የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሠራተኞች ደመወዛቸው በመዘግየቱ ቅሬታ አቀረቡ

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

በፀጥታና በደኅንነት ሥራዎች የተመደቡ ሠራተኞች ሰሞኑን በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ላይ በሙስና ምክንያት በሚካሄደው ማጣራት ሳቢያ፣ ወርኃዊ የደመወዝ ክፍያ እንደዘገየባቸው በመግለጽ ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፀጥታ ሠራተኞች እንደገለጹት፣ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሥር በሚገኙ ልዩ ልዩ ክፍሎች ተመድበው በኤርፖርትና በሌሎችም ተቋማት ውስጥ በጥበቃ ሥራ ላይ ቢሆኑም፣ ከተለመደው የክፍያ ጊዜ ከአራት ቀናት በላይ ደመወዝ ዘግይቶባቸዋል፡፡ የክፍያው መዘግየት አግባብ አለመሆኑ ብቻም ሳይሆን፣ እስኪጣራ በሚል ሰበብ ደመወዛቸው ሳይከፈል ለሳምንት ያህል መዘግየቱን ሠራተኞቹ አልተቀበሉትም፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር በስልክ አነጋግሮአቸው ምላሽ የሰጡት የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መምርያ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ አልማ፣ የደመወዝ መዘግየቱ በሠራተኞቹ እንደተጠቀሰው ከወቅቱ ዕርምጃ ጋር አይገናኝም፡፡ ይልቁንም ግፋ ቢል ለሦስት ቀናት መዘግየት የታየው በመሥሪያ ቤቶች ውስጥ በሚደረገው የተቋማት ማዘዋወር ሒደት ሳቢያ ነው ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል የጥበቃ መምርያን ጨምሮ የዜግነትና የኢሚግሬሽን ጉዳዮችን የሚከታተለው ተቋም ተጠሪነቱ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ነበር፡፡

በአዲሱ የተቋማት አወቃቀር ግን የዜግነትና የኢሚግሬሽን መምርያ የፌዴራል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲን ተቀላቅሏል፡፡ በተቋማቱ መካከል መከናወን የሚገባቸው የኦዲትና የሒሳብ ማወራረድ ሥራዎች የደመወዝ ክፍያውንና የተወሰነ የፔቲ ካሽና የመጠባበቂያ ክፍያን ለጥቂት ቀናት ቢያዘገዩትም፣ መላውን ሠራተኛ ያካተተ የደመወዝ መዘግየት እንዳልተፈጠረ አቶ መንግሥቱ ገልጸዋል፡፡

የመጀመርያው ሩብ ዓመት የበጀት ኦዲት እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በአብዛኛው የደመወዝ መክፈያ ጊዜም በወሩ መጨረሻ ቀናት ከ24 እስከ 25 ባሉት ውስጥ እንደሚፈጸም አስረድተዋል፡፡

ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋናው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ለመረዳት እንደተቻለው፣ የደመወዝ ክፍያ ቀደም ሲል ዘግይቶባቸው እንደማያውቅና በአብዛኛውም ወር በገባ ከ23ኛው ቀን ጀምሮ ክፍያ እንደሚፈጸምላቸው ነው፡፡ ከሁለት ወራት ወዲህም ክፍያቸው በባንክ በኩል እየተፈጸመ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

(ሪፖርተር)

Share.

About Author

Leave A Reply