ዕርቀ ሰላም አስመልክቶ የወጣ መግለጫ (ውጭ ሀገር ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ከሚመራው በስደት ላይ ከሚገኘው ከሕጋዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያናችንን ዕርቀ ሰላም አስመልክቶ ሐምሌ 5/2010 ዓ.ም የወጣ መግለጫ።

በመላው አለም ለምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ካህናትና መመናን እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በሙሉ፤

ጥንታዊት፤ ሐዋርያዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ የሆኑ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ማለትም እምነትን፤ አንድነትን፤ ፍቅርን፤ ሰላምን፤ሥነ ጥበብን፤ኢትዮጵያዊነትን፤ታሪክን፤ባሕልንና ቋንቋን ለትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ያበረከተችና በማበርከት ላይ የምትገኝ ታላቅ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች ለሁላችንም ግልጽ ነው።

ሆኖም ለአለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት በወያኔ አስገዳጅነት በተፈጠረው የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ምክንያት ከላይ የተጠቀሱትን መልካም እሴቶችን እንድታጣ የተደረገ ከመሆኑም በላይ ዘመን ተሻጋሪ የሆነችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ ከማይቻልበት አደጋ ላይ እንደደረሰች ሁሉንም ከልብ የሚያሳዝን ከባድ ፈተና ነው።

በመሆኑም የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ጉዳይ ያሳሰበውና በበጎ ፈቃደኛነት የተቋቋመው የሁለተኛው ዙር የሰላምና አንድነት ኮሚቴ በሁለቱም ሲኖዶሶች መካከል ያለውን የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት በሰላም እንዲፈታ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሲገለጽ የቆየ መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው።

ስለሆነም በሁለተኛው ዙር የሰላምና አንድነት አስተባባሪ ኮሚቴ የተጀመረው በቀኖና ጥሰት ምክንያት የተለያየችውን ቤተ ክርስቲያን አንድ የማድረግ ዓላማ ከሐምሌ 12-21 ቀናት 2010 ዓ.ም.(July 19-28, 2018) የአሜሪካ ዋና መዲና በሆነችው ከተማ በዋሽንግተን ዲ.ሲ. ስለሚከናወን የቅድስት አገራችን ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሁሉንም አካል የሚመለከት በመሆኑ ያለፈው የልዩነት፤ ጥላቻና መከራ ዘመን እንዲያበቃና በአንጻሩ ሰላም፤ፍቅርና አንድነት በሀገራችን ኢትዮጵያና በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እንዲሰፍን፤ ዕርቀ ሰላሙም የተሳካ እንዲሆን ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ከተጣሰበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ለሰላም በሩን ክፍት በማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።አሁንም አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ በማድርግ ላይ ይገኛል።

ይህ ዕርቀ ሰላም የተሳካ ይሆን ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ከልብ በመመኘት ተደራዳሪ 3 ሊቃነ ጳጳሳትን ሰይሟል።

ስለዚህ የሀገራችንና የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ መላው ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚመለከት ስለ ሆነ ሁላችሁም በየአላችሁበት በሀሳብ፣በምክርና በጸሎት እንድትተባበሩ የአክብሮት ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናቀርባለን።

እግዚአብሔር አምላክ ቢተ ክርስቲያናችን አንድ ያድርግልን ሀገራችን ኢትዮጵያን ሕዝባችንንም ይጠብቅልን!!

 

Share.

About Author

Leave A Reply