የህወሓት መግለጫ እና አፀፋዉ – ጀርመን ራዲዮ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ የኢህአዴግ ሥራ አፈፃሚ ኮሚቴ ባሳለፋቸዉ ዉሳኔዎች ብዙ ስሕተትን ፈጽሞአል ሲል መግለጫ ማዉጣቱን አሳሳቢ ሲሉ የፖለቲካ አቀንቃኞች ተቃወሙት።

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ የኢህአዴግ ሥራ አፈፃሚ ኮሚቴ ባሳለፋቸዉ ዉሳኔዎች ብዙ ስሕተትን ፈጽሞአል ሲል መግለጫ ማዉጣቱን አሳሳቢ ሲሉ የፖለቲካ አቀንቃኞች ተቃወሙት። ህወሓት በባህሪዉ ለዉጥ አላመጣም ፤ ህዝቡ የጀመረዉ የለዉጥ ርምጃ እንዳይደናቀፍ እና ወደ አላስፈላጊ መነሳሳት እንዳያመራ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል። ህወሓት ያሳለፈዉን ዉሳኔ በተመለከተ የፖለቲካ አራማጆችን አስተያየት አሰባስናል።

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ያወጣዉን መግለጫ አስደንጋጭ እና አሳሳቢ ካሉት መካከል የህወሓ መሥራች ዶክተር አረጋዊ በርሄ አንዱ ናቸዉ። ዶክተር አረጋዊ እንዳሉት መግለጫዉ ህወሐት ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚም ይሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለዉን ለዉጥ እንደማይቀበለዉ ያሳወቀበት ነዉ።

«አሁን ያለዉ አካሄድ በአዲሱ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ መሰረት ኢህአዴግ እስካሁን ሲከተለዉ የነበረዉ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባል ነገር፤ እንደማያዋጣ በተለያየ መልኩ አይተነዋል። በተለያየ ሁኔታ ኢትዮጵያን ያስቀደሙበትን ጉዳይም አይተነዋል። ከአለዉ ለዉጥ ጋር ሊሄዱ እንደማይችሉ፤ ኢህአዴግንም በአጠቃላይ የሚቃወሙ መሆኑንም የሚያሳይ ይመስለኛል»

ከመግለጫዉ አንድ አንድ አርፍተነገር ልጥቀስሎ ዶ/ር አረጋዊ ፤  «ህወሓት እና የትግራይን ህዝብ ለማዳከም እና ለመምታት በተለያዩ መንገዶች ፀረ-ትግራይ ህዝብ እና ፀረ ህወሓት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ የዉስጥም የዉጭም ሀይሎችን ህዝቡ አምርሮ እንዲታገላቸዉ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ጥሪዉን ያቀርባል» ይላል ይህን እንዴት ይፈቱታል?

« አንደኛ ነገር ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ እነሱ እንደሚሉት ሳይሆን ሆድና ጀርባ ነዉ፤ አይገናኝም። እስካሁን ድረስ ላለፉት ለ ሃያ ምናምን ዓመታት የትግራይን ሕዝብ ጨምድደዉ ይዘዉ አፍነዉ አደኽይተዉ ያኖሩት ሕዝብ ነዉ። በሌላ በኩል ሁሉም ትግራይ መሽገዉ ሕዝቡ ከሌላዉ ወገኑ «ከኢትዮጵያዊዉ» ለማጋጨት ለማታገል ያቀዱት መንገድ መሆኑ የሚያሳይ ነዉ፤ ሌላ ትርጉም የለዉም። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የማይለወጡ መሆናቸዉን የሚያሳየን ነዉ።»

ህዉሓት በትግራይም ሆነ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የመናገር የመጻፍ ነጻነትን ሲደፈጥጥ ኖርዋል ያሉት ዶክተር አረጋዊ በርሄ በመቀጠል፤ « በርግጥ ጦርነትም በማስጮህ ብቻ ሳይሆን አሁንም በፊትም ህወሓት በትግራይም ይሁን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጦርነት አዉጆ ተፎካካሪ ሃይሎችን፤ ነፃ ኃሳብ የሚያንሸራሽሩ ጋዜጠኞችን ሲያፍን ሲገድል ሲያሳድድ የኖረ ድርጅት ነዉ»

ህወሓት በፊት እንደሚፈራዉ በዶ/ር አብይና በአቶ ለማ መገርሳ ይመራል የሚባለዉ ቡድን የጀመረዉን የተሃድሶ ለዉጥ ለማደናቀፍ በግልጽ መዘጋጀቱን ያመለክት ይሆን መግለጫዉ?

« ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ያመላክታል። አንደና በዶ/ር አብይ እና በአቶ ለማ መገርሳ አማካኝነት በኢትዮጵያ ተነሳስቶ ያለዉ የሃገር ፍቅርና የሃገር ስሜት የለዉጥ አዝማምያ ለነሱ እንደ እሪት ነዉ የሆነባቸዉ ፤

ይህንኑ ለማደናቀፍ እደተዘጋጁ  ያሳያል። ለኢህአዴግ አመራር እያሉም እንደ ማስጠንቀቅያ አይነቶችም የሰጡት ነገርም አለ። አብረዉ የወሰንዋቸዉ ዉሳኔዎች እንደ አልጀርሱ የድንበር ስምምነት ጉዳይ ይጠቀሳል። ይህን ስምምነት ሲጀመር እነሱ ነዉ የፈረሙት አብረን ወስነናልም ይላሉ፤ ዉሳኔዉ መጽናት አለበት ይላሉ፤ ወረድ ብለዉ ደግሞ ብልሽት አለበት ይላሉ። ፍጱም እንዲህ እርስ በርሱ የተምታታበት መግለጫ አይቼ አላዉቅም።»

የኦሮሞ መብት አቀንቃኙ አቶ ገረሱ ቱፋ በበኩላቸዉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ሰፊ ድጋፍ ያገኘዉ የለዉጥ ሂደት ህወሓቶችን እንዳላስደሰተ ፤ ከትግራይ ሕዝብም ድጋፍ እደሌላቸዉ የታየበት የአቋም መግለጫ ነዉ ሲሉ ነዉ የተናገሩት።መግለጫዉ በዋናነት ኢህአዲግ ዉስጥ ያለዉ ግንኙነት እንደአዲስ መሰራት ያለበት ወቅት ላይ መድረሱን አመላካች ነዉ ያሉን የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሃሌሉያ ሉሌ በበኩላቸዉ « ህወሓት»፤ ኢህአዴግ ዉስጥ ያለዉን አዲስ የኃይል አሰላለፍ እንዳለመደዉና እንዳልተዋጠለት የሚያሳይም ነዉ።ይላሉ።  ኢትዮጵያ የሽሽግር ወቅት ላይ ነች ሲሉ የተናገሩት አቶ ሃሌሉያ በመሪዎች እና በፓርቲዎች መካከል የሚከሰት ስር የሰደደና መሰረታዊ ልዩነት ሃገሪቱን ወደማያስፈልግ አቅጣጫ ሊመራት ይችላልና ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል። የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እና ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራም በመግለጫው ጠይቋል።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

DW

Share.

About Author

Leave A Reply