ወደ ዓረብ አገሮች የሚሄዱ ሠራተኞችን ደመወዝ ለመወሰን የመዳረሻ አገሮች ምላሽ እየተጠበቀ ነው

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅና ሕግን የተከተለ የሥራ ጉዞ እንዲደረግ ለአምስት ዓመታት ታግዶ የቆየውን የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት ጥቅምት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የተጀመረ ቢሆንም፣ ወደ ዓረብ አገሮች የሚሄዱ የቤት ሠራተኞች ደመወዝ ምን ያህል መሆን እንደሚገባው መንግሥት ለቀጣሪ አገሮች ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

የሥራ ሥምሪቱ ሕጋዊ መንገዱን ተከትለው ፈቃድ በተሰጣቸው 144 የውጭ አገር የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በኩል ብቻ የሚሠራ መሆኑን፣ አስፈላጊውን የጤና ምርመራ ለማድረግ በተመረጡ 66 የጤና ተቋማት ተመርምረው ብቁ መሆናቸው የተረጋገጠ ብቻ እንደሚሄዱ ተገልጿል፡፡ ይኼም የሚሆነው በአዋጅ ቁጥር 923/2008 ላይ በተደነገገው መሠረት መሥፈርቱን የሚያሟሉ ብቻ መሆናቸውን፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሒሩት ወልደ ማርያም (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ የሁለትዮሽ ስምምነት በፈጸሙት ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኳታርና ጆርዳን ብቻ ዜጎችን መላክ እንደሚቻል፣ የተቋረጠው የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት መጀመሩንም ያበሰሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ደመቀ ለአምስት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት መጀመሩን ከማብሰር ባለፈ አንዲት የቤት ሠራተኛ በምን ያህል የወር ደመወዝ መቀጠር እንዳለባት በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባይገልጹም፣ መንግሥት የአንድ የቤት ሠራተኛ ደመወዝ ከ300 ዶላር በላይ መሆን እንዳለበት በመግለጽ ለቀጣሪ አገሮች ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

የመንግሥት አካላት በኢትዮጵያ የሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር በኩል ውይይት በማድረግ የደመወዛቸው መጠን ከ300 ዶላር በላይ እንጂ ከዚያ በታች መሆን እንደሌለበት፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኤጀንሲዎችና ኩባንያዎች በአገራቸው ሥራ ሚኒስቴር በኩል የሚሰጡትን ምላሽ መንግሥት በመጠባበቅ ላይ መሆኑንና በቅርቡ ምላሽ እንደሚሰጥ እየተጠበቀ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ከዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥው የነበሩትና በሳዑዲ ዓረቢያ የኩባንያዎች ኃላፊ መሆናቸው የተጠቆመው ሚስተር ሳኦድ ናሐር አልባዳህ አልሙጣሪ፣ የቤት ሠራተኞች የወር ደመወዝ 850 ሪያል እንዲሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መስማማታቸውን፣ አሁንም የኢትዮጵያ መንግሥት በዚያው ሐሳቡ መፅናቱን በመግለጽ ከእውነት የራቀ መረጃ በተለያዩ ድረ ገጾችና የመገናኛ ብዙኃን እየገለጹ መሆኑን፣ የውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ መዝገቡ አሰፋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት በኩል ደመወዝን በሚመለከት ምንም የተገለጸ ነገር እንደሌለ የጠቆሙት አቶ መዝገቡ፣ የጎረቤት አገሮች የኬንያና የኡጋንዳ ዜጎች ከ1,200 እስከ 1,300 ሪያል እየተከፈላቸው፣ ኢትዮጵያውያን 850 ሪያል ሊከፈላቸው እንደማይገባና ለመሄድ ያሰቡ ዜጎችም ሆኑ ላኪ ኤጀንሲዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ ግለሰቡ ባለፈው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለመፈራረም ያደረጉትን ድርድር፣ መጀመርያ ሕጋዊ ስለመሆናቸው ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ማረጋገጫ ሰነድ እንዲያቀርቡና እውነተኛ ኤጀንሲዎች መሆናቸው ሲረጋገጥ ውል እንደሚፈራረሙ የጊዜ ገደብ በማስቀመጥ መለያየታቸው ተገልጿል፡፡ ይሁንና በስምምነታቸው መሠረት ሊፈጽሙ ባለመቻላቸው ጊዜያዊ ስምምነታቸውን መሰረዛቸውን በወቅቱ እንዳሳወቁ የዓረብ አገሮች ኤጀንሲዎች ለመመልመያ፣ ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለኢንሹራንስ፣ ለትኬት፣ ሌሎች ወጪዎችና ለኮሚሽን ከሁለት ዓመት ዋስትና ጋር መክፈል የሚፈልጉት 900 ዶላር ብቻ መሆኑን በመግለጻቸው አለመስማማታቸውንም አክለዋል፡፡

የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 923/2008 መሠረት፣ የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አገልግሎትን በብቃት ለማስተናበር አዲስ አደረጃጀት መፍጠሩን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡ ከፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገርና ከዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት (አይኤልኦ) ጋር በመተባበር፣ ሙሉ ዝግጅት መደረጉንም አክለዋል፡፡ ሥራውን ቀልጣፋና አስተማማኝ ለማድረግ ከአጋር ድርጅቶች በተገኘ የበጀት ድጋፍ ኢትዮ ማይግራንት ዳታ ቤዝ ሲስተም ዲዛይን መደረጉን፣ የውጭ አገር ሥራ ተሰማሪዎችን ሙሉ መረጃ ክትትል ማድረግ እንደሚቻል ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡ ለሠራተኞቹ በሦስት የሥራ መስኮች ካሪኩለም ተዘጋጅቶ ሥልጠና እየተሰጠ፣ ከ60 በላይ ሥልጠና የሚሰጥባቸው የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት መለየታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ~ ሪፖርተር

Share.

About Author

Leave A Reply