ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት | በተስፋዬ ታደሰ

የኢትዮጵያ የግብይት ታሪክ እቃን በእቃ በመለዋወጥ እንደተጀመረ የታሪክ ድርሳናት ያስረዱናል፡፡ አሞሌ ጨው በኢትዮጵያና በጎረቤት ሀገራት በባህላዊ ግብይት ታሪክ እንደ መገበያያ ገንዘብ ያገለግል ነበር፡፡ የማሪያ ትሬዛ ታበር/ብር/ የተባለው የመገበያያ ገንዘብ በነጋዴዎች አማካኝነት በጎረቤት ሀገራት አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ በመግባቱ የሀገሪቱ ዋና የመገበያያ ገንዘብ ሊሆንም ችሏል፡፡ የወረቀት ገንዘብ ስራ ላይ ኢንዲውል እስከተደረገበት 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የወርቅ፣የብርና የመዳብ ሳንቲሞችን በመቅረጽ ግብይት ሲፈጸምባቸው ቆይቷል፡፡

ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ በማይቻልበት ሁኔታ በመተሳሰብና በመተዛዘን እቃን በእቃ በመለዋወጥ ባህላዊ በሆነ መልኩ ሲገበያዩ የነበሩ የጥንት ሰዎች ዛሬ በሰለጠነው ዘመን ሰልጥነናል ያልነው ሰዎች የምንገበያያቸውን ሸቀጦች ዋጋ ለማንም ሳያዳሉ በትክክል ለይተው የሚነግሩንን ዘመናዊ የመለኪያ መሳሪያዎቻችን/ሚዛኖቻችን/ ቆንጥጠን ገዥን ዋሽተው ለሻጭ እንዲያዳሉ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ሳስብ ምነው ይህ ዘመናዊነት/ስልጣኔ/ ባልመጣ በቀረብን ሊያስብለኝ ከጀለኝ፡፡ በትክክልለኛው መንገድ ህግና ስርዓትን አክብረው፣ ለወገንና ለሀገራቸው በተቆርቋሪነት የሚሰሩትን ነጋዴዎች ሳስብ ደግሞ ጥፋቱ የዘመናዊነቱ/የስልጣኔው/ ሳይሆን ስልጣኔውን ለመልካም ነገር ማዋል ሲገባን ለእኩይ ተግባር እያዋልንው ያለነው የሰው ልጆች ጥፋት ቁልጭ ብሎ ይታየኛል፡፡

በሀገራችን የኋላ ቀር ኢኮኖሚ መገለጫ ሆኖ የቆየው ባህላዊ የምርት ግብይት የሆነው /እቃን በእቃ በመለዋወጥና በአሞሌ ጨው ግብይት/ የሚካሄድበት ዘመን ካለፈ ረጅም ጊዜ ቢቆጠርም የወረቀት ብር ታትሞ ዘመናዊ ግብይት ውስጥ ገብተናል ባልንበት ዘመንም የግብይት ስርዓታችንን የሙጥኝ ያሉት ችግሮች አልጠፉም፡፡ ለአብነትም የተበታተነ የአካባቢ ገበያ፣አስተማማኝ ያልሆነ አቅርቦት፣ የመረጃ ስርጪት ውስንነት መኖር፣ ረጅም የግብይት ሰንሰለት፣ የጥራትና የደረጃ ችግር፣ አለመተማመንና በግብይት ስርዓት የማይመሩ የገበያ ተሳታፊዎች መበራከት፣ ግልጽነት የጎደለው የግብይት ሂደት፣ የምርት ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ተጠቃሽ ሲሆኑ ግብይቱን ከነዚህ ችግሮች በሙሉም ይሁን በከፊል የጸዳ እና ለነጋዴው፣ ለሸማቹና ለሀገር ሊበጅ የሚችል ለማድረግ በመንግስት ደረጃ የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች መኖራቸውም አይካድም፡፡

የሀገራችን ኢኮኖሚ ዋልታና ማገር የሆነው ግብርና ምርቶች አለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ገብተው ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን የውጭ ምንዛሪ ታገኝ ዘንድ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት ዘርግቶ አርሶ አደሩን፣ነጋዴውንና ሀገርን በየልካቸው ሊጠቅም የሚችል ግብይት መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ መንግስትም የግብይት ስርዓቱን በማስተካከል የአርሶ አደሩን ህይወትና በሀገር እድገት ላይ ለውጥ ያለጣልኛል ያለውን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ /ECX/ የተሰኘውን ዘመናዊ የግብይት ማዕከል አቋቁሞ ዘመናዊ የግብይት ስርዓቱን ከተቀላቀለ ሰነባብቷል ፡፡

በ2000 ዓ.ም ሚያዚያ ወር በ67 መስራች መደበኛ አባላት፣በ350 ተገበያይ አባላት 4.7 ቢሊዮን ብር በማገበያየት ስራውን ዳዴ ብሎ የጀመረው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዛሬ በ335 ሙሉ አባላት፣በ118 ተገበያይ አባላት 5.7 ሚሊዮን ቶን ምርት በ196 ቢሊዮን ብር በማገበያየት 10ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ሐምሌ 21 ቀን /2010 ዓ.ም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ አክብሯል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘመናዊ የግብይት ስርዓትና ጠቀሜታን አስመልክቶ እንደ ሀገር ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ግብይት በማካሄድ፣ ወጥነት ያለው የምርት ጥራት አጠባበቅ እንዲኖር፣ የምርት ጥራት አስፈላጊነት ላይ በነጋዴውም በአርሶ አደሩም ዘንድ እምነት በመፍጠር ፣ ለማክሮ ኢኮኖሚ እድገት አስተዋፆኦ ያለው ግብይት በማስፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ ከተቋቋመ 10 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምርት መቀበያ፣ የጥራት መመርመሪያ ላብራቶሪ፣ የምርት ማከማቻና ማስረከቢያ አገልግሎት የሚሰጡ 22 ቅርንጫፎችን በመክፈት ለውጪ ገበያ የሚውሉ የግብርና ምርቶችን ለሚያቀርቡ አርሶ አደሮችና አቅራቢዎች ተደራሽነቱን በማስፋት እየሰራ ይገኛል፡፡

ዘመናዊነት “ዘመናዊነት” ነውና በመልካም ጎኑ ከተጠቀምንበት መልካሙን ውጤት ይሰጠናል፡፡ የጽሁፌ መነሻም ይኸው ነበር፡፡ የምዕተ ዓመታት እድሜውን በባህላዊ ግብይት ውስጥ እቃን በእቃ ከመለዋወጥ ጀምሮ ዛሬ አለበት ደረጃ ላይ የደረሰው የሀገራችን ግብይት ወደ ዘመናዊ ግብይት ስታዲዬም ገብቶ ጨዋታውን በመጀመር ላይ ያለ እንጅ ዘመናዊነቱን ተጫውቶ አልጨረሰም፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አሰራሩን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በማስደገፍ እያንዳንዱን ግብይት በመረጃ ቋት መያዙ፣ ከምርት ቅበላ እስከ ርክክብ ያለውን ሂደት በመረጃ ቴክኖሎጂ ታግዞ መስራቱ፣ ለአገራዊ ኢኮኖሚ ጥናትና ፖሊሲ ውሳኔ የሚጠቅም መረጃ ምንጪ መሆኑ፣ ለአርሶ አደሩና ለተገበያዩ ወቅታዊ የገበያ መረጃ ማድረሱ፣ በየጊዜው አዳዲስ አሰራሮችን እየቀየሰ መተግበሩ የግብይት ስርዓታችን ወደ ዘመናዊነት ስታዲየም ገብቶ ጨዋታ በመጀመር ላይ ነው ብየ እንድናገር ያስደፈሩኝ ሰናይ ተግባራቱ ናቸው፡፡

ሆኖም አሁን የጀመረውን የዘመናዊ ግብይት ጨዋታ ተዋናዮችን በስነ-ልቦና፣ በክህሎት፣ በእውቀትና በአመለካከት በመገንባት፣ የጨዋታ ህጉን በማሻሻል፣ አዳዲስ አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመቅሰምና ወደ ተግባር በማስገባት እንዲሁም የህገ-ወጥ ግብይትን ሜዳ በማጥበብ ሀገራችንን ለዘላቂ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ የሆነውን ዘመናዊ የግብይት ስርዓት ባለቤት ማድረግ ይጠበቅበታል እላለሁ

Share.

About Author

Leave A Reply