆች በሚኖሩበት አካባቢ በተደጋጋሚ ከሜኤኒት ጎልድያና ከሜኤኒት ሻሻ የሚመጡ የታጠቁ ኃይሎች ጥቃቶች የሚፈጽሙ ሲሆን፣ በሥፍራው ሰላም ለማስፈን ከደቡብ ክልል ከመጡ ቡድኖች ጋር በጋራ እየተሠራ እንደሚገኝ የካፋ ዞን የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሤ ወልደ ጊዮርጊስ ለሪፖርተር በስልክ አስታውቀዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ ልዩ ኃይል ገብቶ የማረጋጋት ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ንጉሤ፣ ነገር ግን ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ ያስረዳሉ፡፡ እንደሳቸው ገለጻ የተፈናቃዮች ቁጥር መጨመር ምክንያት ተመሳሳይ ጥቃቶች አሁንም ሊፈጸሙ ይችላሉ በሚሉ ሥጋቶች ነው፡፡ አንዴ ከወጡ በኋላ ተመልሰው ቤተሰቦቻቸውን በመውሰድ ላይ ያሉ ተፈናቃዮችም እንደሚገኙ አክለዋል፡፡

ይሁንና በታኅሳስ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ማግሥት የክልሉ ልዩ ኃይልና ታጣቂዎቹ ባደረጉት ውጊያ ታጣቂዎቹ የበለጠ የተደራጁና የተጠናከሩ መሆናቸው መታየቱን የገለጹት አቶ ንጉሤ፣ ይህ ሰላም የማስፈን ሥራውን ከባድ እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡

እነዚህ የታጠቁ ቡድኖች በዞኑ ወረዳዎች፣ በኮንታ ዞንና በዳውሮ ዞን ተመሳሳይ ጥቃቶችን ይሰነዝራሉ ያሉት ኃላፊው፣ ጉዳዩን በውይይት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸው፣ በስም ጭምር አጥፊዎችን በመለየት ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አክለዋል፡፡ እነዚህ ታጣቂዎች መሽገው ስለሚገኙ መያዝ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው በመግለጽ፣ በልዩ ኃይልና በመከላያ ሠራዊት የመሸጉትን የመያዝ ኦፕሬሽን ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳን ካለፈው ክረምት ወዲህ በዚህ ሥፍራ በተፈጸሙ በተደጋጋሚ ጥቃቶች 31 ሰዎች የሞቱ ቢሆንም፣ በተጠርጣሪነት የተያዘ አንድም ሰው ግን የለም፡፡ ከሞቱት ውስጥ 21 የሚሆኑት ከምባታዎች ሲሆኑ፣ አሥር ደግሞ የካፋ፣ የቤንጃ፣ የጫራና የመኤኒት ተወላጆች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

አሁን መከላከያም ሆነ ልዩ ኃይሉ ነዋሪዎችን ከጥቃት መከላከል ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ነባር ነዋሪዎችም በሥጋት ከአካባቢው እንለቃለን በማለት ላይ ስለሆኑ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት በትብብር እየተሠራ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

የካፋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ማስረሻ በላቸው ተፈናቃዮችን ያሉበት ሥፍራ ድረስ በመሄድ በመጎብኘት የተፈጸመባቸውን ጥቃት ማውገዛቸው ታውቋል፡፡

(ሪፖርተር)

Share.

About Author

Leave A Reply