“የሐምሌ 11 የዋሽንግተን የአባቶች ዕርቀ ሰላም ሒደት፣ ፍጹም የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚመለስበት እንዲኾን ትጉና ጸልዩ” (የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ይህ የምእመናን ልጆቻችን የሰላም ጥማትና የዘወትር ጸሎት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ የዕለት ከዕለት የሰላም ጥረት ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ሰላሙ መቋጫ ወደሚያገኝበት ደረጃ እንዲደርስ፣ የ2010 የጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን ተከትሎ በራሱ ተነሣሽነት ከካህናትና ምእመናን የተውጣጣ የሰላም ኮሚቴ ያቀረበውን የዕርቀ ሰላም ጥያቄ በአዎንታ ተቀብሎት ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው የዕርቀ ሰላም ሒደት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ሠይሟል፡፡

በዚሁ መሠረት፣ ከሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በአባቶች መካከል የሚካሔደው የዕርቀ ሰላም ሒደት ፍጻሜ የሚያገኝበት፣ በውጭ አገር የሚገኙ አባቶች ወደ አገር ቤት የሚገቡበት፣ ፍጹም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት የሚመለስበት እንዲኾን፣ በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ካህናትና ምእመናን በጸሎት እንድትተጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ መንፈስ እየሔደችበት ያለው የሕዝቡን ሰላምና አንድነት ማረጋገጥ ውጤታማ እየኾነ መጥቷል፡፡

ከዚሁ ጋራ ለዘመናት አንድነትና ቤተሰባዊነት የነበራቸው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሕዝቦች ወደ ፍጹም ሰላም እንዲመጡ እየተከናወነ ያለው ጅምር፣ ቤተ ክርስቲያናችን በእጅጉ የምትደግፈውና ለመጨረሻውም ግብ የበኩሏን አስተዋፅኦ የምታደርግበት ይኾናል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በአኹኑ ጊዜ በውስጧ የሚገኙ ችግሮቿን ከጥንት ጀምሮ ይዛው በቆየችው ትዕግሥትና የሰላም ሒደት በቀኖናዋ መሠረት የምትፈታው ሲኾን፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷን በብቃት የምታከናውንበት አቅጣጫ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቀምጧል፡፡

በቀጣይ ወቅቱንና ዘመኑን በዋጀ መልኩ፣ መልካም አስተዳደርን በቤተ ክርስቲያናችን ካለፈው በበለጠ ማስፈን እንዲቻል፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግሮች ሊፈታ ያስችላል፤በሚል በባለሞያዎች የተዘጋጀውን መሪ ዕቅድና ከአሁን በፊት የተጠኑ ጥናቶች በተግባር ማዋል እንዲቻል፣ ጥናቶቹ ለ2011 ዓ.ም. የጥቅምት ምልዓተ ጉባኤ ዋና የመነጋገሪያ አጀንዳ ኾኖ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

አሁን በቤተ ክርስቲያናችን አባቶች መካከል የተጀመረው ዕርቀ ሰላም ያለምንም መሰናክል ለውጤት ይበቃ ዘንድ፣ ዕርቀ ሰላሙን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ከሰጠው አካል በስተቀር መግለጫ መስጠት ጠቃሚ አለመኾኑን ምልዓተ ጉባኤው አበክሮ ያሳስባል፡፡

በዕርቀ ሰላሙ ሒደት በሚደረገው ማንኛውም ውይይት የነበረውንና ቤተ ክርስቲያናችን ይዛው የቆየችውን ቀኖና በተመለከተ፣ ውይይቱም ኾነ እይታው በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ብቻ የሚታይ ይኾናል፡፡

አሁን ለተጀመረው የዕርቀ ሰላምና አንድነት መገኘት፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውክልና ይዘው ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ብፁዓን አባቶች፣ ጉዟቸው የተቃናና የተሳካ ኾኖ ችግሩ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ ሁላችንም ተባብረን እንድንሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለአገራችንና ለሕዝባችን ሰላሙን ይስጥልን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

ሐምሌ 4 ቀን 2010 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

 

(ሀራ ተዋህዶ)

Share.

About Author

Leave A Reply