«ከአርባ ቀን ዕድል ይልቅ የአርባ ቀን ትግል ያስፈልጋል» – ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በየትኛውም የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ለአመራሩ ‹‹ከአርባ ቀን ዕድል ይልቅ የአርባ ቀን ትግል›› አስፈላጊ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ፡፡

አመራሮች፣ ስልጣንን ጨምሮ ምንም ዓይነት ቋሚ የሆነ ነገር እንደሌለ ተገንዝበው በስልጣን ዘመናቸው የማይዘነጋ አሻራ አሳርፈው ማለፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው ለሚኒስትሮች፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና ለፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች በቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የአገሩቱን ህዳሴ ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አመራሩ የተሰጠውን ዕድል በሥራ ትጋት በማጀብ፤ ቋሚ የሆነ ነገር እንደሌለ በመገንዘብ ጊዜውን ህዝብን ለማገልገል መጠቀም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

አመራሩ የተሰጠውን የአገልጋይነት ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም ጊዜና ዕድልን አጣጥሞ መጓዝ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ዕድል ብቻውን ውጤት ስለማያመጣ አመራሩ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ትግል ማድረግና ያለችውን ጊዜ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ውጤታማ አመራር የህሊና፣ የቃልና የተግባር ውጤት ነው፡፡ በመሆኑም አመራሩ ከሌብነት የጸዳ ሕሊና በመያዝ የገባውን ቃል በተግባር ለመለወጥ መጣር ይኖርበታል፡፡

በመርህና ዓላማ የሚመራ ተግባር ማከናወንም ይኖርበታል፡፡ ጥሩ ሥነ ምግባርና ለሥራው የሚያግዝ ችሎታ ያለው፤ ለአገልጋይነትም የተሰጠ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

ራስን ከሥራና አሰራሮች ጋር ማላመድ፣ አሰራርን ግልጽና አሳታፊ ማድረግ፣ ለተቋማዊና አገራዊ ለውጥ የማያስፈልግ አካል አለመኖሩን መገንዘብ፣ በአንድ ጊዜ ሁሉን ላድርግ አለማለት፣ ለውሳኔ አለመቸገርና እጅግ ፍጹምነትን አለመፈለግን የመሳሰሉትም ለሚከናወኑ ሥራዎች ውጤታማነት ጠቃሚ መሆናቸውን አውቆ መስራት ያስፈልጋል፡፡

«ትናንት ከእጅ የወጣ ገንዘብ ነው፤ ዛሬ ደግሞ በእጅ እንዳለ ጥሬ ገንዘብ ነው፤ ነገ ግን ያልተመነዘረ ገንዘብ ወይም ቼክ ነው» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጊዜ እንደ ሕይወት ዘመን መሆኑን ተገንዝቦ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሥራ ሁነቶችን በጣም አስቸኳና በጣም ጠቃሚ፣ ወይም ያነሰ አስቸኳይና ያነሰ ጠቃሚ ብሎ መመልከት በሥራ ላይ መዘናጋትን ስለሚፈጥር ሁሉንም በወቅቱና በጊዜው ማከናወን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ጊዜን፣ ወጪን፣ ጥራትንና መጠንን አጣጥሞ ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ማከናወን፤ ያለውን ነገር ደምሮም የህዳሴውን ጉዞ ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply