የሶቅራጠስ 3ቱ ጥያቄዎች (ምርጥ ታሪክ)

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

አንድ ሠው ወደ ሶቅራጠስ ሄዶ እንዲህ አለው፡፡ ‹‹ሶቅራጠስ ወዳጄ፣ እገሌ ስለተባለው ወዳጅህ የሠማሁት ነገር ደስ አይልም›› አለው፡፡ ሶቅራጦስ ግን ዝም አለ፡፡ ሠውየውም እንደገና “ይገርማል ከእርሱ አይጠበቅም፤ በጣም ገርሞኛል” አለ፡፡

ሶቅራጦስም ይህ ሰው እንደማይለቀው ስለተረዳ አንድ መደራደሪያ አቀረበለት፡፡ ‹‹ስለ ወዳጄ ልትነግረኝ የፈለግከውን ልሠማው የምችለው ሶስት ጥያቄዎች አሉኝ፤ እነርሱን ስትመልስልኝ ብቻ ነው›› አለው፡፡ ሠውየውም ተስማማ፡፡

‹‹የመጀመሪያው ጥያቄዬ የእውነት ጥያቄ ነው፡፡ ስለወዳጄ የሠማኸው መቶ በመቶ እውነት ነው ወይ?›› አለው፡፡ ሠውየውም ‹‹መቶ በመቶ እንኳን እርግጠኛ መሆን አልችልም›› አለው፡፡

ሶቅራጦስም ‹‹ልትነግረኝ የፈለግከው እርግጠኛ ያልሆነ ነገር ነው ማለት ነው፡፡ እሺ ሁለተኛው ጥያቄዬ የመልካምነት ነው፡፡ የምትነግረኝ መልካም ነገር ነው ወይ?›› አለው፡፡ ሠውየውም‹‹እርሱማ መልካም አይደለም›› አለው፡፡

ሶቅራጦስም ‹‹እውነትነቱ ያልተረጋገጠና መልካም ያልሆነ ነገር ልትነግረኝ ፈልገሃል፡፡ እሺ ሶስተኛውና የመጨረሻው ጥያቄዬን ልጠይቅህ?›› አለው፡፡ ሠውየውም ‹‹እሺ›› አለ፡፡

ሶቅራጦስም ‹‹የምትነግረኝ ነገር ለእኔ የሚጠቅመኝ ነገር አለው ወይ?›› አለው፡፡ ሠውየውም ‹‹የለም›› ብሎ መለሠ፡፡

ሶቅራጦስም በመጨረሻ ‹‹እውነትነቱ ያልተረጋገጠ፤ መልካም ያልሆነ፤ ለእኔ የማይጠቅም ነገር አልሠማም›› አለው ይባላል፡፡

ስንቶቻችን ነን ሰው የሚነግረን ነገር እውነት፣ መልካምና ጠቃሚ መሆኑን አጣርተን የምንሰማው? ስንቶቻችን ነን ለሰው ቁምነገር ብለን ልንናገር ስንል ከሶስቱ አንዱን ማሟላቱን የምናረጋገጠው? አሁን እኮ ሰው ዝም ብሎ የተነገረውን ስለሚሰማ በቀላሉ እንደ እንስሳ የሚነዳ ሆኗል፡፡ በየሶሻል ሚዲያው ላይ ፖስት የሚደረጉት ብዙዎቹ መረጃዎች እውነት ያልሆኑ፣ መልካምነት የሌላቸው እና ለእኛ ምንም ጥቅም የማይሰጡ ናቸው፡፡ በተቃራኒው የውሸት መረጃዎች ሆነው ስንቱን ያጭበረበሩ፣ ሰይጣናዊ ርምጃ ለመውሰድ የሚገፋፉ ሆነው ሳለ ያለማቅማማት እንሰማቸዋለን፡፡

አሁን አሁን እውነት ከሚናገሩት ሰዎች በላይ በመርዝ የተለወሰ ውሸት የሚናገሩ ሰዎች የተሻለ ብዙ ተከታይ አላቸው፡፡ መልካም መልካሙን ከሚሰብኩ ሰዎች ይልቅ የጥፋት ሰባኪዎች ብዙ ደጋፊ አላቸው፡፡ ፍለጠው/ቁረጠው ባዮች ናቸው የጀገኑት፡፡ እነሱን ማስቆም አይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን እነሱን አለመስማት/አለመከተል ቀላል ነው፡፡ እነዚህን የሶቅራጠስ 3ቱ ጥያቄዎችን እንደ ወንፊት ተጠቅመን ማጣራት ብቻ በቂ ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ አሪፍ ትያትር እንጠቁምዎ፤ “ባዶ እግር” ይሰኛል፡፡ በሶቅራጠስ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ሲሆን እሁድ 8፡30 ላይ ብሄራዊ ትያትር ጎራ ቢሉ በጣም ተዝናንተው፣ ጥሩ እውቀት አግኝተው ይመለሳሉ፡፡

‹ፅሁፉን› እውነት፣ መልካም እና ጠቃሚ ሆኖ ካገኛችሁት ሼር አድርጉት፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply