የራስ ተፈሪ እምነት ተከታዮች ከሻሸመኔ ወደ ሐረር ሊጓዙ አስበዋል። ለምን?

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

«ወደ አህጉረ አፍሪካ ተመልከቱ አንድ ጥቁር ይነግሣል፤ ነፃነትም ይሆናል» ጃማይካዊው የመብት ታጋይ ማርከስ ጋርቬይ ነበር ይህን የተነበየው።  ኢትዮጵያን ከአራት አሥርት ዓመታት በላይ የገዙት ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በ1923 ዓ. ም. የንግሥና ዙፋናቸውን ጫኑ።

የእሳቸው ንግሥና ዜና አህጉረ አፍሪካን አልፎ ጃማይካ ደረሰ። ወሬውን የሰሙ የራስ ተፈሪ እምነት ተከታዮች ፈጣሪ በሥጋ ተገልጿ፤ ጠባቂያችን ነግሧል በማለት ወደ ኢትዮጵያ ጎረፉ። ራስ ተፈሪያን ጃህ እያሉ የሚጠሯቸው ጃንሆይ፣ በፈረንጆቹ 1966 ዓ. ም. ወደ ጃማይካ አቀኑ። ሥፍር ቁጥር የሌለው ሰው ተቀበላቸው። ባዩትም ነገር እጅግ ተደነቁ። እሳቸው ወደ ኪንግስተን ባቀኑ ጊዜ የሰማይ ውሃ ዓይንሽን ለአፈር ብሏት የነበረችው ጃማይካ በዝናብ እንደራሰችም ይነገራል።

የሬጌ ሙዚቃ ንጉሡ ቦብ ማርሌም በሙዚቃው አፍሪካን እና ኢትዮጵያን እንዲሁም ንጉሡን የመፃኢ ዘመን ተስፋ እና መጠጊያ አድርጎ ይስላቸው ነበር። ለአፍሪካ አንድነት በሠሩት ውለታ ሊታወሱ ይገባል ተብሎ በቅርቡ ሃውልት የቆመላቸው ጃንሆይም ወደ አፍሪካ መመለስ ለሚሻ ጥቁር ይሁን በማለት ሻሸመኔ አካባቢ 200 ሄክታር ገደማ መሬት ለገሱ።

የራስ ተፈሪ እምነት ተከታዮች ከደቡባዊ የአፍሪቃ ክፍል እስከ ምዕራቡ ጥግ፤ ከሰሜን እስከ ምስራቅ ይገኛሉ። እንደ ሻሸመኔ ግን ያለ አይመስልም።\
መጀመሪያ ላይ 12 ጃማይካዊያን ብቻ ወደ ሻሸመኔ እንዳቀኑ ይነገራል። ኋላ ላይ ግን የትየለሌ ራስ ተፊሪያኖች ጉዟቸውን ወደ ሻሸመኔ አደረጉ።

አሁን ላይ ሻሸመኔ ውስጥ በርካታ የራስ ተፈሪ እምነት ተከታይ ጃማይካዊያን ይኖራሉ። አሁን ግን ትኩረቱ ከአራት አሥርት ዓመታት በላይ ከቆዩባት ሻሸመኔ ወደ ሐረር የዞረ ይመስላል። ለምን?

ከሻሼ ወደ ሐረር  ራስ እዝቄል ኩማ ለበርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የኖረ የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታይ ነው። ኢትዯጵያ ውስጥ ወልዶ ከብዷል። ሕይወቱን መሥርቷል። ከሻሸመኔ ወደ ሐረር የሚደረገውን መንፈሳዊ ጉዞ የሚመራው ራስ እዝቄል ኩማ ለራስ ተፈሪያን ማሕበረሰብ ከሻሸመኔ ይልቅ ሐረር የተሻለ ቅርበት እንዳላት ይናገራል።

«ልንሆን የሚገባው ሐረር ነው። ጃህ፤ ንጉሳችን የተወለዱበት ሥፍራ ነው። እዚያ ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስትያን አለች። እዚያ ነው እትብታቸው የተቀበረው» ይላል። እርግጥ ነው ይህን ጉዞ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ ራስ ተፈሪያኖች ጥቂት እንደሆኑ ራስ እዝቄል አይሸሽግም። መኖሪያቸውን ሐረር ያደረጉ ጃማይካውያን እንዳሉም ይናገራል።

«ጉዞው ለኛ ትልቅ ትርጉም አለው። ወደ ሐረር እንድንጓዝ የሚያደርግ መንፈሳዊ ጥሪ ደርሷል። ይህን ጉዞ እኛ ለመጀመር እናስበው እንጂ ጥሪው ለሁሉም የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታዮች ነው።»

ራስ ኩማ ሐረር ለራስ ተፈሪ እምነት ተከታዮች ያላትን ሥፍራ ሲያስረዳ፤ «እኔ ሁሉም የራስ ተፈሪ እምነት ተከታይ በሕይወት ዘመኑ አንዴ ኤጀርሳ ጎሮን ቢያይ ደስ ይለኛል። የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ መካ እንደሚያቀኑት ሁሉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ቤተልሔምን ለማየት እንደሚጓጉት ሁሉ እኛም ሐረርን ማየት እንናፍቃለን» ይላል። ግን ግን የራስ ተፈሪ እምነት ተከታዮች ሐረር ውስጥ እንዴት ያለ ማሕበረሰብ ይሆን ለመመሥረት የሚሹት? ራስ እዝቄል ጉዞው ገና ጅማሮ ላይ ያለ ቢሆንም ልናቋቁም ያሰብነው ማሕበረሰብ ሻሸመኔ ከሚገኘው ለየት ያለ ነው ይላል።

«ለሁሉም የራስ ተፊሪያን እምነት ተከታይ የሚሆን ምቹ ሥፍራ እንዲሆን ነው ፍላጎታችን። እዚያ ከሚኖረው ማሕረበሰብ ተነጥለን የመኖር ዕቅድ የለንም። አንድነትን መሠረቱ ያደረገ፤ እርስ በራስ የሚከባበር እና የሚግባባ ማሕበረሰብ የመፍጠር ፍላጎት አለን።»
ከአርባ ዓመታት በላይ ጃማይካውያንን ያስጠለለችው ሻሸመኔስ ምን ይሰማት ይሆን? ራስ እዝቄል ጉዞው ከሻሸመኔ ጠቅልሎ ወጥቶ ወደ ሐረር የሚደረግ ‘ፍልሰት’ ተደርጎ እንዳይታሰብ ይሰጋል።

«ጉዳዩ አዲስ ምዕራፍ የመክፈት ጉዳይ ነው። በርካቶቻችን በምዕራብ ሃገራት ተጠልለን የምንኖር ነበርን። አሁን ግን አንድ የሚያደርገንን ነገር እንፈልጋለን። ይህን ስናስብ ደግሞ ‘ጃህ’ ከተወለዱበት ሥፍራ የተሻለ ቦታ የሚገኝ አይመስለኝም።»

ኤጀርሳ ጎሮ ጉዞው ጅማሬ ላይ ነው ያለው። ኤጀርሳ ጎሮ ላይ አንድ ቤተክርስትያን የማነፅ ሥራ ከዕቅዱ መካከል ይገኛል። በሁለት ዓታት ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገሮች ተሳክተው ጉዞ ሻሸመኔ – ሐረር የተሳካ እንደሚሆን ራስ እዝቄል እምነት አለው።

ከሐረሪ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በትብብር እየሠሩ እንደሆነም ይናገራል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የምስራቅ ሐረርጌ ፅህፈት ቤት ጉዞው የተሳካ አንዲሆን ከራስ ተፈሪያኖች ጋር በጥምረት እንዲሰራ እንደሚፈልጉ ራስ እዝቄል ይጠቁማል። በመላው ዓለም የሚገኙ ራስ ተፈሪያኖች ለጉዳዩ ጆሮ መስጠት እንደጀመሩ የሚናገረው ራስ እዝቄል ቤተክርስትያን የማነፁን ሥራ እንዲሁም ሌሎች ተግባራት የሚጠናቀቁ ከሆነ እርዳታው ከዚያም ከዚህም መምጣቱ አይቀርም ባይ ነው።

ኤጀርሳ ጎሮ አዲሲቷ የራስ ተፈሪ እምነት ተከታዮች ትሆን ይሆን? በስተመጨረሻ የእምነቱ ተከታዮች የጃንሆይን የትውልድ ስፍራ መጠጊያቸው አድረርገው ኃይማኖታዊ ጉዟቸውን ወደ ተስፋይቱ ምድር ያደርጉ ይሆን?
BBC

Share.

About Author

Leave A Reply