የሚገርመን አፍንጫ ሲመታ ዓይን ባያለቅስ ነው!

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ትናንት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ያለሀጢያቱ ጀሃዳዊ ሃረካትን፤ በንጹሃን ዜጎች የመብት ጥያቄ ላይ አኬልዳማን በሸፍጥ ሲያቀናብሩ፤ ዜጎችን ያለ ምንም ማስረጃ ከርቸሌ አጉረውና በካቴና ጠፍንገው ሀሰተኛ ዶክመንተሪ ፊልሞችን ለዓለም ህዝቦች ሲያዘንቡ ሁለት ተኩል አሥርት ዓመታትን የዘለቁት የጥንቶቹ በረሀኞችና የዛሬዎቹ ቢሊየነሮች፤ በሚገርም ሁኔታ ሰሞኑን ስለ ሜቴክ የተዘገበው ነጭ ሀቅ እንደ አበጨጓሬ ኮሰኮሳቸው።

ራሳቸው በጠነሰሱት የሀሰት ወንጀል የንጹሃን ዜጎችን ክብር ሲያረክሱ የነበሩት “ምርጦቹ” የደደቢት በቃዮች ዛሬ በማስረጃ በተረጋገጠ ወንጀል ተፈልገው ከሀገር ለመኮብለል ሲሞክሩ በህግ ቁጥጥር ሥር ስለዋሉ ብቻ ለክብራቸው ተጨነቁ። ሰብዓዊነትን ቀደው በመጣል ጤነኞችን ያለሀጢያታቸው በሀሰት ወንጀል ከርቸሌ አጉረው ሲያበቁ ያለ ምንም ርህራሄ እጆቻቸውን ሲቆርጡና እግሮቻቸውን ሲጎምዱ፤ በኮረንቲ ሲጠብሱና ሲያኮላሹ ድፍን 27 ዓመታትን የዘለቁት የክፍለ ዘመኑ አውራ ወንጀለኞች፤ በስልጣን ከለላ የሀገርን ሀብት ዘርፈው ሲያበቁ “እንዴት በህዝብ ፊት ባደባባይ በካቴና እንታያለን?” ሲሉ ለክብራቸው ደነፉ።

በጥቅም ሰክረው በሥልጣን ሲባልጉ በነበሩበት ዘመን ለገቢሩ ቀርቶ ለቃሉ እንኳ ጆሮአቸውን ያልሰጡትን ‘ሰብዓዊነት’ ዛሬ ምንተ-እፍረታቸውን ይዘክራሉ፤ የቅርብ ጊዜ ትዝታ የሆነ ጭራቅነታቸውን አድበስብሰው ለሰብዓዊነት ጥብቅና እንቁም ይላሉ። ትላንት በግፍ ያፈሰሱት የቄሮዎች፤ የፋኖዎች፤ የዘርማዎች…ወዘተ ደም ሳይደርቅ እነርሱ ግን ዛሬም እንደትናንቱ ዓይኖቻቸውን በጨው አጥበው እራሳቸውን ከህግ በላይ ሽቅብ በመስቀል ስለ ክብራቸው መርከስና ስለ ሰብዓዊ መብታቸው መደፈር ሊነግሩን ይፈልጋሉ። በተረት “አፍንጫ ሲመታ…” እንደሚባለው ሁሉ ለዘመናት ሜቴክን የመሰለ ግዙፍ ብሔራዊ ኩባንያን እየዘረፈ ቢሊዮናት ዶላሮችን ወደ ራሱና ወደ “በረሃ ጓዶቹ” ካዝና ሲያንቆረቁሩ የነበሩት ሜ/ጀነራል ክንፈ ዳኘው ከሀገር ሊኮበልሉ ሲሉ ተይዘው በህግ ቁጥጥር ሥር ዉለው በካቴና መታየታቸው የበረሃ ጓዶቹን ቆረቆራቸው።

ይህ የጓዶቹ በካቴና መታየት በተለየ መልኩና በሚገርም ሁኔታ፤ የ2009ኙ የኢሬቻ እልቂት ቅንጣት ያላሳዘናቸውን፣ በግፍ የፈሰሰው የጨለንቆ አርሶ አደሮች ደም ያልጸጸተውን፣ የወልቃይት ዜጎች ደም ያልቆረቆረውን፤ ‘የተከበሩ’ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን አሳመማቸው። ከመጋረጃው በስተጀርባ ሆነው አብዲ ኢሌን በመዘወር ሺዎችን በጅምላ ሲያስፈጁ፤ ህጻናትን በእሳት ሲያቃጥሉ፤ አረጋውያንን በግፍ ሲያስፈጁ፤ ሴቶችን በጭካኔ ሲያስደፍሩ፤ ቤተ-ክህነቶችን በእሳት ሲያስወድሙና ቀሳውስቶችን በካራ ሲያሳርዱ የነበሩት ዶክተር ደብረጽዮን፤ ዛሬ ነገሩ ‘አፍንጫ ሲመታ…’ ሆነባቸውና ለጀነራል ክንፈ በካቴና መታየት ተንገበገቡ፤ ለክብራቸው ተቆረቆሩ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ከሱማሌ ክልል ለተፈናቀሉት ወገኖቻችን ማሰባሰብ የጀመረውን እርዳታ በአምባገነንነታቸው እንዲቋረጥ ያደረጉት ዶክተር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል፤ ዛሬ በወንጀለኞቹ “የበረሃ ጓዶቹ” ላይ የተወሰደውን ህጋዊ እርምጃ በትግራይ ህዝብ ላይ የተቃጣ ጥቃት እንደሆነም ባደባባይ ተናገሩ። በርግጥ ዛሬ ይህ ለእኛ ምንም አይገርመንም፤ የሚገርመን አፍንጫ ሲመታ ዓይን ባያለቅስ ነው እንጅ።
———————-
አባ ደራር

Share.

About Author

Leave A Reply