የሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ስለ ለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ማብራሪያ ሰጠ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በሥሩ ካሉት 26 ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው የሚድሮክ ወርቅ ኃ/የተ/የግል ኩባንያ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አዶ ሻኪሶ (ለገደንቢ) የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካን በፕራይቬታይሽን ከተረከበ በኋላ ባለፉት 20 ዓመታት በወርቅ ማምረት ስራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡

ኩባንያው አስፈላጊውን ፎርማሊቲ በማሟላት የመጠቀሚያ ፈቃዱ ለ10 ዓመታት በቅርቡ ከታደሰለት በኋላ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ በሰዎችና በእንስሳት ላይ ጉዳት ደርሷል በሚል በተነሳ ቅሬታ የማምረት ሥራው ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ በማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ለጊዜው እንዲታገድ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ኩባንያው በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ አጭር ማብራሪያ የያዘ መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡ የመግለጫው ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ተስተናግዷል፡፡

ከሚድሮክ ወርቅ ማዕድን .የተ.የግል ማኅበር የተሰጠ መግለጫ

ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኃ.የተ.የግል ማኅበር የማምረት ሥራው ለጊዜው መታገዱን በሚመለከት በተለያዩ የሚዲያ አካላት መግለጫ ለምን አይሰጥም ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ኩባንያው ከቴክኖሎጂ ግሩፕ አንዱ እንደመሆኑ የሚከተለው የአሠራር ፍልስፍና “ገንቢና ውጤታማ ግንኙነትን” ወይም “Constructive Engagement” እና የሀገርን ህግ ፍፁም በሆነ መልኩ መከተልን ቅድሚያ በመስጠት ነው፡፡ ስለሆነም “በሰውና በእንስሳት ላይ የጤና ችግር ደርሷል” የሚል የህብረተሰብ ተቃውሞ ስላለ ተጨማሪ ጥናት ተደርጎ ይህ ሁኔታ በተጨማሪ ጥናት እስኪጠናቀቅ ድረስ የማምረት ሥራችንን በጊዜያዊነት እንድናቆም የማምረት ፈቃድ ሰጪው የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አዟል፡፡

ኩባንያው ትዕዛዙን ተቀብሎ የማምረት ሥራውን ብቻ ማቆሙን ለፈቃድ ሰጪ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ባስታወቀበት ደብዳቤ የጥናቱ ሂደት ፈጣን እንዲሆን ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም በዚሁ ደብዳቤ ኩባንያው ምርጥ የሆነውንና በዓለም ላይ ብዙ ታላላቅ የወርቅ ማምረቻ ኩባንያዎች የሚጠቀሙበትን ሳይናድ (Cyanide) የሚባል ኬሚካል እንደሚጠቀምና ይህም ኬሚካል በህፃናት፣ በእናቶች ላይ አካልን፣ ጽንስን ወዘተ. የመሳሰለ ችግር እንደማያመጣ በመግለፅ ጥናቱ ሚድሮክ ወርቅን ብቻ ሳይሆን አካባቢውን ሁሉ ያካተተ መሆን እንዳለበት ግንዛቤ እንዲያዝ ጠይቋል፡፡ የተሰጠውን ትዕዛዝ አክብሮ፣ ሠራተኞቹን አረጋግቶ፣ የንብረት መበላሸትና መጥፋት እንዳያጋጥም ከአካባቢው የመንግሥት አካላትና የፀጥታ አስከባሪዎች ጋር በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ሳይንሳዊ ችግር በሳይንሳዊ ጥናትና ድምዳሜ የሚፈታ መሆኑን በማመን ኩባንያው ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎችና ከማህበረሰቡ ጋር የሚያደርገውን የተቀናጀ ሥራ በአፅንኦት ይቀጥላል፡፡

ኩባንያው ሳያመርት በሚውልበት እያንዳንዱ ቀን በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አሉታዊ ተጽዕኖ ያደርጋል፡፡ የማምረቻ መሣሪያዎች ካለመንቀሳቀሳቸው የተነሳ የሚደርስ ችግርና የሠራተኞች የመንፈስ መረበሽ የሚያስከትለውን ከፍተኛ ውጭ ከግንዛቤ በማስገባት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚያደርገው ጥናት በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ኩባንያው ጠይቋል፡፡ በቀጣይም ይጠይቃል፡፡

…………………

ፎቶ ካፕሽን፡- ዶ/ር አረጋ ይርዳው፤ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰርና

የሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ

Share.

About Author

Leave A Reply