Thursday, January 17

“ወንበርህንማ ጥለህ መጥተሀል” ታሪኩ ደሳለኝ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ስሟ የፋሽስት ‘ለጋሲ’ ሆኖ በቀረው ፒያሳ ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ ነው። ኮራ-ጀነን ብሎ ወደ ጠላት ምሽግ ሊገስገስ ሁሉት እግሮቹን በዝላይ መልክ ከፍ ባደረገው ፈረስ ላይ በክብር ከተቀመጡት እምዬ ምንሊክ ሀውልት ጀምሮ እንደ ሙዚየም በአያሌ ቅርሶች በተሞላቸው አራዳ ምን ጠፍቶ?! መሀመድ ሰልማን “ለመሞትም ለመኖርም ስታስብ ፒያሳ ሂድ” እንዲል፤ ዛሬ ዛሬ ወደ ታሪክነት በተቀየሩት ውቤ በረሃ ያልጨፈረ፣ በገብረትንሳይ ኬክ ቤት ያልተደስተ፣ በመኮንኖች ጣፋጭ ባቅላቫ ሀሴት ያላደረገ፣ በጥንታዊ ቤቶቿ ያልተገረም፣ በጊዮርጊስ ሜዳ ኳስ ያልተራገጠ-ሲሸነፍ በንዴት ያልተደባደበ … ያዱ-ገነት ፍሬ ነኝ ብሎ እንዳያወራ ገስጨው፣ ወደ አንድ የግንቦት ሃያ ፍሬ ገጠመኝ አልፋለሁ።
ነገሩ የተከሰተው የመብራት ኃይል መ/ቤት ባለበት ህንፃ ስር በሚገኝ፣ የጀበና ቡና ያማረው ሰው አረፍ ብሎ አርካታን ከሚጎናፀፍበት ኮሪደር ስር ነው። በውስጡ ያሉት በርጩማ ወንበሮች ተደላድሎ ለመቀመጥ ሳይሆን አረፍ ብሎ አንድ ስኔ ቡና አጣጥሞ እብስ ለማለት ብቻ የተዘጋጁ ይመስላሉ። ሰው ይገባል ሰው ይወጣል። ዱካዎቹ በሙሉ በደንበኛ ተይዘዋል። ከፊት-ለፊቴም አንድ ሰሞን በኢቲቪ-ዜና ሲጨበጨብለት፣ በኢንተርቪዎቹ ሲቀላምድ፣ በዶክመንተሪ-ፊልም ሽንፈትን ሲሰብክ፣ በአንዳንድ ነዋሪዎች አስተያየት “ትልቅ-ድል” ተብሎ ሲወደስለት… ደጋግሜ ያየሁት ሰው ተቀምጦ ያዘዘው ቡና እስኪቀርብለት ይጠብቃል። በዚህ መሀል የእጅ-ስልኩ በትግርኛ ሙዚቃ ተንጣጣች፤ “ሀሎ” ብሎም መልስ ሰጠ፤ የሚያዳምጠው ድምፅ ጠርቶ አልተሰማውም፣ አሊያም ከደህንነት ቢሮ ተደውሎለት በምስጢር ለማወራት ፈልጎ ይሆን ለይቼ ባላረጋግጥም “ሀሎ፣ ሀሎ…” እያል ከወንበሩ ተነስቶ ከቅራቢያዬ ራቅ ብሎ ሄደ። እኔም ትኩረቴን ወደ ቡናዬ መለስኩ። ይሄኔም አንድ ሸመገል ያሉ ሰው መጥተው ከተለቀቀው በርጩማ ላይ ተቀምጡና ቡና ከጤናዳም ጋር አዘዙ። ግና ያዘዙት ከመቅረቡ በፊት ሰውዬው ተመልሶ በመምጣት ከጆሮው ላይ ስልኩን እያወረደ ሽማግሌውን እንዲህ አላቸው፡- “ይህ ወንበር የኔ ነው ተነሱልኝ”
እርሳቸውም አንገታቸውን ቀና አድርገው ለአፍታ-በአሽሟጣች አይን ከገረመሙት በኋላ በመልስ-ምት አስገቡለት፡-
“ወንብርክንማ በረሃ ጥለህ መጥተሀል” ። ሃሃሃ….።
ሰውዬው በድንጋጤና በሀፍረት የሎጥ ሚስትን መሰለ፤ ቃል-ሳይተነፍስም እንደ ሙታን ፀጥ አለ፤ ግዑዝ ሆነብኝ፤ ከጥቂት ሰኮንዶች በኋላም አመዳይ የተነዛበትና እንደ ኮቸሮ-ክው ያለ ፊቱን ይዞ፣ አንገቱን እንዳቀረቀረ ሹልክ ብሎ ውልቅ አለ። ይህ ሰው የዳሓሚት ዋና፣ እንዲሁም የአርበኞቹ ግንቦት 7 ምክትል ሊቀ-መንበር የነበረውና የትግል ጓዶቹን ተስፋና ህልም ገድሎ፣ ቃሉን አጥፎ… እጁን ለኢህአዴግ የሰጠው ሞላ አሰግዶም ነው።
…እነሆ ዛሬ ታሪክ ተቀይሯል። ለዚሁ ፓርቲ ጥቅም የተንበረከኩት በደላቸውንና ኃጢአታቸውን ታቅፈው በቁጭት-ሲብሰከሰኩ፣ በነዲድ የፀፀት እሳት ሲቃጠሉ፤ እስከ መጨረሻው በጀግንነት የዘለቁት ቤተ-መንግስት በክብር ተጋብዘው አየን። እኔም እላለሁ፡- ኢትዮጵያ ሆይ በረዥሙ የጥምዝዮሽ መንገድሽ በአሳፋሪ ክህደታቸው ያቆሰሉሽ- ምድርሽ ትፋረዳቸው። በእነዚህ ሁሉ ክፉ ዘመናት የተዋደቁልሽን ደግሞ ታላቁ ታሪክሽ ዝንተ-ዓለም ይዘክራቸው።

Share.

About Author

Leave A Reply