Thursday, January 17

ከ2 ሺህ በላይ ብስክሌቶች ከአራት ዓመታት በላይ ያለጥቅም መጋዘን ውሰጥ ተከማችተዋል

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለአማራ ክልል ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የሚረዱ ከ2 ሺህ በላይ ብስክሌቶች ለክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ከአራት ዓመታት በፊት መስጠቱ ተዘግቧል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮም ብስክሌቶቹን ከሶስት ዓመታት በላይ ለጸሃይና ለዝናብ አጋልጧቸው ቆይቷል፡፡ ከአንድ አመት በፊት ደግሞ የዓለም አቀፍ ኦዲተሮች መምጣታቸውን ተከትሎ ያለመጠለያ ተሠጥተውበት ከነበረው ሜዳ በማራቅ አባይ ማዶ ወደሚገኝ መጋዘን እንደተለመደው ያለስርዓት እንዲደረደሩ ተደርገዋል።

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ድካም ያልቀነሰው ሀብት ከአራት ዓመታት በላይ ለጥበቃና ለማቆያ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲወጣ በማድረግ ለከፍተኛ የበጀት ብክነት በማጋለጥ ላይ ነው፡፡

የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ግዥና ፋይናንስ ንብረት አስተዳደር ደጋፊ የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ሰለሞን እጅጉ ብስክሌቶቹ ታሽገው ያለስራ መቀመጣቸውን አምነዋል።

ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተብለው የተገዙት ብስክሌቶች ለግዥ በተጠየቀው ናሙና መሠረት ባለመሆናቸው የጎደሉ እቃዎቸ እና የጥራት ችግር ስላላቸው አልተረከብነውም።ብስክሌቶቹ ለገጠርም ሆነ ለከተማ መንገዶች እንደማይሆኑም አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ለአቅራቢው አካል ብስክሌቶቹ የተሰጣቸውን መስፈርት ባለማሟላታቸው እንዲያነሱልን ብንጠይቅም ከአራት ዓመታት በላይ ያለጥቅም እንዲቀመጡ ተደርገዋል ይላሉ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ብስክሌቶችን ለሶስት ዓመታት እየጠበቁ ለሚገኙ 8 የጥበቃ ሠራተኞች ወርሃዊ ክፍያ እያወጣ ነው። አሁንም ብስክሌቶቹን ከአባይ ማዶ ላስቀመጡበት መጋዘን እንዲከፈል መጠየቃቸውን አቶ ሰለሞን ገልጸውልናል ፡፡

የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን የስራ ጫና መቀነስ ባለመቻሉ እንቅፋት ገጥሞታል። ተለዋጭ ብስክሌቶች እንዲመጡም ሆነ ፈጻሚዎቹን መክሰስ የሚችለው የፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በመሆኑ መቸገራቸውን የስራ ሂደት ኃላፊው ተናግረዋል ።

12 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው ብስክሌቶች ለምን ተገዙ? ጥቅም የማይሰጡ ከሆነስ ለምን የጥበቃና የኪራይ ወጭ ይወጣባቸዋል? ጥቅም ላይ ለማይውሉ ብስክሌቶች በሚደረጉ ወጪዎች ለምን አዳዲስ ብስክሌቶች መግዛት አልተቻለም?

ሚኒስቴር መ/ቤቱ ጥቅም የማይሠጡ ብስክሌቶች ከሆኑ አስመጪውን በፍርድ ለመጠየቅ እስከአሁን ለምን ዘገየ? የሚሉትን በቀጣይ ዘገባዎቻችን የሚዳሰሱ ይሆናል።

ዘጋቢ፡-ግርማ ተጫነ

Share.

About Author

Leave A Reply