የብአዴን 12ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ መስከረም 17 ይጀመራል

Google+ Pinterest LinkedIn Tumblr +

ብአዴን 12ኛ ድርጅታዊ ጉባዔውን መስከረም 17 መካሄድ እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ብናልፍ አንዱዓለም በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ጉባዔው ከመስከረም 17 ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በባሕር ዳር እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ 12ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ “የለውጡ ቀጣይነት ለአማራ ህዝቦች ተጠቃሚነት እና ለዴሞክራሲያዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

ጉባኤው ባለፉት ዓመታት ከተካሄዱት ጉባዔዎች በተለየ መልኩ እንደሚካሄድ የጠቀሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል አቅጣጫ የሚቀመጥበት፣ ብአዴን የለውጥ ድርጅት ሆኖ እንዲወጣ ውይይት የሚደረግበት እንደሚሆንም በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

ለአራት ቀናት በሚቆየው በ12ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ባለፉት ሦስት ዓመታት በድርጅቱ የለውጥ እንቅስቃሴዎች የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንደሚገመገሙና የኦዲት እና የቁጥጥር ሪፖርት እንደሚቀርብም ይጠበቃል፡፡

እንዲሁም በቀጣዩ ሁለት ዓመታት ድርጅቱን የሚመሩ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫም ይካሄዳል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በድርጅቱ ስያሜና ዓርማ ላይም ጉባኤው መክሮ እንደሚወስንም አንስተዋል፡፡

በጉባኤው በድምፅ እና ያለ ድምፅ የሚሳተፉ አባላት፣ በክልሉ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሁራን፣ ባለሀብቶች እና ወጣቶች በተጋባዥነት ይገኛሉ፡፡

Share.

About Author

Leave A Reply