ከአንተ በፊት አባ ገዳ ነግሮኛል !

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

አባቴ እና ወንድሙ በኦሮሞ ምድር ሀብት አፍርተው ትዳር መሥርተው ወልደው ከብደው ይኖሩ ነበር:: ከእለታት በአንዱ ቀን የኦሮሞ አባ ገዳዎች እባቴን እና አጎቴን ጠርተው እንዲህ ሲሉ ጠየቋቸው:: “ሀገራችን ሀገራችሁ ልጆቻችን ልጆቻችሁ ናቸው:: እስካሁን እንደ እንግዶች ሆናችሁ አብረን ኖረናል:: ከአሁን ብኇላ ግን እንግድነታችሁ አብቅቷልና ኦሮሞ ሆናችኇል:: ከፈለጋችሁ ጎሳ መርጣችሁ ስም ሰይመንላችሁ አብረን እንኖራለን:: ይቅርብን ካላችሁ ደግሞ ጎሳም ሳትመርጡ ስማችሁም ሳይለወጥ የኦሮሞ ቤተሰብ ሆናችሁ ኑሩ” አሏቸው:: አጎቴ ስሙ ሽፈራው ደለለኝ መሆኑ ቀርቶ “ባልቻ ሄርጳ” ተብሎ የጎሳ አባል ሆነ:: ልጆቹንም ኦሮሞ ብቻ አድርጎ አሳደገ:: አባቴ ግን ስሙንም ሳይቀይር ጎሳም ሳይመርጥ መኮንን ደለለኝ እንደተባለ አማራ የሆነ የኦሮሞ ቤተሰብ ሆኖ ኖረ:: ልጆቹንም አማራ እና ኦሮሞ አድርጎ አሳደገን:: እኛም በአማርኛ እና በኦሮምኛ አፋችንን ፈተን አደግን::

ኦሮሞ የሆነው አጎቴ ባልቻ ከሦስት ወር በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ ቤተሰብ ለቀብር ሄደን የአየሁት ትንግርት ነበር:: እንደ አንድ የኦሮሞ አባገዳ በፈረስ ጉግስ የታጀበ ከፍ ያለ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመለት:: ከቀብር በኇላም የኦሮሞ አባገዳዎች ቤተሰቡን “የአጎታችሁን መሬት እያረሰ ሀብት ንብረቱን ወርሶ ኦሮሞ ሆኖ አብሮን የሚኖር ሰው ወክሉ” አሉን:: አንደኛው የአጎታችን ልጅ ጎሳውንም ሀብቱንም ስሙንም ወርሶ ኑሮውን ቀጥሏል::

አንተ አውሮፖ አሜሪካ እና አውስትራሊያ ተቀምጠህ “ውጣ እና ግባ ወይንም ነባር ነህ ሠፋሪ” እያልክ የምትሰድበኝን ዘገምተኛና ዘረኛ “አክቲቪስት” ነኝ ባይ አልሰማህም:: ምክንያቱም ስለ ኦሮሞ አቃፊነት (ሞጋሳ) ከአንተ በፊት አባቴ አስጠንቶኛል:: አንተ ሳትወለድ (ሳትጨነግፍ ላለማለት ያህል) ወዶና ፈቅዶ ኦሮሞ የሆነው አጎቴ መንዜው ባልቻ ሄርጳ መርቆኛል:: ከአንተ በፊት አባ ገዳ ነግሮኛል:: ከአንተ ይልቅ አባገዳን ስለማምን ስድብህን አልሰማህም!!!

(ዮሀንስ መኮንን)

Share.

About Author

Leave A Reply