የመከላከያ ሰራዊትን በአዲስ መልክ የሚያደራጅ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ቀረበ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 55ኛ መደበኛ ስብሰባ የመከላከያ ሰራዊት ማሻሻያ አዋጅን ጨምሮ በአራት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ።

የሃገር መከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ቁጥር 809/2006ን ለማሻሻል የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል።

በሃገሪቷ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ መከላከያ ሰራዊቱ ሃገራዊ ተልዕኮውን በተሻለ ብቃት እንዲወጣ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቀሰው ምክር ቤቱ፥ የሰራዊቱን የግዳጅ አፈጻጸም ብቃት ለማጠናከርም የህግ ማዕቀፍ አስፈላጊ መሆኑን አመላክቷል።

በመሆኑም ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ ማሻሻያዎችን በማከል ረቂቅ አዋጁ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልኳል።

ምክር ቤቱ በሌላ በኩል የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ደንቡ ስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል።

ከዚህ ባለፈም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት እንዲሁም የፌደራል ዓቃቢያን ህግ መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ ተግባርና ሃላፊነትን ለመሰወን በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይም ተወያይቶ ደንቡ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲቲዩትና የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በቅርቡ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲቲዩት ተብሎ መቋቋሙ ይታወሳል።

የኢንስቲቲዩቱን ስልጣን፣ ተግባርና አደረጃጀት ለመወሰን የፕላንና ልማት ኮሚሽን ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ባቀረበው መሰረት ነው ምክር ቤቱ ዛሬ ውሳኔ ያሳለፈው።

በተመሳሳይ በስራ ላይ ያለው የፌደራል ዓቃቢያን ህግ መተዳደሪያ ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ስራ ላይ ከዋለ ረጅም ዓመታት ያሳለፈ በመሆኑ፥ በአሰራር ላይ የታዩ ክፍተቶችና ሎላዊነት ያስከተላቸው ለውጦችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ደንቡን መለወጥ ማስፈለጉን ኢዜአ ዘግቧል። FBC

Share.

About Author

Leave A Reply