“የባህር ዳሩ ሰልፍ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ ለሙሉ ይፃረራል” ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለጊዮን መጽሄት የሰጡት ሙሉ ቃለ መጠይቅ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ግዮን፡- የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ለጠ/ሚኒስትርነት መመረጥ እንዴት አዩት?

ዶ/ር ነጋሶ፡- በምርጫው ወቅት ሚዲያዎች በስፋት ስከታተል ነበር:: ኢህአዴግ የም/ ቤት ስብሰባ አድርጎ በራሱ መዋቅር መሰረት ‘ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ዶ/ር ዐቢይን የድርጅቱ ሊቀ መንበር አድርጎ መርጧል’ የሚል ዜና ስሰማ በሙሉ ልብ ነው የተቀበልኩት:: አምኛለሁም:: በጣም ነው ደስ ያለኝ:: ወጣት ቢሆኑም በድርጅታቸው ውስጥ ተቀባይነት እንዳላቸው እከታተል ነበር፤ በሰዓቱ በአብላጫ ድምፅ መመረጣቸውን በደስታ ነው የተቀበልኩት:: ከአዲሱ ትውልድ የተገኙ ውጤታማ ሰው ናቸው ብዬ ነው የማምነው::

ግዮን፡- ጠ/ሚኒስትሩ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ የሠሩት ሥራ እንዴት ይገለፃል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- የነበሩት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደቀሩና በመጥፎ ሁኔታ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ታስረው የነበሩ የፖለቲካ ሰዎች መፈታታቸው በጣም ደስ የሚል ነው:: በሀገር ውስጥ በዚህ ዙሪያ ጠ/ሚኒስትሩ በርካታ አመርቂ ሥራዎችን አከናውነዋል:: ከሀገር ውጪ በተለያዩ ሀገራት በእስር የሚገኙ ዜጎቻችን ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩ ከየሀገሪቱ መንግሥታት ጋር በመደራደር ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ አድርገዋል:: ሽብርተኛ ተብለው የታሰሩ ግለሰቦች ከእስር ተፈተዋል፤ በሽብርተኝነት የተፈረጁ ድርጅቶች ክሳቸው ተቋርጧል:: ይሄ ሁሉ በመጀመሪው ሩብ የሥልጣን ዘመናቸው የሠሩት መልካም ነገር ነው ማለት ይቻላል::

ግዮን፡- ሰሞኑን ለጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በተዘጋጀ የድጋፍ ሰልፍ ላይ፣ ህዝብ በነፃነት ሀሳቡን ሲገልፅ ነበር:: የነፃነት ታጋዮች ተወድሰዋል፤ ኮከብ አልባው ሰንደቅ ዓላማ በከፍተኛ ሁኔታ ተውለብልቧል:: ኮከብ ያለበት ባንዲራ አለመፈለጉን ይህ አያሳይም?

ዶ/ር ነጋሶ፡- በእኔ በኩል ግለሰቦችና ፓርቲዎች የሚወክሏቸው አመለካከቶች አሉ:: ሀሳብና ፍላጎቶች አሉ:: የፓርቲዎችንና የግለሰቦችን መብት ማክበር በጣም አስፈላጊ ነው:: በሌላ መልኩ ደግሞ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት ማክበር አለብን:: ሕገ መንግሥቱን ተመርኩዘው የወጡ ሕጎችን ማክበር አለብን:: በእኔ እይታ አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ የተለያዩ ዓይነት ባንዲራዎች ይታዩ ነበር:: ከላይ እንደገለፅኩት ይሄ የተለያዩ አካላት ስሜት ነው:: በተለያየ አቅጣጫ የሚንቀሳቀሱ አካሎች በአንድነት የጠ/ ሚኒስትሩን እንቅስቃሴ መደገፋቸው ጥሩ ነው:: ሁሉም የየራሳቸውን አመለካከት ይዘው ማለት ነው:: የባህር ዳር የድጋፍ ሰልፍ ግን ሙሉ በሙሉ ከአዲስ አበባው የድጋፍ ሰልፍ ይለያል:: በእኔ እይታ ሕገ መንግሥቱን መፃረር ነው ማለት ይቻላል:: ለሕግ ተገዥ ያለመሆን ነገር የተንፀባረቀበት ነው ብዬ ነው የማምነው::

ግዮን፡- በምን መልኩ ነው ሕገ መንግሥቱን የተፃረረው?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ሁላችንም እንዳየነው አንድ ወይም ሁለት ካልሆነ በስተቀር፤ የአማራ ክልልን ባንዲራም ሆነ የፌደራል መንግሥቱን ሰንደቅ ዓላማ በድጋፍ ሰልፉ ላይ አላየሁም:: ሕግ የሚከለክለው አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ ነበር በብዛት የታየው:: ስታድዮሙን ሙሉ ለሙሉ የሸፈነው የድሮ የኢትዮጵያ ባንዲራ ነው:: ይሄ በሕግ ተከልክሏል:: እነዚያ ባንዲራዎች አንድ ሊያደርጉን እንደማይችሉ ዐይተን፤ በ1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ የሚደምር፣ ሃይማኖታችንን በሙሉ የሚደምር፣ የተለያዩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን የሚያግባባና ሁላችንንም አንድ የሚያደርግ ባንዲራ የቱ ነው? ብለን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ሦስት ላይ አስቀምጦልናል:: በባህር ዳር ላይ የታየው ግን ይሄንን የሚቃረን ነው:: በእርግጥ የመቃወም መብት የሁሉም ነው፤ ይሄንን መከልከል አያስፈልግም:: ነገር ግን ሕገ መንግሥት ሳይሻሻል ‘እኛ የምንፈልገው የድሮውን፣ የነገሥታቱን ባንዲራ፣ የእነ አፄ ኃይለ ሥላሴን ባንዲራ፣ የእነ ሚኒሊክን ባንዲራ ነው የምንፈልገው’ የሚሉ ሰዎች ሀሳባቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ አቅርበው ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻልበት መንገድ አለ:: ሰዎች በባንዲራው ላይ ተቃውሞ ሊኖራቸው ይችላል:: ግን ይሄንን ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል መጠየቅ ነው እንጂ የድሮ ባንዲራ ይዘው በመውጣት ሀሳባቸውን በሌሎች ላይ መጫን አይችሉም:: እኔ እንደሚመስለኝ ባህር ዳር ላይ የታየው ሰንደቅ ዓላማ ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርግ አይደለም:: ሰዎች ትክክል ነን ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፤ ግን ያ ባንዲራ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አንድ ያደርጋል ተብሎ አይታመንም::

ግዮን፡- ሕዝቡ ግን “አንድነታችንን ይገልፃል ሁሉንም ህዝብ ያግባባል” ብሎ ነው ኮከቡን ለኢህአዴግ ትቶ ንፁሑን ሰንደቅ ዓላማ ራሱ ያውለበለበው፤

ዶ/ር ነጋሶ፡- ሰዎች ትክክል ነው ብለው ካመኑ የድሮውን ሰንደቅ ዓላማ መሸከም ይችላሉ:: የሚሸከሙት መብታቸው ቢሆንም፤ በይፋ ትክክለኛው የኢትዮጵያ ባንዲራ ይህ ነው ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ካሉ ስህተት ነው ብዬ ነው የማምነው:: ኮከቡ እንዲነሣ የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ፣ መጠየቅ መብታቸው ነው፤ ሕገ መንግሥቱ ላይ አንቀጽ ሦስት እንዲሻሻል ሕጋዊ አካሄድን መከተል ነው ያለባቸው እንጂ በእንዲህ ዓይነት ሰልፍ ላይ አይደለም ሌላ ነገር የሚያስተጋባው::

ግዮን፡- ሰልፉ ላይ የታየው የሰንደቅ ዓላማ ለውጥ በራሱ እኮ ግልፅ ነው ማለት ይቻላል:: መንግሥት ከዚህ ተነሥቶ የባንዲራውን ጉዳይ መልስ ሊሰጥበት አይገባም?

ዶ/ር ነጋሶ፡- አንደኛ፣ በባህር ዳር ስታዲየም ላይ የተገኘው ህዝብ መቶ ሚሊዮን የሚሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ቀርቶ ጠቅላላ የአማራ ክልልን ሕዝብ አይወክልም:: የተወሰኑ ግለሰቦች ናቸው በስታዲየም የተገኙት፤ እነዚያ ሰዎች በዚያ መንገድ ሀሳባቸውን ሊያቀርቡ ይችላሉ:: ግን ቀደም ሲል እንደገለፅኩት፤ ሕገ መንግሥቱ በግልፅ የሀገሪቱን ህዝቦች እኩልነት የሚያረጋግጥ ነው ያለውን ባንዲራ ይፋ አድርጓል:: በሕግ ፀድቋል:: በ1993 ዓ.ም ሕገ መንግሥት ሲረቅ እኔ ኦህዴድን፣ ዳዊት ዮሐንስ ኢህዴንን (ብአዴንን) ወክለን ተገኝተናል:: ያኔ ኢህአዴግን አይደለም የወከልነው፤ በሕገ መንግሥቱ ላይ ስንወያይ ከሁለታችን ውጪ ሃያ ሠባት የሌላ ፓርቲ ተወካዮች ነበሩ:: አጠቃላይ 29 ሰዎች ነን የተወያየንበት፤ እኛ ተነጋግረን ነው ሕገ መንግሥቱን ወደ ሽግግር መንግሥት ተወካዮች ም/ቤት ያቀረብነው:: ስለዚህ ያኔ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረን፣ ተከራክረን ሕግ አውጥተናል:: የሰንደቅ ዓላማው ጉዳይም በዚያ መንገድ የራሱ ሕግ በሕገ መንግሥቱ ተቀምጦለታል:: በርግጥ እንደሚባለው ሕዝብ የድሮውን ሰንደቅ ዓላማ የሚናፍቅና የሚፈልግ ከሆነ፣ በቀጥታ ሕጋዊውን መንገድ ነው መከተል ያለበት:: ግን እኔ እንደሚገባኝ በባህር ዳር ላይ የታየው ነገር የሁሉንም ኢትዮጵያ ሕዝብ አይወክልም:: ግዮን፡- በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ?

ደ/ር ነጋሶ፡- የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ያስፈልጋል የሚባለው ነገር ትክክል አይመስለኝም:: ሕገ መንግሥቱ “የመንግሥትን ሥልጣን የሚይዝ አካል በምርጫ ያሸነፈው ወገን መሆን አለበት” ይላል:: ስለዚህ ምርጫ ተካሂዶ በምርጫ ነው እንጂ፤ ዝም ብሎ ፓርቲዎችን ሰብስቦ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም አይቻልም:: አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ትክክለኛ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን እየተደረገ ነው:: ስለዚህ ምርጫው እንደከዚህ ቀደሙ አይደለም፤ ፍትሐዊ ይሆናል:: ውጭ ያሉት ኃይሎች ራሳቸው “ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየመጣ ነውና ጦርነቱን ትተን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመሥራት ዝግጁ ነን” ብለው እነ ግንቦት ሠባት፣ አርበኞች ግንባር እየመጡ እኮ ነው:: ስለዚህ በዚያ መንገድ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ ነው እንጂ የሽግግር መንግሥት ይመሥረት እያሉ ጊዜ ማጥፋቱ አስፈላጊ አይመስለኝም፤ ለእኛ የሚያስፈልገን አንድነትና መደመር እንጂ መጨንገፍ አይደለም::

ግዮን፡- እናመሰግናለን::

Share.

About Author

Leave A Reply