የህዝብና ቤቶች ቆጠራ በስኬት እንዲጠናቀቅ የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል—የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

መቀሌ ከተማ ነዋሪዎች በከተማው የሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ በስኬት እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገለጹ። በደቡብ ክልል የሕዝብና ቤት ቆጠራ የአሰልጣኞች ስልጠና እየወሰዱ ያሉ ሰልጣኞች በበኩላቸው የተጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በመቀሌ ከተማ ሐውልት ክፍለ ከተማ የሚኖሩት ቄስ ሐየሎም ገብረመድህን የህዝብና ቤት ቆጠራ ሥራ መብትም ግዴታም በመሆኑ ለስራው ስኬት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በሥራቸው የሚገኙ አምስት ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ጎረቤቶቻቸው የመቆጠር መብት፣ ግዴታና ጠቀሜታውን ተገንዝበው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የማነሳሳት ሥራ እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።

የስነ ምግባርና ስነ ዜጋ መምህርት የሆኑት መሰለች ጉዕሽ በበኩላቸው ራሳቸውና ስድስት ቤተሰቦቻቸው በአግባቡ እንዲቆጠሩ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

“ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ መስጠት የተሳሰተ ዕቅድና አፈጻጸም እንዲኖር በማድረግ ህዝብን ይጎዳል” ያሉት መምህርት መሰለች ህብረተሰቡ ይህንን አውቆ የሚፈለግበትን መረጃ በትክክል መስጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።

” የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ፍትሃዊ የሆነ የልማትና የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ያግዛል” ያለው ደግሞ በመቀሌ ከተማ የቀደማይ ወያነ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት አብርሃለይ ምግና ነው።

ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በቆጠራው ለተሰማሩ ባለሙያዎች ተገቢውን መረጃ እንዲሰጥ የበኩሉን በመወጣት ቆጠራውን ስኬታማ ለማድረግ መዘጋጀቱንም አስታውቋል።

የመቀሌ ስታስቲክስ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የትግራይ ክልል የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ፀሐፊ አቶ አማረ ገብረዋህድ በህዝብና ቤቶች ቆጠራው 11 ሺህ ባለሙያዎች እንደሚሰማሩ ጠቁመዋል።

በመቀሌና በሽሬ እንዳስላሴ ከተሞች በተከፈቱ ማዕከላት ለሁሉም የቆጠራ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።

ለህዝብና ቤት ቆጠራ የሚያስፈልጉ የታብሌት ሞባይል፣ ዘመናዊ የጂፒኤስ መሳሪያዎችና ለቆጠራ ስራው አጋዥ የሆኑ ሰነዶችን በክልሉ ወደ ሚገኙ 52 የቆጠራ ማዕከላት የመጓጓዝ ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመርም አመልክተዋል።

የህዝብና ቤት ቆጠራ ሥራውን ለማሳካት የሚያስችሉ ከ8 ሺህ በላይ የቆጠራ ጣቢያዎችና 11 ሺህ የቆጠራ ባለሙያዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ሕብረተሰቡ አለመቆጠር በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን አውቆ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ለሕዝብና ቤት ቆጠራው ስኬት የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

በተመሳሳይ ዜና የተጣለባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ከደቡብ ክልል ካፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ማጂ ዞኖችና ከየም ልዩ ወረዳ የተውጣጡና በሚዛን አማን ከተማ የሕዝብና በቶች ቆጠራ የአሰልጣኞች ስልጠና እየወሰዱ ያሉ ሰልጣኞች ተናግረዋል።

ከካፋ ዞን የመጡት መምህር ብርሃኑ ሽፈራው እየተሰጠ ያለው ሥልጠና ቆጠራውን በዕውቀት ላይ ተመስርቶ ለማከናወን የሚያስችል ግንዛቤ እንዳስጨበጣቸው አስረድተዋል።

ለሕዝብና ቤት ቆጠራ ሥራው ስኬታማነት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጡም አመልክተዋል። ከቤንቺ ማጂ የመጡት መምህር አብዱ ካሳ በበኩላቸው ከፍተኛ የሆነ የሀገር ሀብት ወጪ ተደርጎበት ለሚካሄደው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ስኬት ተግተው ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በማዕከላዊ እስታትስቲክስ ኤጄንሲ የሚዛን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አማኑኤል አንጁሎ ከጤና፣ ከትምህርትና ከግብርና ዘርፎች የተውጣጡና ባለሙያዎች በሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ስራው እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።

የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች መለየታቸውንና ከአካባቢው አስተዳደር አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል። በሦስቱ ዞኖችና በየም ልዩ ወረዳ 3 ሺህ 766 የቆጠራ ቦታዎችና 998 መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል። በሕዝብና ቤት ቆጠራ ስራው ላይ 3 ሺህ 763 ባለሙያዎች በቆጣሪነት እንዲሁም 1ሺህ 11 ባለሙያዎች በተቆጣጣሪነት እንደሚሳተፉ ታውቋል።

ENA

Share.

About Author

Leave A Reply