የቡድን 20 ሀገራት በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ ኢትዮጵያ ትፈልጋለች- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የቡድን 20 አባል ሀገራት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በስፋት እንዲሳተፉ ኢትዮጵያ ትፈልጋለች አሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በበርሊን በከተፈተውና አፍሪካ ኢኮኖሚ ድጋፍ በማደረግ ላይ የሚያተኩረው “ቡድን ሃያ ሀገራት ኢኒሼቲቭ ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ” ስብሰባ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በተጨማሪም የጀርመን መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል፣ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ፖል ካጋሜ፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እየተሳተፉ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግርም፥ የኢትዮጵያ መንግስት ጀርመን ቡድን 20 ሀገራት ኢኒሼቲቭ ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ ላይ እያደረገች ላለው ድጋፍ አድናቆት አለው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ታሪካዊ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን እያደረገች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ማሻሻያዎቹም ወጤት እያስመዘገቡ ነው ብለዋል።

ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ዘርፉ ላይ እየተገበረች ባለው ማሻሻያ በተለይም በመንግስት ሙሉ በሙሉ ተይዘው የነበሩ ተቋማትን ወደ ግል ለማዘዋወር እየተሰራ መሆኑን ያመለከቱ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ ቴኬሎም፣ የሀይል ልማት፣ ሎጂስቲክ እና የዓየር ትራንስፖርት ዘርፎች ይገኙበታል ብለዋል።

በኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ መንግስት ሌላው ትኩረት ያደረገው በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በመድረኩ ላይ ያነሱት።

ኢትዮጵያ ሳቢ እና አዋጭ የሆነ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አቅርባለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የቡድን 20 ሀገራትም በኢትዮጵያ በስፋት መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እንፈልጋለን ብለዋል።

ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2017 በጀርመን አነሳሽት የተጀመረ ነው።

ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ መሰረተ ልማትን ጨምሮ የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለማጠናከርና ለማበረታት የተጀመረ ኢኒሼቲቭ ነው።
የአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚና የፋይናንስ መዋቅራቸውን ሳቢ በማድረግ የግሉ ዘርፍ በኢንቨስትመንት በስፋት እንዲሰማራ የሚደግፍ መርሃ ግብር ነው።

በዚህም በሀገራቱ የሚገኙ የኢንቨስትመንት ዐድሎችን በስፋት ያስተዋውቃል።

በሀገራቱ የሚወሰዱ የማሻሻያ አጀንዳዎችና የፖሊሲ እርምጃዎችንም ይደግፋል።

ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ የቡድን ሃያ አባል ሀገራትን፣ ለለውጥ ዝግጁ ናቸው፣ የለውጥ አሥተሳሰብን ያራምዳሉ የሚባሉ አፍሪካ ሀገራትንና ዓለም ዓቀፍ አጋሮችን ያሰባሰበ ነው።

እስካሁንም ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ግብጽ፣ ጋና፣ ሴኔጋልና ሞሮኮን ጨምሮ አሠራ አንድ የአፍሪካ ሀገራት በዚህ ኢንሼቲቭ ተካተዋል።

Share.

About Author

Leave A Reply