የማንነት ፖለቲካ የት ያደርሰን ይሆን?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ቋንቋን መሰረት ያደረገ የማንነት ፖለቲካ፣ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር  በሚደረገው ጉዞ ምን ዓይነት ሚና ይኖረዋል?  የነገዳዊ  ማንነት (ethnic identity) ፖለቲካ ገዢ በሆነበት ከባቢ ውስጥ የዲሞክራሲ ተቋማትን መገንባት ይቻላል ወይ? የማንነት ፖለቲካ የመጨረሻ ግቡስ ምንድን ነው? የሚሉና ሌሎች ተያያዥ  ጉዳዮች ብዙ የሚያስቆዝሙ ናቸው። የማንነት ፖለቲካ፤ በነገዋ ኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለውን  ስጋትና የሚፈነጥቀውን ተስፋ   በጥንቃቄ መመርመሩ፣ ሊከሰቱ ለሚችሉ ችግሮች ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመሻት ይረዳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋውን  የነገዳዊ ማንነት ፖለቲካ በደፈናው ከመርገምም ሆነ ከማንቆለጳጰስ ይልቅ በስፋትና በጥልቀት መወያየትና ሃሳብ ማንሸራሸሩ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ይህን ማድረግ በትልቁ ጃንጥላ ስር ለመሰባሰብ ያግዛልና፡፡

የዘርፉ ምሁራን “ነገደኝነት” (ethnicity)  ማህበራዊ አደረጃጀት ነው ይላሉ፡፡ ልክ እንደ ብሄርተኝነት፣ ነገደኝነትም አንድን አላማ ከግቡ ለማድረስ  “እኛ ከእነርሱ እንለያለን”  የሚሉትን ልዩነቶች “ጉዳዬ ነው” ብሎ በማቀንቀን፣ ‘እወክለዋለሁʼ የሚለውን ስብስብ ስሜት እንደ መቀስቀሻ የሚጠቀም ማህበራዊ አደረጃጀት ነው።

የዚህ አደረጃጀት ቅጥያ የሆነው  የ“ነገዳዊ ብሄርተኝነት” (ethnic nationalism) በበኩሉ፤ “እኛ” ብሎ የሰየመውን  የራሱን ስብስብ፣ “እነሱ” ብሎ ከፈረጃቸው ስብስቦች ጋር ያነጻጽራል፡፡ አነጻጽሮ ብቻም አያበቃም፡፡ አንድ ከሚያደርጉ የታሪክ ኩነቶች ይልቅ፣ ልዩነቶቹን በማጉላት፣ “እኛ ከእነርሱ እንለያለን” የሚለውን ቅስቀሳ የነገድ አባላቶቹን ለማሳመን ይጠቀምበታል። በታሪክ ውስጥ ከሌሎች ስብስቦች ጋር በመሆን ካስመዘገቡት የጋራ ጀግንነት ይልቅ፣ ‘ተፈጽሞብናል’ ለሚሉዋቸው የወል ሰቆቃዎች ትልቅ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ በታሪክ ‘ተፈጽሞብናል’ የሚሉትን ‘ሰቆቃ’ ለመሻርም፣ በነገዳቸው መደራጀትን ዋና መፍትሄ አድርገው ያቀርቡታል። በዚህም የዜጎችን ሉዓላዊነትና እኩልነት ወደ ጎን በመግፋት፣ የብሄሮች  እኩልነትና ሉዓላዊነት ዋናው የፖለቲካ ጥያቄ ይሆናል። የብሄሬ ሉአላዊነትና እኩልነት ይከበርልኝ የሚለውን ማጠንጠኛ በመከተል፣ የነገድ ብሄርተኝነት፣ የራስን መንግስት እስከ መመስረት የሚያልም ርዕዮተ ዓለም መሆኑን ምሁራን ይገልጻሉ፡፡

በዛሬዋ ኢትዮጵያም  የነገድ ልሂቃንና ተከታዮቻቸው፤ ʻእኛ’ እና ʻእነሱ’ በሚሉ ጎራዎች ተቧድነው፣ ሰርክ እንደ ተፋጠጡ ነው፡፡ ፍጥጫው ጨርሶ መርገብ አይታይበትም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጦዘ መሄድ እንጂ፡፡ የከረረው ፍጥጫ ወደ አመጽና ግጭት እየተቀየረም፣  የሰው ህይወት በተደጋጋሚ ሲቀጥፍ ተስተውሏል፡፡ ለዓመታት ከኖሩበት የተለያዩ  አካባቢዎች በማንነታቸው ምክንያት ʻመጤዎች ናችሁ’ እየተባሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን በግፍ ተፈናቅለዋል። ሃብት ንብረታቸው ወድሞባቸዋል፡፡ በየቦታው የሚታዩት በጭካኔ የተሞሉ ድርጊቶችም ከፍተኛ ስጋት በሃገሪቱ ላይ ደቅነዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ድርጊቱን የፈጸሙት ወንጀለኞች በህግ እንዳይጠየቁ፣ ድርጊታቸውን  የነገዳዊ ማንነት ቀለም ስለሚቀባቡት ጉዳዩን ውስብስብ አድርጎታል፡፡

“ምርጫና ቃጠሎ” በተሰኘው የባለቅኔ ጸጋዬ ገ/መድህን ግጥም ውስጥ የተሰደሩት ስንኞች የዘመኑን መንፈስ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ይመስለኛል፡፡

“…አየሩ በጥላቻ መርዝ፣ በዘር ጎጥ በመበከሉ

አንድነት እንደቁምጥና፣ ድውይ ተራ በመዋሉ

ቃል እንደ እርኩስ በመቅለሉ ጉድ አዋጅ

እያስተዋሉ፣…”

እርግጥ ነው፣ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጸሙትን ግፍና በደሎች ማስቆም እስካልተቻለ ድረስ፣ የነገዳዊ ማንነት ፖለቲካ የሁሉም ነገር መስፈርያ ሆኖ መቀጠሉ  የማይቀር ነው፡፡ ኢ-ፍትሃዊነትና ሙሰኝነት ከነገዳዊ ማንነት ጋር ሲቆላለፍ፣ ይዞት የሚመጣውን ዘርፈ-ብዙ መዘዝ እየታዘብን ነው፡፡ ሁሉም ነገር በነገዳዊ ማንነት መነጽር ታይቶ በሚመነዘርባት በዛሬዋ ኢትዮጵያ፣ ህግን በመጣስና የሃገርን ሃብት በመዝረፍ ተጠርጥረው ተይዘዋል የተባሉት ግለሰቦች፣ በተርታው ሰው ዘንድ ሳይቀር ፈጠን ተብሎ የብሄር ማንነታቸውን ወደ ማጣራት እስከ መሄድ ተደርሷል፡፡ ከዚያማ ‘የነ እንቶኔ ብሄር በመሆኑ ነው የታሰረው እንጂ ጥፋት የለበትም‘ ወደሚል ንትርክና ብሽሽቅ ይገባል፡፡ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በውጭ ከሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ “…በወንጀል ጉዳይ ብዙ መታሰር የሚገባው ሰው አለ – ኢትዮጵያ ውስጥ፡፡ ችግሩ ግን…ማህበረሰቡ ማን ታሰረ? ለምን ታሰረ? ከማለቱ በፊት የእኛ ታሰረ ይላል፤” በማለት ነበር የጉዳዩን ውስብስብነት የገለጹት፡፡ በአሁኑ ሰዓት ለኢህአዴግም የነገዳዊ ማንነት ፖለቲካ፣ ሌብነትንና ዝርፍያን ለመከላከል የቱን ያህል እጁንና እግሩን ጠፍሮ እንደያዘው ጥሩ ማሳያ ነው። ለዚህ ነው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በዚች አገር እውን እንዲሆን፣ በማንነት ላይ የተመሰረተውን ፖለቲካ በሚመለከት በብልሃትና በጥንቃቄ መመርመር የሚያስፈልገው፡፡

በነገዳዊ ማንነት ላይ የተመሰረተው ፖለቲካ ፈሩን ስቶ ኢትዮጵያን ወደ ባሰ ምስቅልቅልና ትርምስ እንዳያስገባት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በተለያዩ ጽሁፎቻቸው ከወተውቱ ምሁራን መካከል መሳይ ከበደ (ፕ/ር) አንዱ ናቸው፡፡ “የዘውግ ፖለቲካ ዋና ዓላማ ምንድር ነው? ከብሔራዊ አንድነት ጋር በምን ሁኔታ ሊጣጣም ይችላል?” በሚል በአንድ መድረክ ላይ ባቀረቡት ጽሁፋቸው፤ “…የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት …ከስልጣን ማውረድ  ቢችሉም እንኳን …ለዓመታት የተዘረጋውን ዘውጋዊ ክፍፍል ለማብረድና ብሄራዊ አንድነትን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ራእይና ፖለቲካዊ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ከሚስተዋሉት ችግሮች ሁሉ ተቀዳሚና እጅግ አስቸጋሪ የሆነው ዘውጋዊ ፖለቲካ በመሆኑ… አዲስ ስርዓት ለመመስረት ስለ ዘውግና ዘውጋዊ ፖለቲካ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘትን ይጠይቃል፤” በማለት ነበር፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጭምር በሰከነ  መንገድ ጉዳዩን ሊያጤኑት እንደሚገባ ምሁሩ ያሳሰቡት፡፡

ይሁን እንጂ መሬት የቆነጠጠውን ወቅታዊ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለሚታዘብ፣ በልሂቃኑ በኩል የማንነት ፖለቲካው እንዲጦዝ ሰፊ ቅስቀሳ በየአቅጣጫው እየተደረገ መሆኑን መገንዘብ ይችላል። ይህ ጠርዘኝነት በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ያደናቅፈው ይሆን? የሚለው ነው – ትልቁ የስጋታችን ምንጭ፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሰፈነባትን አገር የሚያልም ‘ዜጋ’ ሁሉ፣  በአገሪቱ ውስጥ የተዘረጋውን የነገዳዊ ማንነት ፖለቲካ በጥንቃቄ ሊያጤነው ይገባል። አሁን የተገኘው መልካም አጋጣሚ ከዚህ በፊት ተገኝተው እንደባከኑት የለውጥ ኩነቶች እንዳይጨናገፍ አርቆ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለመብቶቻቸው አስተማማኝ ዋስትና የሚያጎናጽፏቸው የዲሞክራሲ ተቋማት እውን የሚሆኑበት የስርዓት ለውጥ ነው የሚያስፈልጋቸው፡፡

በነገዳዊ የማንነት የፖለቲካ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ይቻላል ወይ? ብሎ መጠየቅ የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው። አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ምሁራን በዲሞክራሲና በብሄርተኝነት መንታ መንገድ ላይ እየዋለሉ መሆናቸውን በጥልቀት በመረመሩበትና በተነተኑበት ‹‹ምሁሩ››  በተሰኘው መጽሐፋቸው (ገጽ፣ 124)፤ “…እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በርካታ ብሄሮች ባሉባቸው ሀገሮች ውስጥ የሚከሰት ብሄርተኝነት፣ በዲሞክራሲ ትግበራ ላይ የሚጫወተው የአደናቃፊነት ሚና እጅግ የጎለበተ ነው ማለት  ይቻላል፤” ሲሉ በነገዳዊ ብሄርተኝነትና በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ትግበራ መካከል ያለውን ግንኙነት አስረድተዋል፡፡

አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) ብዙ ብሄሮች ባሉበት አገር የሚከሰት ብሄርተኝነት ለዲሞክራሲ ትግበራ የአሰናካይነት ሚና እንዳለው ሲያብራሩ፤ “…ተፎካካሪ ፍላጎትና የጥቅም ግጭት በደራበት ፖለቲካዊ ምህዳር ውስጥ፣ ዲሞክራሲን ተቋማዊ ማድረግ እጅግ ይከብዳል፡፡…በመሆኑም ብሄርተኝነት ሊፈጥር የሚችለውን የጥቅም ግጭት ለማስታገስና ለመቆጣጠር የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ሂደት ዋነኛ ተግባር ሆኖ ይቀርባል፤” ይላሉ፡፡

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በዚች አገር የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ብዙዎች ተዋድቀዋል። እኩል ተጠቃሚነት እንዲኖር ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተሰደዋል፡፡ ኢትዮጵያ የጥቂቶች ብቻ ሳትሆን የሁሉም ግለሰቦችና ብሄረሰቦች አገር እንድትሆን ውድ ህይወታቸውን ጭምር ሰውተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ያ ሁሉ መስዋዕትነት ተከፍሎም፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከ”የትም ፍጭው ስልጣኑን አምጭው” አካሄድ ማላቀቅ አልተቻለም፡፡ የፖለቲካ ሜዳው ጉልበተኞች የሚጋልቡበት፤ ያሻቸውን የመጫወቻ ህግጋት በማርቀቅ ‘ኑ እስኪ ይዋጣልን’ በሚል የሚገበዙበት ሆኖ ቆይቷል፡፡  ድምጻዊው፤ “አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ” ሲል እንዳቀነቀነው፣ ከአገዛዝ ወደ አገዛዝ እንጂ፣ ህዝብ ወኪሎቹን የሚያወጣበትና የሚያወርድበትን ስርዓት መትከል አልተቻለም። ይባስ ብሎም የአገሪቱ ልሂቃን፣ በነገዳዊ ማንነት ተሰልፈው  የማይደማመጡ ባላንጣዎች ሆነዋል። የነገድ ማንነት የሁሉም ነገር መመዘኛ በመሆኑ፣ ሌሎች አማራጭ ሃሳቦች ወደ ዳር እንዲገፉም አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የብሄረሰቦች መብት በሚገባ መከበር አለበት፡፡ ‘መከበር አለበት’ ሲባል፣ ባለፉት ሦስት አስርት አመታት እንደታየው፣ መብቶቹን በወረቀት ላይ አስፍሮ መታበይ አይደለም፡፡ በተጨባጭ መተግበር ይገባል፡፡ አንዱ ሌላውን ስጋት አድርጎ የመፈራረጅ አባዜ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፋይሉ መዘጋት  አለበት፡፡

ባለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያን  መላልሰው  ከተፈታተኑዋት  ችግሮቿ ዋነኞቹ፣ ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች  ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት በተደጋጋሚ ለአደጋ ተጋልጧል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነትና ክብር ሲሸረሸር ደግሞ የብሄረሰቦች ክብርም እንደሚሸረሸርና አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ መገንዘብ ያሻል፡፡ “አሰባሳቢ ማንነት” የሆነችውን  ኢትዮጵያን  በጽኑ መሰረት ላይ ማቆም ሳይቻል፣ ብሄረሰቦች ብርቱ ሆነው ይቆማሉ ማለት የዋህነት ነው፡፡

ዶናልድ ሌቪን (ፕ/ር) ‹‹ትልቋ ኢትዮጵያ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ፤ “…የታላቂቱ ኢትዮጵያን ጉዳይ ወቅታዊ ማድረግ ማለት፣ በብሄራዊ  አንድነትና በፍትህ የተመሰረተች አዲሲቱ ኢትዮጵያ የምትገነባበትን ዘዴና መንገድ መፈለግ ማለት ነው፤” ያሉትን ልብ ማለት ያሻል፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው  የለውጥ ጉዞ፣ የመላ  ኢትዮጵያውያን  መብትና ጥቅም ወደሚከበርበት ዲሞክራሲያዊ  ሥርዓት  ማሸጋገር ካልተቻለ፣ “ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ” ከመሆን አያልፍም፡፡ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር በሚደረገው ጥረት፣ ለነገዳዊ ስብስቦች ተገቢውን እውቅናና ቦታ በመቸር፣ ዜግነት ላይ ወደተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት የምንሻገርበትን  ድልድይ መገንባት በእጅጉ ወሳኝ ነው፡፡

(አብርሀም ገብሬ)

Share.

About Author

Leave A Reply