ከቤኒሻንጉል የተፈናቀሉ ከ500 በላይ አባወራዎች ለልመና ተዳርገናል አሉ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ከ5 ወራት በፊት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ ከ500 በላይ አባወራዎች ለልመና መዳረጋቸውን ገልፀው፤ የአማራ ክልል መንግስት ችግራቸውን ተገንዝቦ እንዲያቋቁማቸው ቢጠይቁም ተገቢውን ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናገሩ፡፡ የክልሉ መንግሥት በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ውይይት እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን፣ ሎንጃንፎ ወረዳ፣ ከ20 እና 25 ዓመታት በፊት ኑሮ መጀመራቸውን የጠቆሙት የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ተፈናቃዮች፤ አንድ የክልሉ ተወላጅ ተገድሎ በመገኘቱ “እናንተ ናችሁ የገደላችሁት” በሚል በአካባቢው ሰዎች ጥቀት መፈፀሙን ተከትሎ፣ ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡

በወቅቱ በተፈፀመው ጥቃትም 13 ሰዎች እንደተገደሉ፣ 49 ሰዎች በጦርና በቀስት ተወግተው መቁሰላቸውን እንዲሁም 150 ያህል ቤቶች መቃጠላቸውን የጠቆሙት ተፈናቃዮቹ፤ ህይወታቸውን ለማትረፍ፣ ያፈሩትን ሃብት ሳይሰበስቡ ባዶ እጃቸውን ወደ ባህር ዳር መሸሻቸውን ያስታውሳሉ፡፡

አባወራዎቹ ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ወደ ባህር ዳር በመሄድ በጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የተጠለሉ ሲሆን የከተማዋ ነዋሪዎች ተቀብለው ሲያስተናግዷቸው መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ለልመና መዳረጋቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል።

“ቤኒሻንጉል በነበርን ጊዜ በንግድ፣ በግብርና እንዲሁም በተለያዩ የሙያ መስኮች ተሰማርተን ሃብትና ንብረትም አፍርተን እንኖር ነበር” ያሉት ተፈናቃዮቹ፤ “ያፈራነውን ሃብት ጥለን ስለወጣን በአሁኑ ወቅት ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠናል፤ የአማራ ክልል መንግስትም ለጥያቄያችን ምላሽ አልሰጠንም” ሲሉ ያማርራሉ፡፡

ላፉት ወራት የሚያቋቁመን አጥተን በጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተጠልለን፣ እርዳታ ጠባቂ ሆነናል ያሉት ተፈናቃዮቹ፤ ልጆቻቸውም ትምህርት ማቆማቸውን ይናገራሉ፡፡  የአማራ ክልል ችግራቸውን ተገንዝቦ እንዲያቋቁማቸው ቢጠይቁም፤ “ወደ ቤኒሻንጉል ተመልሳችሁ ኑሩ አሊያም ወደየትውልድ ቀዬአችሁ ተመለሱ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ይገልፃሉ- ተፈናቃዮቹ፡፡

“ሃብትና ንብረታችን ወድሟል፣ ተዘዋውሮ ሰርቶ ሃብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብታችን ተጥሷል” ሲሉ ቅሬታቸውን የገለፁት ተፈናቃዮቹ፤ “ለተጣሰብን ህገ መንግስታዊ መብት መንግስት ኃላፊነት ስላለበት፣ መልሶ ሊያቋቁመን ይገባል” ብለዋል፡፡ መፈናቀላችን ሳያንስ በየአብያተ ክርስቲያናቱ መጠለያ እንዳንጠለል በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ወከባ እየተፈፀመብን ነው፤ የታሰሩም አሉ” የሚሉት ተፈናቃዮቹ፤ አሁን የሃይማኖት አባቶችንና የሃገር ሽማግሌዎችን ወደ አማራ ክልል ባለስልጣናት ልከን ምላሽ እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡

የባህር ዳር ህዝብ ከጎናቸው በመቆም ትብብር እያደረገላቸው እንደሚገኝም ተፈናቃዮቹ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው የክልሉ መንግስት በጉዳዩ ላይ ውይይት እያደረገ መሆኑን ትናንት ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ የማፈናቀል ድርጊቱን የፈፀሙና በድርጊቱ እጃቸው ያለበት የመንግስት ባለስልጣናትና ግለሰቦች በህግ እንዲጠየቁ አሳስቧል፡፡

እነዚህን ተፈናቃዮች ጨምሮ በየቦታው በሚፈጠሩ መሰል ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎች፤ በመንግስት ድጋፍ የሚቋቋሙበት መንገድ መመቻቸት አለበት” ብሏል – ፓርቲው፡፡

“ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካማሽ ዞን የተፈናቀሉት ከ800 በላይ ናቸው” ያለው “ሰማያዊ” ፓርቲ፤ የተፈናቀሉትን ዜጎች የአማራ ክልል ሊያስተናግዳቸው ባለመቻሉ በመጋዘንና በቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ ተጠልለው ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ጠቁሟል፡፡

ፓርቲው አያይዞም፤ በደቡብ ክልል ጌዴኦ እና በኦሮሚያ ጉጂ ዞን አዋሳኝ አካባቢ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፣ የተፈናቀሉ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎችም በአስቸኳይ እንዲቋቋሙ ጠይቋል፡፡

ምንጭ – አዲስ አድማስ

Share.

About Author

Leave A Reply