የመቄዶኒያ ህሙማን በጎርፍ ተወሰዱ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ሃያት ጨፌ ፀበል ለመጠመቅ የሄዱ ሁለት የሜቄዶንያ ህሙማን በደራሽ ጎርፍ መወሰዳቸው ተነገረ፡፡

በጎርፍ ከተወሰዱት መካከል የአንደኛው አስከሬን በፍለጋ የተገኘ ሲሆን የሁለተኛው አስከሬን እስከአሁን ያለመገኘቱን የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

በተያያዘም ትላንትና ከትላንት በስተያ እየጣለ ያለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በርካታ ንብረቶች መውደማቸውንም የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ስለሺ ተስፋዬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

አቶ ስለሺ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሦስት የተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች የገባ ጎርፍ በርካታ ውድመት ማስከተሉን ገልጸዋል፡፡

ከነዚህም መካከል ወረዳ ስምንት በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ገብቶ 200 ሺህ ብር ሲያወድም ባለስልጣኑ ባደረገው ርብርብ 2 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በወረዳ አንድ 350 ሺህ ብር ሲወድም 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን የተቻለ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ወረዳ ስምንት ሰርቄ ማርያም እየተባለ በሚጠራው ስፍራ 500 ሺህ ብር ማዳን መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በሌላ አደጋ ደግሞ በኮልፌ ክፍለ ከተማ ሶር አምባ እየተባለ በሚጠራው ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ በደረሰ የእሳት አደጋ በርካታ የንግድ ሱቆች የተቃጠሉ ሲሆን  2 ሚሊየን 280 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡

በጉዳቱ 10 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ከእሳት ማትረፍ መቻሉንም ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ አደጋ በጉለሌ ናይጄሪያ ኤምባሲ አካባቢ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ የተለኮሰ የእንጀሪ መጋገሪያ ምጣድ መረሳቱን ተከትሎ 700 ሺህ ብር ንብረት ሲወድም 1 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉን አቶ ስለሺ ገልጸዋል፡፡

ባለስልጣኑ ከበድ ያለዝናብ ሊያጋጥም እንደሚችል አስታውሶ ሊከሰት የሚችለውን ጎርፍ ታሳቢ በማድረግ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ያሳሰበ ሲሆን የጎርፍ አደጋ ካጋጠመ 939 ላይ በመደወል ለባለስልጣኑ ማሳወቅ እንደሚቻልም አስታውቋል፡፡

 

Share.

About Author

Leave A Reply