የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ከ7 የተለያዩ ኩባንያዎች ጋር የማዕድን ምርመራ እና ፍለጋ ስምምነት አደረገ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2011(ኤፍ.ቢ.ሲ) የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ከሰባት የተለያዩ ኩባንያዎች ጋር የማዕድን ምርመራ እና ፍለጋ ስምምነት መፈፀሙን አስታውቋል።

የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ኪሮስ አለማየሁ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት ኩባንያዎቹ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሲሆኑ ስምምነቱን የተፈራረሙትም ለ3 ዓመታት ነው ብለዋል።

ስምምነቱን የፈፀሙት ኩባንያዎችም ሰቆጣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ አይጋ ትሬዲንግ ኢንደስትሪስ፣ አጎዳዮ ሜታል ኤንድ አዘር ሚኔራልስ፣ አልታው ሪሶርስ ሊሚትድ፣ ሰን ፒክ ኢትዮጵያና ሂምራ ማይኒንግ ናቸው።

ኩባንያዎቹም በከበሩ ማድናት፣ በወርቅ ፣ ብረት እና ብረት ነክ፣ በፖታሽ፣ በድንጋይ ከሰል እና የመሳሰሉ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የሚሰማሩ መሆኑን አቶ ኪሮስ ተናግረዋል።

ኩባንያዎቹ በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች የሚሰማሩ ሲሆን፥ለ138 ኢትዮጵያውያን ዜጎችም የስራ እድል ይፈጥራሉ ተብሏል:: ፈቃዱ የተሰጣቸው ኩባንያዎች በካፒታል አቅማቸው እና ሌሎች መስፈርቶችን ያለፉ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኪሮስ፥ በሚያከናውኑት ስራ እና ውጤት ታይቶ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድላቸው ይችላልም ብለዋል።

ኩባንያዎቹ ስምምነት ላደረጉበት 3 ዓመታት 90 ሚሊየን ብር ወጭ ያደርጋሉ ያለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፥ በየ ዓመቱ የሚሰሩት ስራም አዋጅ እና አሰራርን ተከትሎ የሚገመገም መሆኑን አሳውቋል።

በዙፋን ካሳሁን

Share.

About Author

Leave A Reply