ኳስ ሜዳ፤ እውነታን በልጅነት የተጋፈጥንበት መንደራችን (መሰረት ደሞዜ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

አንዳንዴ ሰላም ሲሰማኝና መንፈሴ ዘና ሲል አያሌ ትዝታዎች ወደ አዕምሮዬ ጓዳ ይዘልቃሉ። ከልጅነት እስከ ኮረዳነት እድሜዬ የወጣሁት የወረድኩት… የወደቅሁት የተነሳሁ፣ ያጣሁት ያገኘሁት ሁሉ እንደ ዥረት ውሀ ቀስ እያሉ ወደ ስሜቴ ይዘልቃሉ። በዚህ ግዜ ዥረቱን በምናቤ ተከትዬ ትዝታዬን አንድ በአንድ አጣጥማለሁ።…….በአስገራሚው ፈገግ እያልኩ፣ በአስቂኙ እየሳቅሁ፣ በሚያስከፋው ትክዝ ቡዝዝ እላለሁ…

ዛሬ ደግሞ ዥረቱ ወደ አዕምሮዬ ጓዳ ካመጣቸው ትዝታዎች የልጅነት ሕይወት በኛ ሰፈር እንዴት እንደነበር ደጋግሞኛልና እነሆ በረኸት ልል ፈለኩ…

እነሆ!!!….

አዲስ አበባ ውስጥ ኳስ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ነው ተወልጄ ያደኩት። ኳስ ሜዳ የአራዳዎቹ መንደር።…… ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ስማቸው ገናና ከሆኑ ሰዎች መካከል እንጥራ ብንል አብዛኞቹ ከዚሁ ከእኔ መንደር የተገኙ ናቸው። ሌላውን ሁሉ ትተን ቴዲ አፍሮን ብቻ ማንሳት በቂ ማስረጃ ይመስለኛል።

ብዙ ሰው ይገርመዋል። የዛ ሰፈር ልጆች ትለያላችሁም ይሉናል… ነገር ግን ይህ ሌላ ምንም ሳይንስ የለውም። የዚያች መንደር ልጆች ህፃን ሆነን ጀምሮ የዓለምን እውነት ስለምንጋፈጥ ብቻ ነው።

ሰፈራችን አብዛኛው መኖሪያ ቤት ጠበብ ጠበብ ያሉ በመሆናቸው ለእናቶቻችን የሚቀለው ከቤት ይልቅ ውጭ ሆነን ብንጫወት ነው። በኔ ግዜ እኛ ሰፈር ከቤት አትወጡም የሚባሉ ልጆች እጅግ ጥቂት ናቸው። ውጭ ስትውል ግዜህን የምትገልባቸው ብዙ ትዕይንቶችን ትፈጥራለህ። ከሰፈር ልጆችህ ጋር ስትውል ኮንፍሊክት ሪዞልዊሽን ትማራለህ… አልባሌ ፀባይ ካሳየህ በተረብ ትታረማለህ ካስቸገርክ ጉልቤው ይጠፈጥፍህና ስርኣት ትይዛለህ።

በልጅነትህ የምታሳልፋት እያንዳንዷ ነገር ስንቅ ናት። ስትጎረምስ እየመነዘርክ ትኖረዋለህ… መሰላቸትን ያጠፋልሃል… ዓለምን መጋፈጫ ብልሃት ያቀብልሃል… ወዳጄ ስለ ህይወት የምትማረው በመፅሐፍ ብቻ አይደለም… በፊልምም በትምህርትም አይደለም… ከሰው ጋር በምታሳልፈው ነገር ነው። ከሰው መዋል ነው አይን የሚከፍተው። እኔ ልጅነቴን አጣጥሜ ነው ያሳለፍኩት። በጨዋታም በቻሌንጅም። የትም ሄጄ ከሰው መግባባት ከብዶኝ አያውቅም… ሰውን እንደአመሉ መያዝም ጭምር ያው አመል ካለው ማለቴ ነው ሃሃ የህይወት መስመር የሚሰጠኝን ሁኔታ እንደአመጣጡ መቀበል አይከብደኝም። ይህ ልጅነቴ ላይ ያሳለፍኳት እያንዳንዷ ነገር ተደምራ የሰጠችኝ ስጦታ ነው።

በኔ ሰፈር በተለይ ክረምት ላይ ከምናደርጋቸው በርካታ ነገሮች ማለትም የኳስ ግጥሚያ… የሩጫ ውድድር… ድል ያለ የሰርግ ዝግጅት (ብዙ ግዜ ሙሽራ እንሆን ነበር የዕቃቃ ባሌ ጋር ስንጎረምስ ነው የተስማማነው የማንጣላበት ግዜ ትንሽ ነበር ሃሃ)… ተሰብስቦ የባጥ የቆጡን እያወሩ መሳቅ… አረ በድንጋይ ቆፍረን ሰርተን ገበጣ ሁሉ እንጫወት ነበር። ግን ግን ሁሌም የሚያስደምሙኝ ሁለት ነገሮች ነበሩ። አንዱ የምናዘጋጀው የሙዚቃ ዝግጅት ነው።

‘ቁራሌው ባንድ’ ብለን የምንጠራው ዝግጅት ሲኖረን የሚፈጠር ባንድ ነበረን። ከቻልን ጄሪካን ቆርጠን በእንጨት ሰክተን ጃስ እንሰራለን ካልሆነ የአንዱን ሳፋ ደብቀን ወስደን በዱላ እየደበደብን ጃስ እናረገዋለን። ግራ እጁን በቀኝ እጁ የሚነካካ ጊታሪስት አይጠፋም። ሁሌም ግን ጃስ የሚመታልን በቅፅል ስሙ ግንቤው የምንለው ጓደኛችን ነው። የሱ የዘፈን ተራ ሲደርስ ማን ይቀበለው እንደ ነበር ዘነጋሁት። ብቻ ዝግጅት ያለ ቀን በየቅያሱ ባለ የቆርቆሮ አጥር ላይ በከሰል እና ከተገኘ በቾክ ማስታወቂያ ይፃፋል። ‘ ነገ የሙዚቃ ዝግጅት ስላለ የምትፈልጉ ኑ መግቢያ የሜታ ከረሜላ መጥቀለያ እና ማስቲካ መጠቅለያ ነው’

እነዚን ያልያዘ አይታደምም መንገድ ላይ ስለሆነ እንዳያዩ አባራሪ አንድ ሰው ይመደባል። ግን ብዙ ሳቅ ስለነበረው ሁሉም ጩጬ ይሳተፋል። በግዜው የከረሜላው ሽፋን የሌለው ስገዛ እከፍላለሁ ብሎ ይገባል። ይከፍላልም።

በዝግጅቱ ላይ ዘፋኝ አለ… መድረክ መሪ አለ… ፊልም የሚሰሩም አሉ።

እኔ ግምቤው ሊበን ዘፋኝ ነበርን መድረክ ማንቼ ነበር የሚመራው ነፍሱን ይማረውና… ፊልም ቁንዝርና ሊበን ይሰራሉ።

ሁልግዜም ዝግጅቱ ይጠናቀቅ የነበረው በፊልም ነው። ቁንዝርና ሊበን ፊልም እንስራ ይሉና ይነሳሉ። ሁሌም የሚሰሩት አክሽን ፊልም ነው። ለፊልም ብለው የጀመሩት ድብድብ የእውነት ይሆንና እነሱን ስንገላግል ጨዋታው ይበተናል ሃሃሃ

ሌላው የማልረሳው አንድ ቀን ተሰብስበን ስናወራ ግምቤው እኛ ቤት ማታ የፋፋ ገንፎ በላን ብሎ አለን። እስኪገባ ወደ ቤት ጠበቅነው። ከዛ በቾክ በሚታይ ቦታ ላይ

በ…. ቀን…. ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰኣት ላይ እነ ግምቤው ቤት የፋፋ ገንፎ የመብላት ስነ ስርኣት ተካሄደ ሃሃሃ’ ብለን ፃፍን። ፀሐፊዋ እኔ ነኝ። ፅሑፉ ስለሚያምር አላፊ አግዳሚው እያየ እየሳቀ ያልፋል። ከዛ የግንቤው ወንድም አይቶት ቤት ሲገባ የቤትህን ገመና ደጅ የምታሰጣው ብሎ ጠፈጠፈው። ግንቤ የፃፈው ቁንዝር መስሎት ጠበቀው። የእነ ቁንዝር ሽንት ቤት ከግቢያቸው አልፎ እነ ግንቤው ግቢ ነበር እና ሲገባ ጠብቆ መጣበት። በሩ ስላረጀ ከሩቁ ሰው አለ ካላልክ ትታያለህ። እና ቁጢጥ ብሎ እያለ መጣበት። ድንጋይ ይዟል። ና ውጣ አንተ ቁንዝር ሲለው ምን ቢለው ጥሩ ነው አረ ግምቤው እሺ አንዴ ካካዬን ልጨርስ ሃሃሃ አትጨርስም ውጣ ሃሃሃ ሲጨቃጨቁ እትዬ መጥተው አባረሩለት….

ለዛሬ ይብቃን

Share.

About Author

Leave A Reply