ኻርቱም፤ ሱዳን ከአሜሪካ የሽብርተኛ ዝርዝር ልትወጣ ነው

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሱዳን ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ስልታዊ ያለችውን ሁለተኛ ዙር ውይይት ለማካሄድ ከስምምነት መድረሷን አስታወቀች። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ይህን ያመለከተው ዋሽንግተን የኻርቱም መንግሥትን ከአሸባሪነት ፍረጃ ዝርዝሯ ውስጥ ልታወጣ ነው የሚለው ዜና እንደተሰማ ነው። ከዓመት በፊትም አሜሪካ ለ20 ዓመታት በሱዳን ላይ ጥላ የቆየችውን የንግድ ማዕቀብ ማንሳቷ ይታወሳል። ሆኖም ዋሽንግተን ሱዳንን ከኢራን፣ ከሰሜን ኮርያ እና ከሶርያ ጋር አዳብላ መንግሥታዊ ሽብርን የሚደግፉ ስትል መፈረጇ መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾችም ሆኑ ባንኮች ወደ ኻርቱም ፊታቸውን እንዳያዞሩ ማድረጉን የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሱዳን ከዩናይትድ ስቴትስ በኩል ፍረጃውን ሊያስነሳላት የሚችለው ውይይት መጀመርን በደስታ መቀበሏን ብትገልፅም የመብት ተሟጋቾች ግን ጥንቃቄ እንዲደረግ እያሳሰቡ ነው። ዋና ጽሕፈት ቤቱ ኒውዮርክ የሚገኘው ሂዉማን ራይትስ ዎች ኻርቱም መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን መጣስ መቀጠሏን፤ የፀጥታ ኃይሎችም በየጊዜው ሲቪሎች ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝሩ እና ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ጥይት እንደሚተኩሱ አመልክቷል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሄዘር ናወርት በበኩላቸው ሀገራቸው ሱዳን በስብዓዊ መብቶች፣ ሃይማኖት እና የፕሬስ ነፃነት ላይ ቀጣይ መሻሻሎችን እንድታደርግ፤ የሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦትን እንድታሻሽል እና የፀረ ሽብር ትብብሯን እንድታሰፋ እንደምትፈልግ በጽሑፍ ባወጡት መግለጫ አመልክተዋል። የሱዳን ኤኮኖሚ፤ በስተደቡብ የነበረችው አካሏ ደቡብ ሱዳን ሆና ከተገነጠለች ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2011 ዓ.ም. ወዲህ እየተውተረተረ ነው።

Share.

About Author

Leave A Reply