“የቤተክህነት ኃላፊዎች የሚያመልኩት ሥርዓቱን ነው”

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

የዋልድባ መነኮሳቱ አባ ገብረየሱስ ኪዳነማሪያምና አባ ገብረስላሴ ወ/ኃይማኖት በባለፈው እትማችን ቆየት ያለውን የዋልደድባ ገዳምና የህወሃት ታጋዮችን ውዝግብ፤ ብሎም እስካሁን ድረስ የቆየውን የቦታውን ችግር በተመለከተ ሰፋ ያለ መረጃ ለአንባብያን አድርሰዋል፡፡ አንድ አመት ከሶስት ወር የቆየው የእስር ህይወታቸው ያሳያቸውን የፍትህ እጦት፣ የዜጎች መንገላታትና ሌሎች አንገብጋቢ አገራዊ ችግሮችን በተመለከተ ዛሬም የሚነገሩን በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ በተለይም ቤተ ክርስትያንና ቤተክህነትን በተመለከተ ጠለቅ ያለ መረጃ አድርሰውናል፡፡ መነኮሳቱን ከእስር እንደተፈቱ ያነጋገሯቸው የግዮን ጋዜጠኞች ፍቃዱ ማ/ወርቅና ሮቤል ምትኩ ሁለተኛውንና የመጨረሻውን ክፍል በዚህ መልኩ አቅርበውታል፡፡

ግዮን፡- በእስር ላይ እያላችሁ አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር ተሹሟል:: የዋልድባን ጉዳይ በተመለከተ ከጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ለማነጋገር አስባችኋል?

አባ ገብረ ኢየሱስ፡- ጠቅላይ ሚንስትሩን ለማነጋገር አስበናል:: እንደውም በቅርቡ እንገባለን ብለን ነበር፤ ነገር ግን መቀሌ በሄዱበት ሠዓት ያልሆነ ንግግር ሲናገሩ ቅሬታ ተሠማን:: በተለይ ስለ ፈላስፋው ዘርአያዕቆብ የተናገሩትን በደንብ ሠምተነዋል:: “የዘርአያዕቆብ አገር” ማለታቸው ትንሽ ተሠምቶናል:: ያልሆነ ታሪክ በአደባባይ መናገር፣ የሌላ የሆነን ታሪክ አሳልፎ ለሌላ መስጠት ወንጀል ነው:: ዘርአያዕቆብ ዘእንፍራንዝ መጠቀስ ያለበት ኢትዮጵያዊ መሆኑ እንጂ ትግራይ መሆኑ አይደለም:: በዚህ ደግሞ ልንሞግታቸው ስለምንችልና መረጃው ስላለን ነው፤ ይሄ ትንሽ ቅር አሰኝቶን ነበር:: እኛ ከህወሓት ጋር የመጀመሪያው ፀባችንና ልዩነታችን የዋልድባ ገዳም ነው:: ሁለተኛው የድጓ ምስክር፣ የቤተልሔምን ምስክር የመሠሉ ወደ ትግራይ የመውሠድ ጥረት ነው::

የራስ ዳሽን ተራራን የተነጠቅን ሰዎች ዛሬ እንዴት የቤተልሔም ምስክር፤ የማኅበረ ሥላሴ ገዳም፤ የጎንደር መሬት ለሱዳን ተላልፎ መስጠት፤ የራስ ዳሽንን ወደ ትግራይ መከለል አግባብ አይደለም እያልኩ ነው:: ይሄ የእምነት ጉዳይ ነው:: ዝም ተብሎ የሚታለፍ አይደለም:: ደብረ ቢዘንን የመሠለ ገዳማችንና ቅርሳችንን አሳልፈን ሰጠን:: አሁን ሌሎችን አሳልፈን ልንሰጥ እየተዘጋጀን ነው:: ምንም ያልመሰላቸው ሰዎች ዝም ይበሉ፣ እኔ ግን እናገራለሁ:: የታሪክ ዝርፊያ አስፈላጊ አይደለም:: ታሪኩን ላባለ ታሪኩ ነው መተው ያለበት:: የእኔ ያልሆነውን ታሪክ ተቀብዬ አስተናግዳለሁ ብል ታሪኩ ራሱ አይቀበለኝም::

በቅርብ ጊዜ የተዘጋጀ የመስቀል በዓል አለ፤ ትግራይ ላይ፣ የታሪኩ ባለቤት ማን ሆነና ነው ፓትርያርኩ አዲግራት ድረስ ተጉዘው መስቀልን እናክብር ለማለት የተፈለገበት ምክንያት ምንድነው? የመስቀሉ ባለቤት ወይም ባለታሪኩ ማን ሆነና ነው እዛ አካባቢ እንደዛ መጮሁ? ይሄ ነገር ወደ ነገ ሲሄድ ታሪኩ አቅጣጫውን የሳተ መንገድ ይከተላል ማለት ነው:: የዛሬ ሦስት ሺህ ዓመት ላስታና ሠቆጣ ላይ የነበረው የአሸንዳ ታሪክ ትናንት ትግራይ ላይ መከበር ስለተጀመረ ዓለም ዓቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝ ተደርጓል:: እንዲህ ያለውን ታሪክ አሳልፈን የምንሰጥበት ምክንያት ምንድነው? ያልሆነ ታሪክ ለሌላ አካል እንዴት ተላልፎ ይሰጣል? እኛኮ ይሄን መሠሉን ትውልድ የሚበርዝና የሚያበላሽ ነገር ነው የምንቃወመው::

ስለዚህ ታሪኩን ለባለታሪኩ መተው ይገባል:: የሌለን ታሪክ ለራሳችን ብንወስደው ሸክም ካልሆነ በቀር አይዋሃደንም:: ብሔር፣ ክልል የሚባለውን ነገር እኔ አልቀበልም፤ አላምንበትምም:: ግን የትኛውም ታሪክ ለሌላ ተላልፎ መሠጠት የለበትም:: ለምሣሌ፤ የጎንደርን ታሪከ ለራሱ ለጎንደር ስንስጠው ይዋሃዳል፤ የትግራይን ታሪክ ለትግራይ ስንሰጠው ይጣጣማል፤ የሸዋውንም፣ የሀረሩንም እንደዛው ነው ማድረግ ያለብን:: አሳልፈህ ባለቤቱ ላልሆነ ስትሰጥ ግን ታሪክ ይበላሻል:: ማኅበረ ሥላሴ በጎንደር ክልል ተከልሎ ግን ወደ ሱዳን ሊሄድ በዝግጅት ላይ ነው:: ገዳሙ ይሄን መሠሉ አደጋ ከፊት ለፊቱ ተጋርጦበታል:: በምን መስፈርት ይህ ቦታ ለሱዳኖች ታሪክ ይሆናቸዋል? የላስታን ታሪክ ለላስታ ስትሰጠው መጽሐፉ ላይም ስታነበው ከትውልድ ወደ ትውልድ ላስታ እያለ ይሄዳል:: የጎንደርን የቤተልሔም ድጓ ታሪክ አምጥተህ ጎንደር ከተማ ላይ ብታስቀምጠው አይዋሃድልህም:: ቤተልሔሞች ጋይንቶች ግን ይጠቀሙበታል:: ሌላውም ህዝብ የራሱን ታሪክ ይዞ ይሄዳል ማለት ነው:: እኔ በኢትዮጵያዊነቴ የማምን የዓባይ ዳር የግዮን ፍሬ ነኝ:: አንዱን ከሌላው ለይቼ ልመለከት አልችልም:: ግን ታሪክ እንዲበረዝ ደግሞ አልሻም:: ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጉዳይ ስንመጣ፤ እሳቸው ጋር የዋልድባ ገዳም ጉዳይን በተመለከተ መግባታችን አይቀርም፤ በቅርብ ቀጠሮ እናስይዛለን::

ትግራይ ላይ ያደረጉት ንግግር ቅር ስላሰኘን በተለይ የወልቃይትን ጉዳይ አስመልክተው የተናገሩት ጥሩ ስሜት ስላልያዘ የእኛም መልስ በቂና ጥሩ አይሆንም በሚል አቁመነው ነበር:: አሁን በቅርቡ ጎንደርና ባህር ዳር ላይ ባደረጉት ንግግራቸው ደግሞ የተወሠነ መልክ ቀየር ብሎ መጥቷል:: ጎንደር ስንደርስ ከጎንደር ህዝብና ከተለያዩ የአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተነጋግረን ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ የምንመጣበት ጊዜ ይኖረናል:: ያ በዕቅድና ፕሮግራም የሚሆን ነገር ነው::

አባ ገብረ ሥላሴ፡- ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድን እኔና አባ ገብረ ኢየሱስ ስለ ገዳሙ ጉዳይ ልናነጋግራቸው ተዘጋጅተን ነበር:: ቀደም ሲል እንደተገለፀው ትግራይ ላይ የተናገሩት ነገር ለእኛም በቂ መልስ አያስገኝልንም በሚል ልባችንን አሻክሮት ነበር:: ግን ላመሰግናቸው የሚገባ ነገር አለ:: ጎንደር ላይ ሄደው ይቅርታ የጠየቁበት መንገድ ሁላችንንም ልባችንን ሰብሯል:: ትህትና በጣም ብዙ ሰውን ይገነባል:: ሰው ማለት፣ ኢትዮጵያዊነት ማለት እንደዚህ ነው:: ይቅርታ ስለጠየቁ እኛም ደስ ብሎናል:: ወደ ፊት ያለውን ባናውቅም:: ጠቅላይ ሚንስትሩ አፍ አውጥተው በልበ ሙሉነት እንዲናገሩና ወደ መንበረ ሥልጣኑ እንዲመጡ ያደረጋቸው፤ እንዲሁም እነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና አቶ ለማ መገርሳ በድፍረት ነገሮችን እንዲጋፈጡ ያደረጋቸው የህዝብ ጩኸት ነው:: ህዝቡ፤ ተሠቃይተናል፣ እየሞትን ነው፣ እስከመቼ ድረስ እንዲህ እንዘልቃለን ብሎ መትረየስ ያጠመደ ወታደርን ያለ ፍርሃት ሲጋፈጥ ሲያዩት፤ ‹‹ይሄ ህዝብ እየሞተ እየተፈናቀለ የእኛ ሥልጣን ላይ መቆየት ምኑ ላይ ነው?›› በማለት ለማ መገርሳ እስከ መናገር የደረሰው የህዝብ ጩኸት ተሰምቶት ነው:: የተወሠኑ ባለሥልጣናትም በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከህዝብ ጎን በመቆማቸው በጣም ደስ ብሎናል:: አሁን ባለው ሁኔታ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጋ ስንገባ ፍትህ ይሠጡናል ብለን እናምናለን:: ምክንያቱም አሁን አገራችን ትልቅ ውድቀት ላይ ነው ያለችው:: ታሪኳ እየተዘረፈ እየተሸጠ ነው:: ለምሣሌ “ነፍስ ገበያ” የምትባል በመተማ መስመር የምትገኘው ቦታ የሠፈረባት ማነው? ‹‹ተዋበች››፤ ‹‹መድህን›› የሚባሉት ሱዳን ውስጥ ያሉ ቦታዎች የእኛ ነው የነበሩት:: አሁንም ድንበር እየተገፋ ነው:: ማሕበረ ሥላሴም ወደዚያው እየሄደ ነው:: ብዙ ቦታዎች እየተቆራረሱ ነው:: ኢትዮጵያ ማንነቷን ልታጣ ትንሽ ነው የቀራት:: ነገስታት ሁሉ እያከበሩት፣ መባ፣ አምሀ እየሰጡት የመጣው ታላቁን የዋልድባ ገዳምንም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎችን በተመለከተ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር መልስ ይሠጡናል ብለን እናስባለን::

ግዮን፡- ስትያዙ በለበሳችሁት የመነኩሴ ልብስ አንድ ዓመት እንድትቆዩ ተገዳችኋል፣ በእስር ላይ በነበራችሁበት ወቅት ፀሎት በአግባቡ ታካሂዱ ነበረ? የፀሎት መጻሕፍት እንድታነቡስ ተፈቅዶላችኋል?

አባ ገብረ ሥላሴ፡- ሌላ ተለዋጭ የመነኩሴ ልብስ እንዳይገባ ስለከለከሉን እኔም ሆንኩ አባ ገብረ ኢየሱስ መጀመሪያ ስንገባ የነበርንበትን ልብስ እስር ቤት ውስጥ አንድ ዓመት ከሶስት ወር ሙሉ ለብሰነዋል:: መጀመሪያ ቀን ሲይዙን እየደበደቡን ቀደውት ነበር:: ያንን የተቀደደውን እየሰፋን፣ ስንታጠብም እዛው እያጠብን ነው አንድ ልብስ ይህን ያህል ጊዜ የለበስነው:: ይህች ልብስ አሁንም አለች፣ ለታሪክ ተቀምጣለች:: የእኛ ሁኔታ ያሳሰባቸው ወገኖቻችን ልብስ ይዘውልን ሲመጡ ፖሊሶቹ እየደበደቡ፣ ምራቅ እየተፉ፣ እያንጓጠጡ ነበር የሚያባርሯቸው:: እዛ ውስጥ የሚሰሩት ሰዎች የተማሩት ሥነ-ምግባር አይደለም:: ስድብ፣ ዱላና ሌሎች መጥፎ ነገሮችን ነው የሚያውቁት:: ከማዕከላዊ ጀምሮ እሰከ ቂሊንጦ ድረስ ያሉት ሰዎች በጠቅላላ ስድብና ሰውን ማዋረድ ነው ዕውቀታቸው:: ስለ ፀሎቱ ጉዳይ ካነሳን ማዕከላዊ እያለን ኪዳን እናደርስ ነበር:: ስብከተ ወንጌል እንሰብክ ነበር:: ምህላ እናደርግ ነበር:: ይሄን እነሱ ፈቅደውልን ሳይሆን የሚመጣውን ቅጣት እየተቀበልን በገዛ ጉልበታችን ነበር የምናደርገው:: ሰው ይሰበሰባል ፀሎት እንጀምራለን፣ ያኔ ፖሊሶች ዱላ ይዘው ይገባሉ:: ችግር ሊፈጠር ሲል ጥለው ይወጣሉ:: የፀሎት መጽሐፍ ግን የለንም፤ አላስገቡልንም::

አባ ገብረ ኢየሱስ፡- ፀሎቱ ተፈቅዶ አይደለም:: ማዕከላዊ እያለን ሳይቤሪያ የሚባለው የምርመራ ክፍል ቀኑን ሙሉ በሩ ስለሚዘጋ በተዘጋበት ፀሎትህን ታደርሳለህ:: እነሱ ሲመጡ ፀሎቱን አቁሙ ይላሉ፤ እኛ ደግሞ ሰብሰብ ብለን የመጣው ይምጣ በሚል እንቀጥላለን:: ግማሹ ሲፀልይ፣ ግማሹ ይከላከላል እንጂ እነሱ ፈቅደውልን አይደለም የምናካሂደው:: ይሄ በዋናነት ምርመራ የጨረሱ ሰዎች የሚገቡበት ሸራተን የተባለው ቦታ ላይ ነው:: ሳይቤሪያ 8ተኛ ቤት የሚባል አራት ክፍል ያላት ጨለማ ቤት አለች:: እያንዳንዱ ክፍል ብቻህን ነው የምትገባው:: ጠባብና መቆሚያ የሌላት፣ ለስምንት ወይም ለአስር ደቂቃ ፀሐይ አይተህ እንድትመለስ ነው የሚደረገው፤ ይሄ ዋነኛ ማሰቃያ ቦታ ነው::

በር አከፋፈታቸውና ካቴና አስተሳሰራቸው ራሱ ይመጣብሃል:: ማዕከላዊ ድሮ ሮማውያን ሲያደርጉት የነበረው የማሰቃያ ስልት የሚተገበርበት ቦታ ነው:: ብዙ ግፍና በደል ይፈፀማል:: በሰው ገላ መጫወት ምን ያደርጋል? ወንድምህን ለማጥቃት እንዴት ትመኛለህ? ቢያንስ በተጠና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ፣ ባህላዊ በሆነ መልኩ ጥፋተኛ ነው የምትለውን ሰው መመርመርና ማጣራት ሲገባህ በዱላ እንዴት ሰውን ልታሳምን ትሞክራለህ? ሰው በመስቀል፣ በመደብደብ፣ ብልት በማኮላሸት እንዴት ምርመራ ታካሂዳለህ? ይሄ ብልት ማኮላሸት የሚባለው ነገር ለምን አስፈለገ? ሌላ አካል አይደበደብም ወይ? ጣልያኖች እኮ መጀመሪያ በቀጥታ ያደርጉት የነበረው ብልት መቁረጥ ወይም መስለብ ነበር:: ህወሓትም ይሄን ነው እያደረገ ያለው፤ ሌላ አይደለም:: በጣም የሚገርምህ ደግሞ ዘር ለይቶ አማራና ኦሮሞ ተወላጅ በሆኑት ላይ ነው ይሄን የሚያደርገው::

በተጠና ሁኔታ ዘር የማጥፋት ዘመቻ እኮ ነው እያካሄዱ ያለው:: ይሄ ችግር ሲፈፀም የነበረበት ማዕከላዊ አሁን ተዘግቷል እያሉ ነው ግን አይመስለኝም:: እናንተ ብትፈልጉ ይሄን ቢሮ ዘግታችሁ ትሄዳላችሁ፤ በቀጣይ ሌላ ቢሮ ትከራያላችሁ የማዕከላዊ መዘጋትም ከዚህ የተለየ አይመስለኝም:: የቤትና የቦታ ለውጥ ልክ እንደ ትልቅ ነገር በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብሎ “ማዕከላዊ ተዘጋ፣ ሊዘጋ ነው” ማለት ዋጋ የለውም:: ቤቱ ምን አደረገ? መማርና መለወጥ ያለባቸው እዛ ያሉት ሰዎች ናቸው:: እነሱን በስነ-ምግባር ማነፅ፣ መልካምነት ምን ያህል ጥቅም እንዳለው እንዲያወቁ ማድረግ ነው የሚያስፈልገው::

እኔ አሁን ክፉ ከሆንኩ ይሄን ቤት ዘግቼው ብሄድ ምን ትርጉም አለው? የምሄድበት ቦታ ዓመልና ድርጊቴ አብሮኝ ስለሚኖር:: የማዕከላዊ መዘጋት ‹‹ይሄን ሰው አውቆብኛልና ሌላ መግረፊያ ማሰቃያ ቦታ አሉኝ፤ ወይም ልክፈት ነው›› አካሄዱ:: አዲስ አበባ ውስጥ ወገኖቻችን እያለቁ ያሉበት ብዙ የማሰቃያና የመግረፊያ ቦታዎች እንዳሉ በእስር ቆይታችን ተረድተነዋል:: በእነዚህ ድብቅ ማሰቃያ ስፍራዎች ስንት ወገኖቻችን አልቀዋል? ስንት መነኮሳትና ባህታውያን ሞተዋል? በእነዚህ ስለአገራቸው ስለኃይማኖታቸው የሞቱ ሰዎች ደም ላይ ነው ቁጭ ብለን ያለነው::

ግዮን፡- ይሄን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈላችሁት ለዕምነታችሁ፣ ለቤተክርስትያን ክብር ነው:: ጉዳዩ የሚመለከታት ቤተ ክህነት እንደ ተራ ዱርዬ ስትገረፉና ስትጣሉ ዝምታን ነው የመረጠችው:: የታሠሩብኝ መነኮሳት አሉ፣ የቤተ ክርስትያን ክብርና ሞገስ ተገፏል፤ መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ነው በማለት ቤተክርስትያን ለገዥው አካልም ሆነ ለህዝብ ጥሪ ያላስተላለፈችበት፤ መግለጫ ያልሰጠችበትም ሆነ ድምጽዋን ያላሰማችበት ጉዳይ ህዝበ ክርስትያኑን በእጅጉ ያሳዘነ ነበር:: እናንተስ በዚህ ጉዳይ ምን ተሰማችሁ?

አባ ገብረ ኢየሱስ፡– እኛ የቤተርክርስትያን ልጆች ነን:: ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስብንም አሁንም ወደፊትም ከእሷ ህግና ደንብ አንወጣም:: ስለ ዕምነት፣ ስለ አገር፣ ስለ ነፃነት ለመናገር ዶክተር ወይም ሊቀ ጳጳስ መሆን አያሰፈልግም:: ሁሉም ስለ ነፃነቱ ስለአገሩ መናገር ግዴታው ነው:: እኛ በዚህ መካከል ያለን ሰዎች እስከሆንን ድረስ ስለ መብታችን እንናገራለን:: በቂሊንጦ፣ በቃሊቲ፣ በማዕከላዊ መሠል ቦታዎች ያሉ ሰዎች እኮ፤ ነፃነት ያጣሁት እኔ ወንድማቸው ነፃነት አግኝቼ በአገሬ ላይ እንድኖር ስለተናገሩ፣ ስለፃፉ ነው እስር ቤት እየገቡ እየሞቱ ያሉት:: ብዙ ጋዜጠኛችና የነፃነት ታጋዮች በዚህ መንገድ ስለተጓዙ ነው የታሠሩት::

እኔም እናንተም በአገራችን ላይ የዜግነት መብታችን ተከብሮ በነፃነት እንድንኖር ነው የታገሉት:: በሌላ በኩል እኛ ደግሞ ‘‘ቤተ ክርስትያኗ እየጠፋች ነው፤ ቅርስ እየወደመ ነው’’ ነው ያልነው:: ይሄ ሁኔታ ደግሞ ቤተ ክርስትያኗን እናስተዳድራለን ለሚሉት ሰዎች አይዋጥላቸውም:: በመንበረ ፓትሪያርክ ጽ/ቤት ያሉ ሰዎች፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነትና በየሀገረ ስብከቱ ያሉት አብዛኛው ሰዎች በሙስናና በዘረኝነት ታጭቀው የተቀመጡ ሰዎች ናቸው:: በጥቅም የታወሩት እነዚህ ሰዎች የሚያወሩት ስለፖለቲካ ነው እንጂ ስለ ቤተ ክርስትያን አይደለም:: ቤተ ክርስቲያናችን በእነዚህ ሰዎች ተተብትባለች ማለት ነው:: እስቲ ለዚህ አባባል በቂ መረጃ እንዲሆነን ነገሮችን ወደ ኋላ መለስ ብለን እናስታውስ:: ሲኖዶስ ተሰብስቦ አንድ ቀን ስለ ቤተክርስትያን ችግርና ጥፋት፣ ስለአገር ጥቃት ተነጋግሮ ያወጣው መግለጫ አለ ወይ? የለም::

ምክንያቱም የሚሰበሰቡት ደመወዛቸው ላይ ስንት ይጨመር፤ በጀታችን በምን ያህል ይደግ የሚል ካልሆነ በቀር በኃይማኖት ጉዳይ መንግስት ችግር እየፈጠረ ስለሆነ ይሄን ጉዳይ በተቃውሞ መልክ አውጥተን መንገዱ ስህተት መሆኑን ማሳየት አለብን፤ ጉዳዩን ህዝበ ክርስትያኑ እንዲረዳው ማድረግ አለብን ብለው አያውቁም:: ..እነሱ አቶ እገሌ እንዲህ ዓይነት መመሪያ አስተላልፏልና ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ መግለጫ እንስጥ የሚል ካልሆነ በስተቀር በትክክለኛው መንገድ ተጉዘው አያውቁም:: እኛ ከእነሱ የጥቅም መንገድ ወጥተን ለየት ባለ መንገድ ነው የመጣነው:: ስለዚህ እኛን ከማጥላላት፣ ጥቁር ነጥብ ከመጣል ውጭ አጋዥ ሆነውን አይቀርቡም:: ምክንያቱም ቤተ ክርስትያኒቱን እናስተዳድራለን የሚሉት ሰዎች ሌላ፣ እኛ ሌላ ሰዎች ነን::

ልክ እንደ ፖለቲካ ፓርቲና የመንግስት መ/ቤት ቤተ ክርስትያን ውስጥ ተሰግስጎ ያለው ህወሓት ነው:: ግልፅ ሌብነትና ዘረኝነት የተንሠራፋበት ቦታ ነው:: የሳህሊተ ምህረት ሀና ማሪያም ቤተ ክርስትያን ጉዳይ እስካሁን ድረስ ሳይፈታ መቆየት ነበረበት? የጣና ገዳማት ለዝርፊያ ሲዘጋጁ ለምን የሚል የቤተ ክህነት ሰው ነበር?.. ቤተ ክርስትያኖች ሲቃጠሉ ለምን አይሉም? ቢያንስ ቢያንስ ማነው ያቃጠለው? ብሎ እንኳ ጥናት ማድረግ አይሹም፤ ለምን ስራቸውን ስለሚያውቁ:: ለምሳሌ የእንጦጦ ማሪያም ቅርስ ሲዘረፍ ዘራፊዎቹ እነማን ናቸው? በዚህ ጉዳይ ላይስ የቤተ ክህነት ሰዎች ይገቡበታል? ለህዝብ ያሳውቃሉ? ፈፅሞ አይገቡበትም፤ ህዝቡምን የቤተ ክርስትያን አካል አያደርጉትም::

የእነሱ ኃይልና መሳሪያ ህወሓት ነው፤ አምላካቸውም ሥርዓቱ ነው:: እነዚህ ሰዎች እየኖሩ ያሉት በህዝቡ ሐብትና ንብረት ነው:: እኛን በተመለከተ “የቤተ ክርስትያን ልጆች፣ የዋልድባ መነኮሳት ታስረዋል” ብሎ ህዝብ ሲያወራ፣ መላው ሚዲያ ከአገር ባሻገር በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሲያወጣና እነሱም ሲወቀሱ ነበር:: እውነተኞች ወይም ሐሰተኞች መሆናችንን መጥተው እናንተ እነማን ናችሁ? ብለው ለምን አልጠየቁንም:: በታሰርንበት ቦታ ቢጠይቁን እኛም መልስ ለመስጠት ዝግጁ ነበርን:: ከፓትሪያርኩ ጽ/ቤት ይሁን ከጠቅላይ ቤተክህነት ወኪላቸውን ልከው ‹‹እናንተ ከየት ቦታ ነው የመጣችሁት? ማንስ አመነኮሳችሁ? ለምንስ ታሰራችሁ?›› ተብለን መጠየቅ ነበረብን:: እነዚህ ሰዎች የእኛ አይደሉም ብለው ለመመለስ እንኳን መጥተው መጠየቅ ነበረባቸው:: ለኢትዮጵያ ህዝብም በተለይም ለምዕመኑ በጉዳዩ በቂ መልስ መሰጠት ነበረበት:: እነሱ ግን ዝምታን ነው የመረጡት::

ለምን ቢባል የሥርዐቱ አገልጋይ ስለሆኑ ሥራቸው ያሳፍራቸዋል:: እኛን “የቤተክርስትያን ልጆች አይደሉም” እንዳይሉ በደንብ እንተዋወቃለን፤ ማንነታችንን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ማስረጃም ስላለን:: ለምሳሌ እኔ የሰሜን ጎንደር አገረ ስብከት የገዳም ክፍል ሃላፊ ነበርኩ፤ ይሄንን መጥቀስ አልፈልግም ነበር:: በዛ ዘመን በፔሮል ላይ ፈርሜ ደመወዝ የምቀበል ሰው ነበርኩ፤ በተለያዩ ጊዜያት በሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ስሳተፍ የነበርኩ ሰው ነኝ፤ እንዴት ብለው አላወቅንህም ይበሉ? አላውቅህም ቢሉ ደስ ይለኝ ነበር፤ በቂ መረጃ ስላለኝ:: መላው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ክርስትያን ሳይል ከዳር ዳር በእኛ ጉዳይ ሲንጫጫና መንግስት ላይ ግፊት ሲያደርጉ፤ የቤተ ክርስትያኒቱ አስተዳዳሪ ነን ባዮች ዝምታን የመረጡት አዕምሮአቸው በንዋየ ዓለም ስለተጠመቀ ነው::

አሁን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን “ሰው አላት” ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር አንችልም:: እንደውም የሚሠሩ አካላትን ላለማሠራት ችግር የሚፈጥሩ ሰዎች ናቸው ያሉን:: አሁንም እኛ ትግላችን ከእነሱ ጋር ነው:: ቤተ ክርስቲያን ክብሯ ሲገፈፍ፣ እንድትጠፋ ሙከራ ሲደረግባት መቼም ዝም ብለን አናይም::

አባ ገብረ ሥላሴ፡- አባቴ አባ ገብረ ኢየሱስ የተናገሩት ላይ ለመጨመር ያህል፤ እነዚህ በቤተ ክርስትያን ዙሪያ የተሠገሠጉ ሰዎች መሰብሰብያ አድራሻቸው ውሸት ነው እያፈለቀ ያለው:: የእግዚአብሔር ቃል እንዳይነገርበት፣ ዕውነት እንዳይሰበክበት ከፓትሪያርኩ ጽ/ ቤት ጀምሮ እስከ ገጠሯ ቤተክርስትያን ድረስ የራሳቸውን ሰው በማስቀመጥ፤ ህዝበ ክርስትያኑ ጠዋት ለመሳለም፣ ፀሎት ለማድረግ ሲመጣ የሚነገረው ስለ ፖለቲካና ስብስባ እንጂ የእግዚአብሄር ቃል አይደለም::

እንግዲህ እኛ ከተያዝንበት ቀን ጀምሮ አንድ ጳጳስ ወይም ኃላፊ ከአገረ ሥብከት ወይም ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የተናገረ፣ ድርጊቱን ያወገዘ ሰው የለም:: “ይሄ ገዳም እየፈረሠ ነው፤ ይሄ ገዳም እየታረሠ ነው፤ እነዚህ መነኮሳት እውነታቸውን ነው” ያለ አካል የለም:: እኛንም ማብራሪያ የጠየቅን አካል የለም:: ሙት ወቃሽ አያድርገኝና ያኔ ገና ነገሩ ሲጀመር ገዳሙን በተመለከተ የትግራይ ክልል ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ሰው “ገዳሙ ልማት ላይ ቢውል ምን ችግር አለው? እናንተ የልማት ፀር ናችሁ” ነበር ያሉን:: እኛ በዓላማችን ፀንተን ታስረን፣ ተገርፈን ወጥተናል:: እሳቸው ግን ወደማይቀረው ዓለም በፍጥነት ሄደዋል:: በቤተ ክህነት ውስጥ ያሉት ሰዎች ዋልድባ ገዳም ቢታረስ፣ አፅመ ቅዱሳኑ ወጥቶ ቢጣል የሚያሳስባቸው አይደሉም:: አባቶች መጀመሪያውኑ በመፈንስ ቅዱስ የተቃኙ፤ ሥልጣንና ኃላፊነቱን በመንፈስ ቅዱስ የተቀበሉ ቢሆኑ ኖሮ ይሄ ሊሆን አይችልም ነበር::

በእኛ ጉዳይ ከህዝቡ ተነጥለው ዝም ያሉትም ለእዚህ ነው:: አንድ ሰው በሚያገባው ነገር ላይ አውቆ ዝም ካለ ችግር አለ ማለት ነው:: ቤተ ክርስትያን ከፖለቲካ ነፃ መሆን አለባት! ከህወሓት ነፃ መውጣት የሚገባቸው ብዙ ሰዎች አሉ:: በድርጅት የተቃኘ ሰው ቤተ ክርስትያንን ሊመራ ሊያስተዳድር አይችልም:: መንግስት ነኝ ብሎ የተቀመጠው አካል ህዝቡን ሲያስር፣ ሲያሰቃይና ሲገድል ቤተ ክርስትያን የራሷ ሥርዓት አላት፤ የራሷ ህግ አላትና “አቁም” ልትልና ህዝቡን ልትታደግ መጣር ይገባት ነበር:: ቤተ ክርስትያን የፍቅር፣ የሠላምና የአንድነት ተምሳሌት እንደ መሆኗ ችግሩ ሲፈጠር “ተው” ማለት ይገባታል እንጂ ከገዳዩ ጋር አብራ መቆም የለባትም:: አቡነ ማቲያስ እኮ በአደባባይ “ወላጆች ልጆቻችሁን ከልክሉ” አይደል እንዴ ያሉት? ተው እረፍ መባል ያለበት ጥይት የሚተኩሰው ነው? ወይስ መብቱን የሚጠይቀው? እንዲህ ዓይነት ነገር መቅረት አለበት፤ ይሄንን ከህሊናቸው ማውጣት አለባቸው::

ግዮን፡- ከብዙ መከራና እንግልት በኋላ ክሳችሁ ተቋርጧል፤ ውጡ ስትባሉ ምን ተሰማችሁ?

አባ ገብረ ሥላሴ፡– እኛ በግርፋት ብዛት ሰውነታችን ለአስቀያሚ ሽታ ከተዳረገበት ማዕከላዊ ጀምሮ እግዚአብሔር በራሱ ሠዓት ያወጣናል እንጂ ሕወሓት ይፈታናል የሚል ተስፋ አልነበረንም:: አድርገንም አናውቅም:: ህግም፣ ፍትህም ስለሌለ ተስፋችን ቸሩ መድኃኒዓለም ብቻ ነበር:: በነገራችን ላይ ክሳችን በመቋረጡና በመፈታታችን ደስተኛ አይደለንም፤ የተደሰትነው በህዝባችን ብቻ ነው:: ህዝባችን ዕውነታውን ስለሚፈልግ፣ ለዕውነት የቆመ መሆኑን ማወቃችን አስደስቶናል:: ከዛ ውጭ መፈታታችን ትርጉም የለውም:: ብንቆይም ሊያደርጉ የሚችሉትን በሙሉ አድርገውብናል:: የቀራቸው መግደል ብቻ ስለነበር አዲስ ነገር አይጠበቅብንም:: ሁሉንም ከፈጣሪ ጋር ችለናል፣ ተወጥተነዋል:: እኛን ያስፈታን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታስሮ፣ ተደብድቦ፣ ሞቶ ነው ያስፈታን:: ታስረን በነበረበት ጊዜ እንኳ ፍርድ ቤት ሰው እንዲጠይቀን ሲፈቀድ በፖሊስ እየተገፈተረ፣ እየተወረወረ ፀሐይና ብርዱን ተቋቁሞ ነበር የሚጠይቀን:: ሙስሊሞች ሁሉ “አይዟችሁ” እያሉ አበረታተውናል::

ያሠረን ህወሓት ቢሆንም መግለፅ በሚያቅት ሁኔታ መስዋዕትነት ከፍሎ ያስፈታን የኢትዮጵያ ህዝብ ነው:: የእዚህች አገር ፈላጭ ቆራጭ የሆነው ህወሓት እኛን እንደዛ ባለ ሁኔታ ሲያሰቃየን የቤተ ክርስትያኒቱ ኃላፊዎች “ለምን?” ማለት ይችሉ ነበር:: ግን እነሱ ደጋፊ ናቸው፣ የሚያስጨንቃቸው የራሳቸው ጥቅም ብቻ ነው:: ስለቤተክርስትያኑ የሚከፈል መስዋዕትነት፤ ለዕምነት የሚደረግ ትግል አይገባቸውም:: እንደውም ህዝቡ ቀድሟቸዋል:: በስራቸው ቢያዝንም ለእኛ ግን ጊዜውን አካሉን፣ ሕይወቱን ሰጥቶልናል:: አሁንም በጣም ብዙና የተለያዩ ሰዎች ፍትህ አጥተው በቂሊንጦ የተቀመጡ አሉ:: ለምሳሌ አስቻለው ደሴ የሚባል ልጅ ብልቱን አኮላሽተውት እየተሰቃየ ነው:: እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጠኝ፣ እነ አሸናፊ አካሉ፣ እነ ጌታ አስራደን የመሳሰሉ በእስር ቤት ውስጥ በፍትህ እጦት ላይ ነው ያሉት:: አጋየ አድማሱ፣ አበባው ሰጠኝን የመሰሉ በርካታ የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች ለአገር መስራትና ማገልገል እየቻሉ በእስር ላይ ናቸው::

እነዚህ ሰዎች ፍትህ አልባ ናቸው:: እኛ የዘር ጉዳይ ውስጥ የለንበትም:: ሰውን ሰው በመሆኑ ብቻ በእኩል ዓይን የምናይ ነን:: የመጣንበትም ሁኔታ ፍቅርና የሰው ልጅ እኩልነትን የሚሰብክ ነው:: ግን ያየነውን መናገር ካለብን ሰዎች የሚደበደቡትም የሚታሰሩትም ሆነ የሚሰቃዩት ኦሮሞና አማራ በመሆናቸው ብቻ ነው:: አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ የሚባል የዘረኝነት ጉዳይ መቅረት አለበት:: አምላክ የሰውን ልጅ እኩል አድርጎ ነው የፈጠረው:: ይሄ ነገር መቅረት አለበት:: የኃይማኖት አባቶችም ይሄንን ጉዳይ ለምን ዝም ብለው እንደሚመለከቱት ግራ ነው የሚገባኝ:: ህዝቡ ሲደበደብና ህዝቡ ሲገደል፤ ህዝብ በዘረኝነት ሲከፋፈል እና ሲጎዳዳ ዝም ብለው ለምን ያያሉ? እነዚህ ሰዎች በምድር ህግም ሆነ በሠማያዊ ንጉስ ተጠያቂ ናቸው:: እኛ ግን ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው:: ከመናገር ወደኋላ ብለን አናውቅም:: የትኛውንም እግዚአብሄር ከመፍጠር ያልናቀውን ፍጡር ልናከብረው ይገባናል:: ሊገደልም ሊሰቃይም አይገባም:: እኛ ክሳችን ተቋርጦ ብንለቀቅም አሁንም እስር ላይ ነን:: ለበርካታ ዓመታት ታስሮ ያለውን ህዝብ ነው የተቀላቀልነው::

አባ ገብረ ኢየሱስ፡- በኢትዮጵያ ለተፈፀመው ጥፋት ተጠያቂው በአሁኑ ሠዓት ከሥርዓቱ ጋ ሆነው ከጀርባ እያስተባበሩ ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን አባቶች ነን ያሉ ሰዎች ናቸው:: በታሪክም በህዝብም ይጠየቃሉ:: የሰው ልጅ ደም ሲፈስ እያዩ ለምን? ካላሉ የእነሱ አባትነት ምኑ ላይ ነው? አባትነታቸው የሚለካው ከህገ ዕምነት ባልወጣ መልኩ ስለ ሰው ልጅ መብት፣ ነፃነት ሲናገሩ ነው:: የኃይማኖት፣ የሀገርና የህዝብ ፍቅር ሲኖራቸው ነው:: አሁን ያሉት ሰዎች ግን ፖለቲካና አፍቅሮተ ነዋይ ነው ቀፍድዶ የያዛቸው:: እነዚህ ሰዎች ከተጠያቂነትም ሆነ ከነፍስም ለመዳን ከፈለጉ ከዘረኝነት ማነቋቸው መላቀቅ አለባቸው::

ግዮን፡- በቅርብ ወደ ገዳማችሁ (በአታችሁ) ልትመልሱ ነው፤ እዛ ደግሞ እናንተ እስር ላይ ሆናችሁ የህወሓት ሰው በገዳሙ ኃላፊነት መሾሙ ይነገራል:: ገዳም ስትደርሱ ከዚያ አኳያ ምን ዓይነት ነገር ይጠብቃችኋል? መነኮሳቱስ በምን መልኩ ነው የሚቀበሏችሁ?

አባ ገብረ ሥላሴ፡– አሁን እዚህ ሆነን በስልክ እዛ ካሉት ጋር እንገናኛለን:: ገዳሙ አሁን ስላለበት ሁኔታ በቂ መረጃ እናገኛለን:: በተለይ ግድብ ይሠራበታል ተብሎ የሚታሰብበት ቦታ ጥንታዊ ደኖች እየተመነጠሩ ከሠል የማክሠል ሥራ እየሰሩበት ይገኛሉ:: ይሄንን አሁንም እየተቃወምን ነው:: ስለ አቀባበሉ፤ ዋልድባ ሠፊ ነው:: ዋልድባ አብረንታንት፤ ዋልድባ ዳልሻ፣ ዋልድባ ሰቋር ነው ያለው:: አብዛኛው መነኮሳት የእኛ ነው:: ከህወሓት ሰላዮችና አመራሮች ወጪ… እነሱ ከእኛ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አይኖራቸውም:: ድመትና አይጦች ነን፤ ምክንያቱም እነሱና እኛ አላማችን የተለያየ ነው:: መቼም ቢሆን እነሱ ይቀበሉናል ብለን አናስብም፤ መከልከል ግን አይችሉም:: ስለዚህ እኛ ወደ ትግራይ ክልል ወዳለው የገዳሙ “አብረንታት” አንሄድም:: እዛ መሄድ ለአደጋ መጋለጥ ነው:: ዝም ብዬ ልሙት ማለት ካልሆነ በስተቀር:: እነዛ መነኮሳት ወደ አሉበት በትግራይ ወደ ተከለለው ገዳም አንሄድም:: በሌሎች የገዳሙ ክልሎች ግን እንደ ልባችን መንቀሳቀስ እንችላለን:: አስፈላጊ ሆኖ ካገኘነው ወደ እነ አቶ ገዱ ጋ በመሄድ በጉዳዩ ላይ እናነጋግራቸዋለን::

አሁን ወደ ጎንደር ነው የምንሄደው:: የአዲስ አበባ ህዝብ ተቀብሎ እንዳስተናገደን ሁሉ የጎንደር ህዝብም ተቀብሎ ያስተናግደናል፤ ምክንያቱም ከአብራኩ የወጣን ነንና:: የአዲስ አበባ ህዝብ ዘር ቀለም፣ ሐይማኖት ሳይለይ መጥተው ጠይቀውናል፤ ስንፈታም በደስታ አስተናግደውናል:: ታዲያ ለዚህ ህዝብ አትሞትለትም? ይሄን ምስኪን ህዝብ ፊቱ ላይ ቆመህ ስለ መብቱ ልትናገርለት ይገባሃል:: ይሄ የኃይማኖት ቀናኢነት ነው:: ጎንደር ከገባን በኋላ ሰቋር ዋልድባ አለ፣ ዳንሻ ዋልድባ አለ፤ እነሱ ገዳሞቻችን ናቸው፤ የምንኖርባቸው የምንሞትላቸው ገዳማት:: አፈሩን እናገኛለን ብለን የምንጠብቀው ገዳም ስለሆነ ወደ እዛ እንሄዳለን:: ለእነዛ ሰዎች በቂ መልስ ስላለን ዝግጁ ነን ድፍረቱ ኖሯቸው ሊጠይቁን ከቻሉ::

ግዮን፡- በመጨረሻ ለኢትዮጵያ ህዝብ የምታስተላላፉት መልዕክት ምንድን ነው?

አባ ገብረ ኢየሱስ፡– እኛ ለኢትዮጵያና ህዝቧ የምንመኝላት የቀደመ ክብሯ፣ የቀደመው ልዕልናዋ እንዲመለስ፤ ህዝቦቿ በሰላም፣ በፍቅርና በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ነው:: የተለያየ እምነት ውስጥ ያሉ ሰዎች በነፃነት እምነታቸውን እንዲያራምዱ እንሻለን:: ይሄ ምስኪን ህዝብ ያለ መለያየት በሠላምና በደስታ እንዲኖር እንመኝለታለን:: ማንም ቢመጣ አብልቶ አጠጥቶ አስተናግዶ፣ አኑሮ፣ ድሮ የሚሸኝ ደግ ህዝብ ነው:: ይሄን ህዝብ መንካት ፈጣሪን ማስቀየም ነው:: ህዝቡን ዘመን አመጣሽ ነገር ወዲያና ወዲህ ቢያላጋውም መንፈሳዊነቱን አልለቀቀም:: ይሄንን ህዝብ ተግተን ልናገልለግለው ይገባናል::

ደም አፍሳሾች እጃቸውን እንዲያነሱ፣ ህወሓትም ከቤተ ክርስትያን ላይ እጁን እንዲያነሳልን፣ በቤተክርስትያን ያሉ ሰዎች አምልኮተ እግዚአብሄርን በቅድስናና በንፅህና እንዲያደርሱ ነው የምንመኘው የምንፀልየው:: ኢትዮጵያ ውስጥ እኔ በግሌ የኃይማኖት መንግሥት እንዲመሠረት አልፈልግም፤ ነገር ግን መንግስት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ላይ እጁን እንዲቀስርባት ደግሞ አልፈቅድላቸውም:: ምክንያቱም ይህች ቤተ ክርስትያን ለዚህች አገር ባለውለታ ናት:: ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣ፣ ፊደል ቀርፃ ለዓለም ያስተላለፈች፣ ድንበር ጠብቃ እስካሁን ድረስ አገሪቷን አስከብራ የምትኖር ቤተ ክርስትያን ናት:: በዚች ቤተ ክርስትያን ላይ ማንም ይንገስ ማንም እጁን እንዲቀስር አንፈቅድለትም::

ቤተ ክርስቲያናችንን አክብሮ ሊይዝ ይገባዋል:: ማንም ተመረጠ ማንም ነገሰ ይሄ ግዴታው ነው:: በቤተ ክርስቲያናችን ክብር፣ በሀገራችን ክብር ላይ ግን መቼውንም አንላቀቅም:: በአገራችን፣ በእምነታችን ላይ ህይወታችንን መስዋዕት እናደርጋለን:: በመጨረሻ መላው የኢትዮጵያ ህዝብን እግዚአብሄር ያክብርልን ነው የምለው:: ሌላው ዲያቆን ዘመድኩን በቀለ፤ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራውን በጣም አመሰግኑልን፤ ከታሰርን ጀምሮ ብዙ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ ትልቅ ሚና የተጫወቱ ናቸው::

አባ ገብረ ሥላሴ፡– ወደ ገዳማችን ልንሄድ በዝግጅት ላይ ነን:: ፈፅሞ አንቀርም:: እዛ ቦታ ላይ በህወሓት የተቀመጡት ሰዎች እኛን በሌላ ሊያዩን ይችላሉ፤ ግን ይሄ ጉዳያችን አይደለም:: እኛ ከታሰርን በኋላ ዋልድባን ለሁለት ከፍለውታል:: አበረንታትን ወደ ትግራይ፣ ዳንሻና ሰቋርን ወደ አማራ አድርገውታል፤ ለአሁን ማለት ነው:: ስለዚህ አሁን ለህይወታችን አስጊ የሆነበትን ቦታ ትተን በእነዚህኞቹ ገዳማት እንኖራለን:: ወደፊት ግን ገደማችን ስለሆነ መሄዳችን አይቀርም:: ሌሎች መነኮሳት በደስታ ነው የሚቀበሉን:: በገዳሙ ህግና ደንብ መሠረት ማንም ሰው ሲመጣ እግር አጥበው፣ አስተናግደው በረከት የሚቀበሉ መነኮሳት ናቸው ያሉት:: ስለዚህ እንኳን ለእኛ ለሌሎችም ገዳሙ ክፍት ነው:: የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር በጎሳ እንዳይለያይ፣ ሁሉም የራሱን ኃይማኖት ጠብቆ በመያዝ የሌላውን ሳይነካ በፍቅርና በሠላም እንዲኖር እመኝለታለሁ:: እግዚአብሄር “ወደ ሁለት ነገሮች እጅህን ስደድ፣ እኔን ብታመልከኝ ህያው ትሆናለህ፣ ትድናለህ፤ ወደ እሳቱ እጅህን ብትሰድ ግን ትሞታለህ” ነው ያለው አዳምን:: ስለዚህ እግዘአብሄር የሰጠውን ነፃነት ሰው ሊነፍገው አይገባም:: ህዝባችን ታግሎልናል፣ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎልናል፤ ሁሌም እናመሰግነዋለን፤ በፀሎት እናስበዋለን:: ቤተ ክርስትያን ግን ቃለ እግዚአብሔር የሚነገርባት፣ ስብሐት እግዚአብሔር የሚደረስባት፣ የተማሩ አባቶቻችን የሚያገለግሉባት፤ ውዳሴ ማርያም የሚደገምባት ቦታ እንድትሆን ነው ምኞቴ፤ መልዕክቴም ይሄው ነው::

ግዮን፡- ከልብ እናመሠግናለን::

 

Share.

About Author

Leave A Reply