የሚልዮኖች የነፃነት ድምፅ ይሰማ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የሚሊዮኖች የነፃነት ድምፅ ይሰማ
ውስጤን ሲሞግተኝና ዛሬ ነገ ስለው ባጅቼ በዕለተ ልደታ ግን ሳላነሳው ላልፈው ያልፈለኩትን ጉዳይ ላጋራችሁ። – የወንድሜ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የ”ይፈታ ዘመቻ” ነው።
ከሁሉም በፊት ግን ለክርስትና ዕምነት ተከታዮች(ዕለቱን ለምታከብሩ) እንኳን ለልደታ ማርያም አደረሳችሁ ለማለት እፈልጋለሁ። በውዳሴዋም “ቅድስት አንቲ እም አነስት ወብሩክ ፍሬ ከርስኪ፤ ተፈስሂ ፍስህት ኦ ምልዕተ ፀጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ …. ሰዓሊለነ ቅድስት።”ብዬ በዚሁ ወደ ወደዕለቱ ነገረ ዝክሬ ልዝለቅ።
ከላይ እንደጠቀስኩት “ዘመቻ አንዳርጋቸው ፅጌ ይፈታ” በትንሹ ከመነሻ እስከመድረሻው ሶስት ዓበይት ቁም ነገሮችን ያበክራል። የመጀመርያውና ቀላሉ የዚህ ዓይነት ዘመቻዎች ሲካሄዱ እንደአቶ አንዳርጋቸው በተገለለ ቦታና ለብቻው ለታሰረ(በየዕለቱ ምን ዓይነት ጫናዎች እየደረሱበት እንዳለ እግዚአብሔር ይወቀው፤ በእኔ ደረጃ በነበርን ሚዛን የማናነሳ ታሳሪዎች ላይ እንኳ የነበረው የዋዛ አልነበረምና)የብርታት ስሜት ሲሰጥ በዘመቻው ለሚሳተፉ ወገኖች ደግሞ አጋርነታቸውን በማሳየት ለሚፈለገው ውጤት የየራሳቸውን አሻራ ያሳርፋሉ፤ ይህም የህሊና እረፍት ይሰጣቸዋል።
ዘመቻው ዓለም ዓቀፍ ባሕሪን የተጎናፀፈ፣ ቅቡል መርሆች ያሉት፣ የብዙሃን ፍላጎት በጋራ የሚገለፅበትና የዚህ ዓይነት ዘመቻዎች ተጨባጭ እውነታ ደግሞ ተፅዕኖው በአጭር ጊዜ ናኝቶ ተንኖ ይቀራል ተብሎ የማይገመት ሲሆን ከሁሉም በላይ አፈፃፀሙ ቁሳዊ ሃይልን በመጠቀም ሳይሆን ህሊናዊ፣ ሞራላዊና መንፈሳዊ በመሆኑ አድራጊው ወገን በየትኛውም ሚዛን አሸናፊ የሚሆንበት ነው።
በተለይ አሳሪው ወገን የዚህ ዓይነት ዘመቻዎችን ሞራላዊ ልዕልና፣ ዴሞክራሲያዊነትና ዘመቻው ተደራሽ ለሆነለት ወገን(ለአሳሪው) የሚሰጠውን በመርህ አንፃር የሚመዘን ዕውቅና 1- ካለማጤን 2- ዝቅ አድርጎ ከመመልከት 3- ለፖለቲካዊ ውሳኔዎች መርሕ ወጥ አመለካከት ካለመያዝ 4- ከግትርነትና ቂመኝነት እንዲሁም 5ኛ- ከሕግ አኳያ የመወሰን መብቱ ያላቸው አካላት በተጨባጭ ግን የማድረግ አቅም ከማጣትና ከ’መስጋት’ ምላሹን አሉታዊ ቢያደርጉት፣ ወይም ሰምተው እንዳልሰሙ ቢያልፉት ቢያዘገዩት ሚዛን በራሳቸው የፖለቲካ ሜዳ ነጥብ ይጥላሉ።                                                                                                                                                                                                                                                                            በጀመርኩት አገላለፅ ልቋጨውና ጥያቄውን አጢኖ ፈጣን አዎንታዊ መልስ መስጠት ሁለቱንም ወገን ነጥብ ያጋራል። በግሌ እንደብዙው ሰው ለራሴ ያህል ካለችኝ መጠነኛ ግንዛቤ በስተቀር፤ ስለትጥቅ ትግል ሁለንተናዊ ምንነት፣ መስመር፣ ስልት፣ ስትራቴጂ፣ የአማራጩን ለምንነትና እንዴትነት፣ ወዘተ ገፋ አድርጌ ማተት አልችልም። ከመንስኤ፣ አካሄድና አፈፃፀም አንፃር ግን የሚመለከተው አካል በጥልቅና በፅሞና፤ እንደተባለው ለዴሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ ምህዳሩ መስፋትና መሰል እውነቶች ሲባል ብዙሃንን ያሳተፈው በጎ ዘመቻ በአፋጣኝ ከተመረመረ(የቁርጠኝነትና መግባባት መጥፋት ካልሆነ እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም አልተደረገም ለማለት ይከብደኛል)፣ የወንድሜ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የፍች ቀን በቀናት የሚቆጠር ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ። እመኛለሁ፤ ተስፋ አደርጋለሁ።
አቶ አንዳርጋቸው ያኛውን መንገድ ሲመርጥ በእሱ ደረጃ ላለ የፖለቲካ ሊቅና የረዥም ዘመን የትግል ሰው አሁን ያጋጠመውን (እገታ እንበለው ምርኮ ወይም አንዳች አይነት መካድ) ጨምሮ መቁሰል መድማትና መሰዋት እንደሚደርስበት ያጣዋል ተብሎ አይታሰብም። ይህን ዘመቻ የሚያካሂዱ ወገኖችም በተመሳሳይ ይህን ሃቅ ጠንቅቀው ያውቁታል። ይህ ግዙፍ እውነት ነው የጥያቄውን ዋጋ የከበረ የሚያደርገው። ጥያቄው እየቀረበ ያለበት መንገድም ለየትኛውም የፖለቲካ ‘ሀሁ’ የሚያውቅ አካል የዋዛ አይደለም።
የዚህ ዓይነት ጥያቄዎች መርሐቸውን ሳያፋልሱ፣ ያዝ ለቀቅ ሳይደረጉና በተጠናከረ ሁኔታ ከተካሄዱ፤ መንግሥታዊ ከተማን በታንክ ከብቦ ከመደራደር የበለጠ አስጨናቂና ውጤታማ መሆናቸው በተለያዩ የታሪክ ልምዶች ውስጥ ተስተውሏል። እውነታውን በሽፋኑ ጋርደን የእኛ የተለየ ነው ሊባል አይችልም ወይም ብዙ ቢገፋበት አያዋጣም።
ይህን ጥያቄ እያቀረቡ ያሉትን ወገኖች ማንነትም በአግባቡ መመልከት ጠቃሚ ነው። ኢትዮጵያውያን ናቸው። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? አንደኛውን መገለጫቸውን ብቻ እንይ ብንል እንኳ አገር ስትወረር “ልዩነታችን ይቆየን” ብለው ለአገራችን ሉዓላዊነትና አይደፈሬነት በጋራ የሚቆሙ፣ ከአብራካቸው የወጡ ልጆቻቸውን መርቀው ለሰማዕትነት የላኩ፣ እንደአባይ ግድብ ባሉ ፕሮጀክቶች ቴክኒካዊ ዝክሩ ምንም ይሁን ለአገራችን እስከጠቀመ ብለው ከልጆቻቸው ጉሮሮ ነጥቀው የበኩላቸውን ያደረጉ፣ እነሱ በሚገብሩት ግብር አገር የምትኖር፤ በዚህ ወይም በዚያ በአገራቸው ጉዳይ ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ ወደጎን ሊደረግ የማይችልና በአጠቃላይ አነጋገር ጥያቄያቸው በአክብሮት ሊታይ የሚገባ እንጂ የተቀናቃኝ ሃይሎች ዘመቻ (ጫፍ በወጣ አገላለፅ የጠላት) ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት ሊስተዋል ይገባል።
ብዙ ያለመታደሎችና ለዘመናት ሲውሰበሰቡ የመጡ የፖለቲካችን እንክርዳዳዊ ጦሶች ውጤት እንጂ አሳሪም ታሳሪም የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች መሆናቸው ያሳምማል፤ እስከመቼ? ያሰኛል።
ዘመቻውም ለአንድ ግለሰብ ብቻ የሚደረግ ሳይሆን ተምሳሌታዊና በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ መሆኑም ሌላው ወርቃማ ጎኑ ነው። ይህ የሚሊዮኖች የነፃነት ድምፅ ይሰማ!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!                                                                                                                                                                      በ ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ

Share.

About Author

Leave A Reply