ወጣቱ የደበብ አፍሪካ ፖለቲከኛ ጁሊየስ ማሌማን ተዋወቁት South African young politician Julius Malema

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ያሳደገውንና ለአመራር ያበቃውን ፓርቲ ረግጦ በመውጣት መልሶ የጎን ውጋት የራስ ምታት የሆነው የደቡብ አፍሪካው ስመ ጥር የተቃዋሚ መሪ – ጁሊየስ ማሌማ

ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ሀገሪቱን በአመታት ትግል ከአፓርታይድ አገዛዝ ነጻ ካወጣት ANC ይልቅ የወጣቱ የተቃዋሚ መሪ ጁሊየስ ማሌማ ስም ይበልጥ የገነነ ይመስላል።

በጉልበት ስራ በምትተዳደረው እናቱ እጅ ያደገው ማሌማ የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ ፓርቲን የተቀላቀለው ገና የዘጠኝ አመት ጨቅላ ሳለ ነበር። እድሜው ለአቅመ አዳም ሳይደርስ የሀገሩን ፖለቲካ ማፍተልተል የጀመረው ይህ ታዳጊ በዚህ ግዙፍ የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የአመራር ስፍራ ሲይዝም እንዲሁ እድሜው ለጋ ነበር።

እ.ኤ.አ በ2009 አመተ ምህረት ማሌማ የ ANC የወጣቶች ክንፍ ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ። በዚሁ የስልጣን እርከን ለአራት ተከታታይ አመታት ያገለገለ ቢሆንም ወጣትነቱ ተጨምሮበት የማሌማ የለውጥ ጥያቄ እጅግ ከፍ እያለ ሲመጣ በፓርቲው አመራሮች ዘንድ ደግሞ “ፓርቲውን” የመናጥ ፍርሀት ነገሰ።

ማሌማ ANC ለድሀ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የገባላቸውን ቃል ተግባራዊ አላደረገም። የእርሻ መሬት ከነጮች እየተቀነሰ ወይም እየተነጠቀ ለጥቁሮች ለማዳረስ የታቀደው የፓርቲው አላማም ግቡን አልመታም እያለ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ማንሳት ጀመረ።

በዚህ የለውጥ ጥያቄዎቹ ሳቢያም ማሌማ እ.ኤ.አ በ2012 ከANC ተባረረ።

ይሁንና ጁሊየስ ማሌማ ገና በማለዳ አፉን የፈታበትንና አምሮውን ያሟሸበትን የደቡብ አፍሪካ ፖለቲካ ከANC በመባረር ሰበብ እስከወዲያኛው ሊሰናበት አልፈቀደም።

እንዲያውም ይግረማችሁ ሲል ከፓርቲው ተባሮ አመት ሳይሞላው ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ (የኢኮኖሚ ነጻነት ተጋዳዮች) EFF የተሰኘ ፓርቲ መሰረተ።

ራሱን “The Son of the Soil” ወይም (የሀገሩ ወንድ ልጅ) በማለት የሚጠራው ጁሊየስ ማሌማ አዲሱ ፓርቲው ተመስርቶ ገና ከጅምሩ የወጣቶችንና የበርካታ ደቡብ አፍሪካውያንን ቀልብ መሳብ ጀመረ።

እንድያውም የህዝቡን ጥያቄ በማንገብ አጀንዳ ፈጣሪ በመሆን ግዙፉን ANC ን ከደቡብ አፍሪካውያን ልብ ውስጥ እያወጣ በምትኩ EFF ተወዳጅነቱን እያስፋፋ ይሄድ ጀመረ።

በተመሰረተ በአመቱ በ2014 በተካሄደው ህዝባዊ ምርጫ EFF ከ6 ከመቶ በላይ ድምጽ በማግኘት ጉድ አስባለ። በቀጣዩ አመት በተደረገው የከተማ ምክር ቤት ምርጫም ተቀባይነቱን አሳድጎ ፓርቲው የስምንት ከመቶ ድምጽ አግኝቷል።

“በዚህም አለ በዝያ ጥቁሮች መሬታችንን በሰላማዊ ወረራ መልሰን እንይዛለን” በሚለው አቋሙና የሀገሪቱ ፖለቲካ ድሆችን በመደገፍና ለድሆች በመቆርቆር ላይ መመስረት አለበት” በሚለው ፍልስፍናው የማሌማም ሆነ የፓርቲው ዝና ከፍ እያለ ሄደ።

የጥቁሮች መብት ገና አልተከበረም በማለት የሚከራከረው ማሌማ “አፍሪካውያን ዛሬም በቅኝ ገዢዎች ገመድ እንደታሰር ነን። ሲል ይደመጣል። በተለይም አፍሪካውያን አንድ ፓርላማ፣ አንድ ፕሬዚዳንት እንጂ ሀምሳ አራት ሀገር አያስፈልገንም ይላል። “እነዚህ ድንበሮች የቅኝ ገዢዎች እንዳንስማማ የፈጠሩልን በመሆኑ ልንሰርዛቸውና አንዲት ሀገር ልንመሰርት ይገባል በማለት በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና የትምህርት ተቋማት በመሄድ ወጣቶችን ይቀሰቅሳል።

በአንጻሩ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት በተደጋጋሚ ያብጠለጥላል። የአፍሪካ ህብረት ይላል ማሌማ “ወዴት መሄድ እንዳለበት የማያውቅ ህልም የሌለው ድርጅት ነው።” እንድያውም ህብረቱ እከከኝ ልከክልህ በማለት እርስ በእርስ የሚሸነጋገሉ ወንድማማቾች የተጠራቀሙበት እድር እንጂ አፍሪካን ወደ አንድ የሚያመጣ ዋጋ ያለው ነገር አይደለም” በማለት ይተቻል።

የሰላሳ ስምንት አመቱ ወጣት ጁሊየስ ማሌማ በቅርቡ በበርካታ የሙስና ክሶች ሳቢያ ስልጣን የለቀቁትን የሀገሪቱን ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በተደጋጋሚ ሪፖርት ለማቅረብ በሚመጡበት ወቅት “ይህ ሰው እዚህ አዳራሽ ውስጥ የመገኘት መብት የለውም፣ እንዲናገርም ሊፈቀድለት አይገባም” በማለት ከሌሎች የፓርቲው የፓርላማ አባላት ጋር በመሆን በሚያሰሙት ተቃውሞ በተደጋጋሚ እየተጎተተ ሲወጣ ታይቷል።

ብዙ ጊዜ የአፍሪካ ፖለቲከኞች በትረ ስልጣን እስኪጨብጡና ወንበር እስኪያደላድሉ ለህዝባቸው የማይገቡት ቃል የማይነድፉት እቅድ የለም። ወጣቱ የደቡብ አፍሪካ ፖለቲከኛ ጁሊየስ ማሌማም በሚመራው ፓርቲውም ሆነ በግሉ የአፍሪካ መሬት የጥቁር አፍሪካውያን ነው፣ አፍሪካም አንድ ሀገር ነች የሚል አቋም ያንጸባርቃል። ይህንም ተግባራዊ ለማድረግ ፓርቲው EFF በትጋት እንደሚሰራ ይገልጻል።

ይሳካ ይሆን? … እድሜ ይስጠን!

Share.

About Author

Leave A Reply