ከ700 በላይ ተጠርጣሪዎች በላይ በቁጥጥር ስር ውለዋል – ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በአዲስ አበባ ሰሞኑን ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ሁኔታ ላይ ገለጻ አድርጓል፡፡

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዎች ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ እና ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ናቸው ማብራሪያውን የሰጡት፡፡

ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ የኤፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ወቅት ጀምሮ በርካታ የለውጥ ተግባራት ስለማድረጋቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም በውጭ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸውን፣ እስረኞች መፈታታቸውን፣ የመገናኛ ብዙኃን በነጻነት እንዲቀሳቀሱ ስለማድረጋቸው፣ ምጣኔ ሃብታዊ ማሻሻያዎች ስለመተግበራቸው ለዲፕሎማቶቹ አብራርተዋል፡፡

ይሁንና የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰው በቡራዩና አካባቢው የተከሰተው እኩይ ተግባርም ይህንን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

በዚህም የ25 ሰዎች ህይወት ማለፉንና በርካታ ንብረት መውደሙንም ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ይፋ አድርገዋል፡፡

ወይዘሮ ሂሩት የፌደራል፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ፖሊስ በጋራ በመቀናጀት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ባከናወኑት ተግባርም ከጉዳዩ ጋር በቀጥታ ግንኙነት አላቸው የተባሉ ከ700 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አብራርተዋል፡፡

ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖችም መንግስትና ህብረተሰቡ በጋራ በመቀናጀት የምግብ የመጠለያ እና የአልባሳት እያደረጉ መሆኑን አንስተው ከተፈናቃዮች መካከልም የተወሰኑት ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በአዲስ አበባ በነበረው ሰልፍም በርካታ ዜጎች ሐሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ መግለጻቸውን አንስተው ሆኖም ከጸጥታ ኃይሎች መሳሪያ ለመንጠቅ የሞከሩ አምስት ግለሰቦች ህይወት ማለፉንም ገልጸዋል፡፡

ከሚኒስትር ዴዔቷ ገለጻ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ዲፕሎማቶቹ የተጀመረውን ለውጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ለጋዜጠኛች ገልጸዋል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply