የቀድሞ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽነር በጫና ሥልጣን መልቀቃቸውን አጋለጡ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የቀድሞ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮምሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ከኮምሽነርነት ሥልጣናቸው በባለስልጣናት ጫና እንዲለቁ መደረጉን አጋለጡ፡፡

አምባሰደር ጥሩነህ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት ምርጫ 2002ን መከታተልና ሪፖርት በማቅረባቸው ምክንያት ከአቶ በረከት ስምኦን ጋር መጋጨታቸውን አስታውሰዋል፡፡ አምባሳደሩ እንዲህ ላሉ፡፡ ” አይ! ከወደቁ በኋላ ስም መጥቀስ እንዳይሆን እንጂ ከእነ አቶ በረከት ጋር ነው የተጣላሁት:: እኔ የዚያን ያህል አቅም ያላቸው አለመሰለኝም፡፡ በህግ የተሰጠኝን ነገር ማስፈፀምና መፈፀም የማልችል ከሆነ ጥዬ እንደምወጣ ነገርኳቸው::”

አያይዘውም ” ከእነ አቶ በረከት ጋር በተጣላሁ ማግስት ከፍተኛ የመንግስት ባስልጣናትም ሆኑ ሌሎች ተሰሚነት ያላቸው አካላት መልቀቂያ እንዳስገባ ጎተጎቱኝ፡፡ ምክንያቱም እኔ መልቀቂያ ካላስገባሁ ሊያባርሩኝ አይችሉም፡፡ መልቀቂያ አስገባ የሚል ጫና ከምቀርባቸውም ሆነ ከማከብራቸው አካላት ሲበረታ የ‹ልልቀቅ› ደብዳቤ አዘጋጀሁ” ብለዋል፡፡

የቅራኔው መነሻ ሲያስረዱም “አንድ ዓመት ከምናምን ያህል እንደሰራሁ ነው፤የቅራኔው መንስዔ ደግሞ ምርጫ 2002ን መከታተልና ሪፖርት ማቅረቤ ላይ ነው፡፡ የምከታተልበት ምክንያት ደግሞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ግዴታ በመሆኑ ነው በማለቴ ነው፡፡ እነሱ ደግሞ ‹አይደለም› በማለታቸው ነው:: በመሆኑም ይህን ማድረግ የማልችል ከሆነ በሚልና ሰዎችም ለቀህ ውጣ ባሉኝ መሰረት ልወጣ ከወሰንኩ በኋላ በዚህ መሃል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደውለው አንድ ነገር እንድስራ ጠየቁኝ:: ከዚህም አቶ መለስ ዘንድ የደረሰ አንዳች ነገር አለመኖሩንና እንደምለቅ የሚያውቁ አለመሆኑን ስረዳ ለምን ብዬ ነው ታዲያ የምለቀው በማለት በወቅቱ ‹ልቀቅ› ባዮችን ዞር በሉ አልኳቸውና ስራዬን ቀጠልኩ፡፡

በሥራቸው ላይ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነበር ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም እንደነበር በማያወላውል ቃል አረጋግጠዋል፡፡ “በጣም ነበር! ግን ህጉ አይፈቅድላቸውም፡፡ ስለዚህም ህጉ እንደማይፈቅድላቸው በመናገር መስራት ይቻላል:: ነገር ግን አሁን ደርሶ አንበሳ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ምንም አይናገሩም ነበር፤ እኔ ግን በአደባባይ እናገር ነበር” ብለዋል፡፡

አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮምሽንን ለአምስት ዓመታት በኮምሽነርነት መምራታቸውን ለጋዜጣው ተናግረዋል፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply