Thursday, January 17

“ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐጺባ በደመ ኢጣልያ” /ሃይማኖት ተካ/

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ዓድዋ
ዓድዋ
ዓድዋ

በሁለት ብርጭቆ የቀዳሁትን ጭማቂ ሞልቼ አንዱን አነሳሁና ልሰጠው ወደሱ ስጠጋ…

«ምን?…ለኔ እንዳይሆን የቀዳሽው?» አለኝ እያሾፈ::

«ታዲያ ለማን ሊሆን ነው?» አጠገቡ ላስቀምጥለት ስል…
«አረ በፈጠረሽ…እንዴ? መች ሆዳችን መለሳለስ ለመደ ብለሽ ነው?…ቢጫ መጠጥ በብርሌ ነው ‘ሚያምርበት…ማለት…Sorry ለዚ የሚሆን አይናፋር አንጀት የለኝም… »

አጠገቡ አስቀምጬለት ወደቦታዬ ተመለስኩ:: እሱም መጽሐፉን መግለጽ ጀመረ:: በመሐከላችን የሰፈነውን ጥቂት ጸጥታ ድንገት በትንሹ ጀምሮ የጎላው ሳቁ አቋረጠው::

«አይ እቴጌ ጣይቱ!…ደፋርና ጀግና ሴት እኮ ነበሩ..ምን እንዳሳቀኝ ታውቂአለሽ» አለኝ ከኪሱ ውስጥ ቢያንስ ለሶስተኛ ጊዜ ተጠቅሞ ያልጣላትን ሶፍት መልሶ እያወጣ እና አፍንጫውን እየጠረገ:: «አፄ ምንሊክ የውጫሌውን ውል እንዳልተቀበሉት ለአንቶኔሊ ሲነግሩት…አንቶኔሊ ሆዬ በንዴት ወረቀቱን ፊታቸው ቀዶ ይጥልና…ጦርነቱ አይቀርሎትም…ሲያሞ ፔሪኮሎዞ…ስታይ ሞሬንዶ…ምናምን እያለ ሲዝት እቴጌአችን ደሞ ከት ብለው ስቀው…..”ስትፈልግ ጦርነቱን የዛሬ ሳምንት አድርገው በዚ ማንም አይደነግጥልህም” አላሉትም?….» እየሳቀ አልጠጣም ያለውን ጭማቂ አንስቶ ፉት አለው::

«በእውነት ሴት እኮ የጀገነችበት ነገር ሁሉ … የሆነ በቃ…ክንፍ የመሆን ሀይል አላት…ማለት…ሀገር እራሷ እኮ ፆታዋ ሴት የሆነው ሁሉን በብቃት መሸከም የሚችል አቅም ስላላት ነው….ሀገር እናት ናት…ሀገር ሁሉም ነገር ናት ሲል ነው…..ማለት…» የስልኬ ጥሪ ወሬውን አቋረጠው:: ስልኬን እያወራሁ እሱም እየተጎነጨ ያነብ ነበር:: ስልኬን ዘግቼ ሳስቀምጥ…
«በጣም የሚገርመኝ» አለ እንደማስጠንቀቂያ በአመልካች ጣቱ እየጠቆመኝ

«በጣም የሚገርመኝ: የሰለጠነ የጦር መሳሪያ እኮ በጊዜው አልነበረም:: እህእ! በቆመጥና በጎራዴ ከመከተ ትውልድ ጋ’ማ ይሄኛው በፍጹም አይነጻጸርም:: እንዴ..ስንት የቫንዳም መዓት…የሸዋዚንገር መአት እኮ ነበረን:: እንዴ ሃይሚ ኢትዮጵያ እኮ ለሀገራቸው በሞቱ የተሞላች ሀገር ነች:: »
የመጨረሻውን የጭማቂውን ጭላጭ አንስቶ ጨለጠና ብርጭቆውን ገጭ አ’ርጎ አስቀመጠው::
«እየውልሽ እዚ ጋ ደግሞ ሌላው ደስ ያለኝን ነገር ላንብብልሽ….እ..አፄው ዓድዋ ላይ ባገኙት ድል ተደስተው ለፈረንሣዊው ሙሴ ሞንዶን የጻፉት የምሥራች ደብዳቤ …እንዲህ ነበር ያሉት›› እንደልማዱ ብድግ ብሎ ድምጹን ከፍ በማድረግ ማንበብ ቀጠለ::

‹‹”የምሥራች! በእግዚአብሔር ቸርነት የየካቲት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዕለት ኢጣልያንን ድል አድርጌ መታሁት፡፡ በጨረቃ ሲገሰግስ አድሮ እሰፈሬ ድረስ መጥቶ ገጠመኝ፡፡ አምላከ ኃያላን ረድቶኝ ፈጀሁት፡፡ ደስ ብሎኛል ደስ ይበልህ”›› በኩራት ፈገግ ብሎ ትክ ብሎ አየኝ::

‹‹ሌላው ደግሞ ለሙሴ ሽፋኔም እንዲህ ብለው የዓድዋውን ድል ገለጹለት…
. . .”በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የእነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረግኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም”…
By the way ጦርነቱ የካቲት 23 1888ዓ.ም. ላይ ነው የተፈጸመው::» አለኝ

«ይሄ ታሪክ ነው! ለትውልድ የተረፈ ውብ ማንነት! ቀና ያደረገን ጀግንነት! በየትኛውም ዓለም በኩራት የምንዘክረው እና ስማችን የተጠራበት ዓድዋ! This is our BIG history!» የቀኝ እጁን ቡጢ አንስቶ ወደላይ እያወናጨፈ ትንሽ የተበሳጨ በሚመስል አቀማመጥ ተቀምጦ ፊቱን በመዳፉ ያሻሽ ጀመር::

«ገባኝ…
“ባሕር ዘሎ መምጣት ለማንም አትበጅ
እንደ ተልባ ስፍር ትከዳለች እንጂ
አትረጋምና ያለተወላጅ፡፡”
ሲባልም ሰምቻለሁ» አልኩት ንዴቱን ለማብረድ::

«ምን ዋጋ አለው…የሚያረጋ ምን አለና» በትካዜ በረጅሙ ተነፍሶ ብድግ አለ::
«ልትሄድ ነው?» አልኩት ለማረጋገጥ «አዎ ይሄን ያህል በግድ ካወራሁሽ ይበቃል……ግን…የአብይ ጾም ሲጠናቀቅ ለትንሣኤ ምን እንደሚወረብ ታውቂአለሽ?» አለኝ ቀዝቀዝ ብሎ

«አዎ አልኩትና ወረቡን በዜማ አልኩለት…”ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ : ተሐጺባ በደመ ክርስቶስ…» ፈገግ ብሎ አየኝና

« ከአድዋ ድል በኋላ አፄ ምኒልክ ወደሀገራቸው ሲመለሱ ካህናቱ ልብሰ ተክህኖአቸውን ለብሰው ጃንሜዳ ተሰብስበው በመጠበቅ ይሄንኑ ነበር ለአፄው የዘመሩላቸው::» አለኝ:: ነገሩ ትንሽ ግር ስላለኝ…

«እንዴት…ማለት…» አልኩት:: እሱም በተራው በዜማ ነገረኝ::

‹‹…”ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ : ተሐጺባ በደመ ኢጣልያ”…እያሉ ነዋ…የላይኛው በፋሲካ እለት “መሬት በክርስቶስ ደም ታጥባ ደስታ አደረገች ሲሆን…ይሄኛው ደግሞ በጣልያን ደም ታጥባ ደስታ አደረገች ይሆናል…ገባሽ?»

አለኝና መጽሐፉን ይዞ ወደበሩ ሲራመድ ከተቀመትኩበት ተነሳሁ::

‹‹አመሰግናለሁ…መልካም እረፍት…መልካም የድል በዓል» ብሎኝ ዞር ሳይል መጽሐፉን ዘርግቶ መንገዱን ቀጠለ:: እኔም በሩን ዘግቼ የጠጣበትን ብርጭቆ እያነሳሁ ስላወራኝ ታሪክ ማሰብ ጀመርኩ::

ዓድዋ…ዓድዋ…ዓድዋ…..የጥቁር ሕዝብ ኩራት

Share.

About Author

Leave A Reply