ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያት ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በሞያሌ ከተማ በሚያዝያ 28/2010 ዓ.ም በተደራጀና በህቡእ ዝግጅት በተደረገበት የጥፋት ተልዕኮ በሁለት ጎራዎች የታጠቁ ኃይሎች መካከል ማህበረሰብን ዒላማ ያደረገ በመጠኑም ሰፋ ያለ ግጭት ተከስቶ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ደርሷል። በዚህ ግጭት የዜጎች ጠፍቷል የመቁሰል አደጋም ደርሷል።

በመላ ሃገሪቱ መንግስት እና የፀጥታ ኃይሎች ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን እያካሄዱ ባሉት ተከታታይ ስራና ጥረት ሰላምና መረጋጋት እየሰፈነ ባለበት በአሁኑ ወቅት በህብረተሰቡ መካከል ግጭት እንዲፈጠርና ያለመረጋጋት እንዲሰፍን በሚሰሩ የሁከትና ብጥብጥ ኃይሎች ምክንያት ለደረሰው የዜጎች ህይወት መጥፋት ኮማንድ ፖስቱ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ይገልፃል። በዚህ ተግባር ላይ የተሳተፉና ከጀርባ ሆነው ድርጊቱን ሲመሩ የነበሩ አጥፊዎችን የመለየትና የማጣራት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ሃይሎች ግጭቱን ያስቆሙት ሲሆን ሁኔታዎችም በመረጋጋት ላይ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በስፋት እይተካሄደ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ተገንዝቧል። እስከ አሁን የፀጥታ ኃይሎች ባካሄዱት ጥብቅ ክትትልና በህብረተሰቡ ጥቆማ በሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም ብቻ 142 ክላሽ፣ 88 ሽጉጥ፣ 17 የኋላ ቀር መሳሪያዎች፣ ከበርካታ ተተኳሾች ጋር እንዲሁም 11 የእጅ ቦምቦች በቁጥጥር ስር ውሏል።

ይህ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ በሞያሌ ከተማም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ለሚከሰቱ ግጭቶችና ለሚደርሰው ጉዳት ስፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው።

በመሆኑም በሞያሌ ከተማ የፀጥታ ኃይሉ ከመንግስት በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት ትጥቅ የማስፈታት ስራ እያከናወነ ሲሆን አስፈላጊው ጥናት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ሁሉ የተጠናከረ ትጥቅ የማስፈታት እርምጃ የሚቀጥል መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ያስገነዝባል።

ህጋዊና ለስራም ሆነ ለአካባቢ ጥበቃ የሚውል ትጥቅ ያላቸው ዜጎችም ትጥቃቸው ለማንኛውም ግጭት መንስኤና ለህገ ወጥ ድርጊት አገልግሎት እንዳይውል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኮማንድ ፖስቱ ያሳስባል።

በመጨረሻም ህብረተሰቡ ሰላሙን ከሚያናጉ ማንኛውም ኃይሎች ሴራና የጥፋት ድርጊት ራሱን በመጠበቅና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተባብሮ በመስራት የከተማውን ብሎም የአካባቢውን ሰላም የማስጠበቅ ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮማንድ ፖስቱ ጥሪውን ያቀርባል።

Share.

About Author

Leave A Reply