የሁለቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የእርቀ ሰላም አመላካች ሐሳብ (መጋቤ ጥበብ መንገሻ መልኬ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ቅድመ ዓለም ከአበ ብዙኃን አብርሃም ዘመነ አበው ጀምሮ እምነት አይሁድን ከብሉይ ኪዳንን ተቀብላ መስዋዕተ ኦሪትን እየሰዋች የክርስቶስን ልደት በተስፋ ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ  የጠበቀች፣ የክርስቶስ የልደት ዜና ወይም ብሥራት ቀድሞ የድረሳት ሐዲስ ኪዳንን አምና በማሳመን ሁለት ሺህ ዘመን ያስቆጠረች በድምሩ ከሦስት ሺህ ዘመናት በላይ ሀለዎተ እግዚብሔርን አምና የተቀበለች በዓለም ቀደምት ክርስቲያናዊት ሀገር ነች።

ቀጥሎ በወቅቱ በነበሩት በአሌክሳንደርያ ሊቀ ጳጳስ አሌክሳንደር እና አሪዎስ በሚባል መናፍቅ መካከል በአሌክሳንደርያ በተፈጠረው የነገረ መለኮት ችግር፤ እንደ ኢሮፓውያን አቆጣጠር በ325 በንቂያ በተደርገው የመጀመሪያው የሊቃውንት ስብሰባ  አሪወስን በማውገዝ ለቤተ ክርስቲያን ሕልውና ለማስጠበቅ የተደነገገው መንፈሳዊ ሕግጋተ ተከትላ ከላይ የወረደውን ከድንግል የተወለደውን መንፈስ ቅዱስ የተዋሐደውን ቅድመ ዓለም የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር አንድ አምላክ ቃል ሥጋ ሆነ የሚለውን መለኮታዊ ትምህርት በተዋሕዶ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የአበው ድንጋጌን መሠረት ጠብቃና አስጠብቃ ኦርቶዶክሳዊ ክርስትናን እካለንበት ዘመን ድረስ በማስተማር ላይ ትገኛለች፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ማርቆስ አባቴ እስክንድርያ እናቴ በማለት ለአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመታት ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፤ ሊቀ ጳጳስ እየተሾመላት እንደ አንድ ሀገረ ስብከት ሆና በእምነት የቆየች ሲሆን፤ ከጊዜ በኋላ ከራሷ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ፓትርያርክ እየመረጠች መሾም ጀመረች።

የመጀምሪያው ፓትርያርክ ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ባስሊዮስ ሲሆኑ፣ ሁለተኛው ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ ሦስተኛው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት፣ አራተኛው በግፍ ለስደት የተዳረጉት ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ አምስተኛው ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ስድስተኛው  አሁን አዲስ አበባ ያሉት ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ማትያስ ናቸው።

ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ ምላተ ጉባዔ  ሙሉ ድምጽ ተመርጠው ቤተ ክርስቲያኒቱን እየመሩ ባለበት ወቅት በ1983 ዓ.ም ሕወሀት አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። ሕወሀት በቤተክርስቲኗ ላይና አማራዊ በሆነ ዘር መሠረት የሌለው ከንቱና አሳፋሪ በሆነ መልኩ በተመሠረተ የዜጎችን አንድነት የሚከፋፍል የሀገርን ልዑላዊነት ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል በማኒፌስቶ የተቀረጸ በማስረጃ የተረጋገጠ ሥር የሰደደ ጥላቻ የነበረው በመሆኑ አዲስ አበባ እንደደረሰ በቀጥታ የመጀመሪያ ዱላውን ያሳረፈው በቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ላይ መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው።

ቅዱስነታቸው መንበራቸውን እጅግ በጣም ሊቋቋሙት ከማይችል አቅም በላይ በሆነ አስገዳጅነት ለቀው እንዲወጡ ከዚያም ለስደት እንዲዳረጉ የሆኑበት ምክንያት እራሳቸው አስገድጆቻቸው በአንደበታቸው የመሠከሩት በዓለም አቀፍ ከፍተኛ የመረጃ ምንጮችና የስለላ መረቦች የተረጋገጠ ጉዳይ በመሆኑ ማንም በውሸት መጋረጃ ሸፈኖ የማያስቅረው እወነት ነው።

በወቅቱ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላቱ ፓትርያርኩ ጋር አንድ አካል አንድ አምሳል ሆነው ሕውሀት በፓትርያርኩ ላይ የሚያደርሰውን አስገዳጅነት ለቤተ ክርስቲያን ክብር ሲባል ከመጠበቅና ከመቋቋም ይልቅ ሁሉም በየድርሻው መቧደን ጀመረ። ጊዜው የእኛ ነው የሚሉት ክፍል የራሳች ቡድን፤ መሐል ሰፋሪነት ያለው ለብቻው ቡድን፤ ፓትርያርኩን የሚደገፉና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን አይጣስም የሚለው ቡድን በመሆን የየራሱን ሽኩቻ ሲያደርግ ቆይቶ፤ ዘመኑ የሰጣቸው ቡድኖች ኃይላቸው ስለበረታ መሀል ሰፋሪው ቡድን ኃይል ወደ አመዘነበት ተደምሮ ፓትርያክ በሕይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም የሚለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተጥሶ አምስተኛው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ተሾሙ።

አቡነ ጳውሎስም ጊዜው የፈቀደላቸውን ዘመን በተድላ ኖረው ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ። ይህ የግዚአብሔር ጥሪ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ መርቆሬዎስ ሕጋዊ ፓትርያርክ እኔነኝ እያሉ በየጊዜው መግላጫ እየሰጡ፣ ሊቃነ ጳጳሳት እየሾሙ እያለ በሀገር ቤት ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ እዱሉን ተጠቅሞ ውሳኔ አሳልፎ ቅድመ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ቅዱስ ፓትርያርኩን ወደ መንበረ ክብራቸው ከመጥራት ይልቅ፤ የሕወሀት ተወካዮች እነ  ኑቭረዕድ /አባ/ ኤልያስ  ባሉበት የይስሙላ ሽማግሌ በመላክ የተድበሰብሰ ሥራ ከሠሩና እርቀ ሰላሙ ሆን ብለው እንዲከሽፍ ካደረጉ በኃላ፤ አሁንም በድጋሜ ለጊዜው ቅርብ ናቸው የሚባሉት ብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ማትያስ ተሾሙ። ይህም ለቤተ ክርስቲያን የመከፋፈል ክፉ ዘመን ይበልጥ እንዲራዘም አስተዋጾዖ አደረገ።

ጉዳዩ እየሰፋ መጥቶ በሁለቱም በኩል ሊቃነ ጳጳሳት እየተሾሙ በዘመናችን የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር በሚል ለሁለት ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያንን ተከፍላ አማኙም ሆነ አገልጋይ ካህናቱ በሁለት ወገን ለመጓዝ የተገድንበት ዘመን ሲሆን፤ ቤተ ክርስቲያን እንደብራና የተወጠረችበት ምዕመናኑ የተንገላቱበት፣ የባዘኑበት፣ ያለቀስቡት ሃያ ሰባት ዓመት የሰቆቃ ዘመን ተቆጠረ።

ይህን ችግር ተረባርቦ በመቅረፍ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ ሕጋዊ  መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ከላይ እንደተጠቀሰው ሊቃነ ጳጳሳቱ በሦስት የመከፋፈል ጎራ የጠነሰሱት ግድፈት ሥር ሰዶ ሦስተኛው የማህል ሰፋሪው ሕዋስ በውጪ ሀገር አቆጥቁጦ ከገነትም ከጋሃነብም ወይም ከጽድቅም ከኩነኔም የለሁበትም  ወይም እንዳያማ ጥራው እንዳይበላ ግፋው ዓይነት «ገለልተኛ ነኝ» በሚል የፓትርያርክ ስም የማይጠራበት አደረጃጀት መሥርቶ እራሱን አቋቋመ።

ለዚህ ሕዋስም የልብ ለልብ የሰጡት አገር ቤት ከሚገኘው ቅዱስ ሲኖድስ አባላት መካከል በሽሉልክታና በመላሾ ታቦት እየባረኩ የሚሰጡ ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው። አራተኛውን ፓትርያርክ ከባለ ጊዜዎች ጋር ተደምረው ማባረራቸው ሳይቀር፤ እንደገና በውጪ ሀገር የፓትርያርክ ስም የማይጠራበት «ገለልተኛ ቤተ ክርስቲያን» ብለው አቋቋመው አሁንም የቤተ ክርስቲያን ላይ የግፍ ዘመን እንዲራዘም አስተዋጾኦ በማድረጉ እረገድ የሀገር ቤቱ ቅዱስ ሲኖድስ አባላት የሰለጠነ እጅ ያለበት  መሆኑ መታወቅ አለበት።

ሀቁ ይህ በዚህ ከዚህ በላይ በአጭሩ እንደተመለከተው ሲሆን፤ «ጊዜው ሲደርስ አንባ ይፈርስ ነውና እግዚብሔር ባልተጠበቀ ባልታሰበ መንገድ ከእድሜያቸው በላይ አርቀው የሚያስቡ፣ የታሰሩትን የሚፈቱ፣ የተበተኑትን የሚሰበስቡ፣ የተሰደዱትን የሚጠሩ የተጣሉትን የሚያስታርቁ፣ ምህረትን የሚያውጁ …..ለኢትዮጵያ ዐቢይ ሰው ላከ። ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚባሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቅላይ ምንስትር እግዚብሔር አስነሳ።

ጠቅላይ ምስትሩም የመጀመሪያ ትኩረታቸው በእምነት አብላጫ የሕዝብ ቁጥር ይዛ የምተመራውን ታሪካዊት የሆነችውን ታላቋ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ ማድረግ የመጀመሪያ አጀንዳቸው አድርገው  «በእኔ የሥልጣን ዘመን ማንም አሳዳጅ ማንም ተሳዳጅ» የለም በሚል መርህ የሁለቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የዕርቀ ሰላም ጉዳይ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው አጀዳዎች አንዱና ዋነኛው አድረገው መዘገቡት።

ሆኖም ይህን አጋጣሚ ተከትሎ አንዳንድ ሰርገው በመግባት፣ መስሎ የመቅረብ ልምድ ያላቸው ጮሌዎች በውጪ ባለው ቅዱስ ሲኖዶስ ላይ የተለመደ ማሳበቃቸውን አላቆሙም። ይህም ማሳበቅ በሀሰት ላይ የተመሠረተ ከዘረኝነት ጋር የተያያዘ የሚል ሲሆን ማሳበቁ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንደሚባለው ዓይነት ዘይቤ የሚገልጸው ነው።

በሃያ ሰባት ዓመታ ውስጥ ከአርባ በላይ የሚደርሱ የትግራይ ተወላጆች ሲሾሙ ያልተቹ አሳባቂው፤ እየሸመገሉ ለመጡት ነባር አበው ሊቃነ ጳጳሳት የውጪ የቅዱስ ሲኖድስ አባላት ጥቂት ረዳት  ከአማራው ክፍል  ሊቀ ጳጳስ ሲሾሙ ከዘር ጋር በተያያዘ ለማሳበቅ መቻላቸው ሳያሳፍራቸው አስታራቂ ሆነው አይናቸውን በጨው ታጥበው መቀመጣቸው እጅግ የሚገርም ጉድ ነው።

በውጪ ያሉ አባቶች የተወቅሱበት የዘር ጉዳይ ለምን በተመሳሳይ አካባቢ ያሉ አማሮችን ሾሙ የሚል ሲሆን፤ ነገርግን ከሌላው አካባቢ ለመሾም ተሰዳጁን ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስን በአባትነታቸው ተከትሎ ስለ ሕገ ቤተ ክርስቲያን መከበር በሀገር ቤት ግፍና በደል ለሚደርስባቸው ዜጎች ከመጮህ ይልቅ «ገለልተኛ ነን» ብለው በመቆማቸው በዚህ ምክንያት በወቅቱ ለሹመት የሚበቃውን ለይቶ ለመሾምም ሆነ ብቃት ያላቸውን መርጦ የሚያቀርብ አልተገኘም። በዚህ ምክንያት በቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ መርቆሬዎስ በኩል ቆመው ስለሕገ ቤተ ክርስቲያን ሲጮሁ ቅዱስ ፓትርያርኩን ሲራዱ የቆዩትን ብቃት ያላቸው ቆሞሳትን መሾሙ ከቶ ሃጥያት ሆኖ በአፈ ጠቦች አንደበት ሊያስወቅስና አሳልፎ ሊሰጣቸው ባልተገባ  ነበር።

ነገሩን ለማሳጠር ለሃያ ሰባት ዓመት በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው መከራና ችግር እንደተረት እያለፈ እግዚአብሔር ጊዜውን ጠብቆ ዶክተር አቢይን መሲህ አድርጎ፣ ከሁም በላይ የቤተ ክርስቲያን እርቅ ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝበ ክርስቲያኑ አንድነት ለሕዝባዊ አስተዳደር የመደመር ስሌት ወጤት ወሳኝነት ያለው በመሆኑ እርቁ ተጀምሯል።

የእርቀ ሰላሙ ጉዳይ ከአሁን በፊት ብዙ ሙከራ ተደርጎ አመርቂ ውጤት ባይኖረውም የሁለቱም ልዑካን አብረው ቅዳሴ መቀደስ እና በመጸለይ በሁለቱም በኩል ተላልፎ የነበረው መወጋገዝ ሽረውታል። ወደፊትም መወጋገዙ እንዳይኖር ገድበውታል። ይህ በዚህ እንዳለ የእርቀ ሰላሙ ጉዳይ  ከዚህ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ማተኮር ይኖርበታል የሚል ሐሳብ ለማቅረብ እንወዳለን፤

1ኛ/ ምንም እንኳን አጥፊውን ለመቅጣት የጠፋውንም ለመካስ ባይቻልም ፍርዱን ለ እግዚብሔር በመስጠት  በማውቅም ሆነ ባለማወቅ ክፉ ዘመን በፈጠረው ችግር የተነሳ ጉዳቱ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መሆኑ ታውቆ፤ ፓትርያርክ እያለ ፓትርያርክ መሾሙ ሕገ ቤተ ክርስቲያን የጣሰ መሆኑ በሁለቱም በኩል በጋራ የጋራ ችግር ሆኖ ሊታመንበት ይገባል፤

2ኛ/ የአራተኛው ቅዱስ ፓትርያርክ በኃይልና በአስገዳጅነት መሰደድ ምክንያት ለአምስተኛውና ስድስተኛው ቅዱስ ፓትርያርክ መሾም ለቤተ ክርስቲያን የሁለት ቅዱስ ሲኖዶሳት መከፈል የሃያ ሰባት ዓመት ዘመን የሁለትዮሽ ሲኖዶስ ዘመን መሆኑ ታምኖበት በሁለቱም በኩል የተሰጠው ማንኛውም አገልግሎት መንፈሳዊ የደረጃ እድገትና ሹመት ሁሉ ምንም ዓይነት መበላለጥ ወይም ተቃውሞ  ሳይኖረው በእኩል የሚዛን ተቀባይነት  እንዲኖረው ማድረግ፤

3ኛ/ ቅዱስ ዳዊት ”የሰው ልጅ እደሜው ሰባ ቢበዛ ሰማንያ ነው…” እንዳለው ሁሉ፤ ሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርክ እድሜያቸው ሰባ ዓመትን አልፎ ሰማንኛው ላይ የደረሰ በመሆኑ የመሾም የመሻር የመሳሰሉት በአረጋዊነት እድሜ አድካሚና አሰልች አጨቃጫቂ ከሆኑ የአስተዳደር ሥራዎች ተዐቅበው፤ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ምላተ ጉባዔ ላይ ሁለቱም እየተገኙ ስብሰባውን በጸሎት በመክፈት እና በመዝጋት፣ የጋራ አባታዊ ቃለ ምዕዳን፣ ቡራኬና ምክር በመስጠት እንዲሁም በየአድባራቱና ገድማቱ የሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርክ ስም እየተጠራ፤ የማይቀርበት ቀጠሮ ያለውን የመጨረሻ ጉዞ እግዚአብሔር ከሁለቱ አንዱን ቀድሞ ስኪጠራ ድረስ ምላተ ጉባዔው በሰየመው ባለሙሉ ሥስልጣን የፓትርያርክ እንደራሴ ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አስተዳደ እንዲመራ፤

3ኛ/ የውጪው ቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑት ሊቃነ ጳጳሳት በሙሉ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገር በመረጡት ቦታ አህጉረ ስብከት እንዲሰጣቸው እንዲሁም  በአዲስ አበባ መንበረ ፓትርያርክም ማረፊያ ቤት ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮች ምደባ እንዲደረግላቸው፤ በአጥቢያ አቢያተ ከርስቲያናት አስተዳዳሪነትና በልዮ ልዮ የሥራ ኃላፊነት የተመደቡት ሁሉ እንደዘሁ አስፈላጊ እንዲሟላላቸው፤

4ኛ/ በውጪው ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ በሀገር ቤት ቅዱስ ሲኖዶስ አጠቃላይ የሥራ  ሪፓርት ተደረጎ ያለው የተንቀሳቃሺና የማይንቀሳቀስ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት ታውቆ በአንድ የቅዱስ ሲኖዶስ  መንፈሳዊ አስተዳደር መዋቅር ሥር እንዲሆን፤

6ኛ/ «ገለልተኛ ነኝ» የሚለው አካል ከማን ጋር እንደሚታረቅ፣ ከማን ጋር እንደተጣላ እንደዚሁም ከማን ጋር እንደሚስማማና ከማን ”ገለልተኛ”  እንደሆነ ባይታወቅም ተዋሕዶን በምትሰብክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም “በገለልተኝነት” ያለውን ሀብትና ንብረት አስቆጥሮ ለቅዱስ ሲኖዶስ ካስረከበ በኋላ በነዚህ አቢያተ ክርስቲያናት ውስጥ የተሾሙት አስተዳዳሪዎች የተቀጠሩት አገልጋዮችና ሠራተኞች የሚያገኙት ጥቅማጥም እንደተጠበቀ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲጽድቅላቸው ሆኖ ወደፊት እንዲያው እንጀራ ፈላጊው ሁሉ ድነገት ተነስቶ እንደ ሱቅ በደረቴ “ገለልተኛ” እያለ ቤተ ክርስቲያን መክፈት እንደሌለበት ጥብቅ መመሪያ እዲስጥ ቢደረግ፤

7ኛ/ በቅርቡ በመገናኛ ብዙኃን እንደሰማነው ሀገር ቤት በሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ቤተ ክርስቲያን በግሏ ባንክ ማቋቋም አልቻለችም በሚል ምክንያት፤ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ  ከጥቂት ባለሀብቶች ጋር የአክሲዮን የጣምራ የግል ባንክ ለመክፈት የተደረገው ስምምነት፤ ቤተ ክርስቲያን በጸሎት፤ በፍትሐት፣ በስዕለትና በመባዕ የስበሰበችውን ግብር የማይከፈልበትን የእግዚብሔር ገንዘብ፤ ከአራጣ አበዳሪዎች ገንዘብን በገንዘብ ለወጠው፣ ከግብር ከፋዮችና አትራፊዎች ነጋዴዎች፣ እንዲሁም በምን መልኩ ገንዘቡን እንዳገኙት ምንጩ ከማይታወቅ ገንዘብ ጋር መቀላቀል «የእግዚአብሔርን ለእግዚብሔር የቄሳርን ለቀሳር ስጡ» ከሚለው የቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ ሀብትና ንብረት አጠባበቅ ጋር የሚጣረስና የቤተ ክርስቲያንን አንጡራ ሀብት ለክፍተኛ አደጋ የሚያጋልጥ በጀራፍ አስገርፎ ከምኩራብ የሚያስወጣ መሆኑ ከወዲሁ ታስቦበት  በአስቸኳይ ስምምነቱ እንዲፈርስ እንዲደረግ፤

8ኛ/ የእርቀ ሰላም ስምምነት በሬድዮ፣ በተለቪዝንና በጋዜጣ እንዲሁም በማኅበራዊ መገናኛ መስመሮች ሁሉ እንዲሰራጭ፤ ይህ ከፍተኛ ብሔራዊ እርቅ ለስኬት ያበቁት አዲሱ ጠቅላይ ምንስትር  ዐቢይ አሕመድ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ከፍ ያለ ምስጋና ከሽልማት ጋር እንዲደርሳቸው ማድረግና የቅዱስ ሲኖዶስ ምላተ ጉባዔ ወስኖ በሚሰጠው መንፈሳዊ ስያሜ የዕለት ተዕለት ሥራቸው የተቃና የሠመረ  እንዲሆን በጸሎትና በቅዳሴ እንዲታሰቡ በማድረግ ለስምምነቱ የሚረዱ ሐሳቦች ይሆናሉ በማለት ለመጠቆም እንወዳለን።

እግዚአብሔር የቤተክርስቲያንን እርቀ ሰላም ዐቢይ ጉዳይ በሰላም ያስፈጽምልን፤ አሜን!

መጋቤ ጥበብ መንገሻ መልኬ

ኢንግላንድ፤ ለንደን፤

 

Share.

About Author

1 Comment

  1. I do not think as long as MK and his missionary exited the negotiation of two Synod will going to happened, MK and his mecinary is the cancer of Ethiopian Orthodox Church at this time . Thismafia grouo must hund of from the church.

Leave A Reply