የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የቆዳ ጫማ የዳርማር አጀማመር ታሪክ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ከ1920ዎቹ በፊት ከባህላዊው ነጠላ ጫማ በስተቀር ሽፍን ወይም ኩፍ ጫማ የሚመጣው ከውጭ አገር በነጋዴዎችና በአስመጪዎች ነበር። የጫማ ስራ አገራችን አመጣጥ የሚያስገርም ታሪክ አለው። በ1912 ስቴፓን ዳርካጂያን የሚባል የአርመን ተወላጅ ወደ አሜሪካን ለመሄድ ግብጽ አገር ካይሮ የመጓዣ ፈቃድ ከአሜሪካን ኤምባሲ ለማመልከት ይሄዳል።

በዚያን ዘመን አሜሪካ ለመጓዝ የውጭ ዜጋ የትራኮማ በሽታ የሌለው መሆኑን የሐኪም ምስክር ወረቀት ማግኘት ነበረበት። ስቴፓን ይህን ሰርቲፊኬት ለማግኘት በሚጠብቅ ጊዜ የአሜሪካ ካፌ የሚባል ቡና ቤት ሄዶ ቡና ሲጠጣ ላላ ሁቫሰን አሳዱሪያን የሚባል ያገሩ ያገኝና ጨዋታ ይጀምራሉ። ስፔፖን ለአዲሱ ጎደኛው የቆዳ ሰራተኛና ፤ አሜሪካም ሄዶ ያንንም ስራ ለመቀጠል ምኞት እንዳለው ይነግረዋል።

ይህ አሳዱሪያን ኢትዮጵያ የሚኖር ነጋዴ ስለ ነበር ፤ ስቴፓንን አሜሪካ ሄደህ ከምትለፋ ኢትዮጵያ ማንም ጫማ ሰሪ ስለሌለህ ባጭር ጊዜ ትከብራለህ ይለዋል። ስቴፕንም ይህን ምክር ሰምቶ የአሜሪካ ሀሳቡን ትቶ ተጉዞ ሐረር ገባ። እዚያም ካሪኪያን ከሚባል የአርመን ሸሪካ ጋር የዘመናዊ ቆዳ ማልፊያ ጀምሮ ሚስትም አስመጥቶ ወልዶ ከብሮ መኖር ጀመረ። ከልጆቹ አንዱ ማርዲሮስ የሚባለው ከሐረር አዲስ አበባ መጥቶ ፤ አቃቂ የተስፋፋ የቆዳ ማልፊያና በኋላም አዲስ ጫማ ፋብሪካ ከፈተ። ስሙንም ዳርማር ብሎ አርማውን አንበሳ አድርጎ ከፈተ። በጣም ከበርቴም ሆነ።

እኛ የቀድሞ ልጆች ጫማ የሚገዛልን ፒያሳ የሚገኘው የዳርማር ሱቅ ነበር። በዚያን ዘመን ሌላው ምርጫ አስኮ ጫማ ነበር። ጫማው ሙሉ ለሙሉ ቆዳ ነበር። ፋብሪካው ደርግ ሲመጣ እንደማንኛውም ቅሚያ በገልበት ወርሶ አምበሳ ጫማ ብሎ ሰይሞ የመንግስት አደረገው። የዳርማር ባለቤት ልጆችም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ደርግን ሸሽተው አሜሪካ አምበሳ ጫማ የሚባል ፋብሪካ ጀምረው እስካሁን በስኬት ይካሄዳል።

(አበበ ሀ/ወይን ዶ/ር)

Share.

About Author

Leave A Reply