የባሕር ዳር ነዋሪዋ እና አደራ የተረከቡት አባት ለ20 ዓመታት በአደራ የኖሩበትን ቤትና የቤት ኪራይ ለኤርትራዊ ባለቤቱ አስረከቡ፡፡

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የባሕር ዳር ነዋሪዋ እና አደራ የተረከቡት አባት ለ20 ዓመታት በአደራ የኖሩበትን ቤትና የቤት ኪራይ ለኤርትራዊ ባለቤቱ አስረከቡ፡፡ የ20 ዓመታት የአደራ ቤትና ኪራይ ዛሬ ተመለሰ፡፡

‹‹ያሉት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ›› ትናንት ደብረ ማርቆስ ዛሬ ደግሞ ባሕር ዳር ላይ በተግባር ታየ፡፡ የታሪኩ መነሻ ጊዜ 1991 ዓ.ም ነው፡፡ ቦታው ደግሞ ባሕር ዳር ከተማ፡፡

ትውልድ ኤርትራዊው አቶ አብርሃም ደስይበለኝ በባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ነበር የሚሰሩት፡፡ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት ግን ከስራ እና ከመኖሪያ ቦታቸው ተነስተውና ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ተደረጉ፡፡

ከአባቷ ጋር አብራ ወደ ኤርትራ እንድትሄድ የተደረገችው የዛሬዋ ባለታሪካችን ሰናይት አብርሃም በወቅቱ የትና ለምን እንደምትሄድ ባታውቅም ተወልዳ ያደገችበትን ቀየና ቤት እየተሰናበተች ነበርና ‹‹አደራ!›› ለባለአደራ ሰጠች፡፡

አደራው ደግሞ የአባቷ የስራ ባልደረባ ለነበሩት ለአቶ ተፈራ አባተ እና እነሰናይት ከሀገር ሲወጡ ግቢው ውስጥ ተከራይታ ለነበረችው ለወይዘሮ መዓዛ ሳሙኤል ነበር የተሰጠው፡፡ ወይዘሮ መዓዛ ለረዥም ዓመታት በአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ውስጥ ሲሰሩ ቆይተው አሁን ላይ በጡረታ ከተቋሙ ወጥተዋል፡፡

እንደ ዋዛ ከሀገር እንደወጡ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠሩት ሰናይት እና ቤተሰቦቿ አንድ ቀን ወደ ባሕር ዳር-ቀበሌ 8 እንደሚመለሱ እና ንብረታቸውን እንደሚያገኙ ተሰፋ ነበራቸው፡፡ ዘመን መመለሳቸውን ሲፈቅድ፣ ያለያያቸው የፖለቲካ ቁርሾ በፍቅር ሲሽር፣ ተስፋ ወደ እውነታ ተቀየረ፡፡

ሰናይት ያደገችበትን ቀየና ቤት ዳግም ለማየት በቃች፡፡ ‹‹አደራ የተሰጠን ቤቱን ጠብቆ ለማቆየት ቢሆንም በየጊዜው ከኪራይ የሚገኘውን ገንዘብ በተለያየ መንገድ ለባለቤቶቹ እንዲደርስ ስናደርግ ቆይተናል›› ያሉት አቶ ተፈራ ዛሬ ደግሞ ከ20 ዓመታት ቆይታ በኋላ 18 ሺህ ብር ቀሪ ኪራይ እና ቤቱን ለባለቤቷ በአካል አስረክበዋል፡፡

‹‹ባለፉት ዓመታት በአስመራ በነበረኝ ቆይታ አንድ ሰው ‹ኢትዮጵያዊ ነው!› ሲባል ሀገሩን ብቻ ሳይሆን ታማኝነቱንም መግለጫ›› ነው ያለችን ሰናይት ከተቀበለችው ገንዘብ በላይ የግቢው እና የቤቱ አያያዝ ልዩ ስሜት እንደፈጠረባት ነግራናለች፡፡

ከ20 ዓመታት በላይ በኪራይ ቤት መኖር ያልተለመደ ነው ባይባልም እንግዳ ነገር ለመሆኑ ግን አጠራጣሪ አይደለም፡፡ ወይዘሮ መዓዛ ሳሙኤል ግን ከኪራይ ያለፈ ቃል እና እምነት ተጥሎባቸዋልና የእርሳቸውንና የሌሎችን ተከራዮች ወርሃዊ ኪራይ ለአቶ ተፈራ እየሰጡ ግቢውንም እንደ እራሳቸው ንብረት እየተንከባከቡ አደራቸውን ዛሬ ለሰናይት አስረክበዋል፡፡

(አብመድ) – ታዘብ አራጋው

Share.

About Author

Leave A Reply